20 ሚሊዮን ብር ለኢህአዲግ ከንግዱ ማኅበረሰብ
ፍቅሩ
ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 3 ቀን 2002 ዓ.ም. የወጣው በሀገር ቤት የሚታተመው የእንግሊዝኛው ”ፎርቹን” ጋዜጣ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች ለኢህአዲግ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ 20 ሚሊዮን ብር እንዳዋጡ ዘገበ። ’እሰየው!’ የሚያሰኝ ክንውን ነው - ከምርጫ 97 በኋላ የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲህ በግላጭ የሚደግፈውን ፓርቲ ማሳወቁ ’ይበል!’ የሚያሰኝ ነው። በንግድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች እንዲህ በድፍረት የሚደግፉትን ፓርቲ ሲያሳውቁ ለሁሉም ጥሩ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ የፈቀደውን ፓርቲ የመደገፍ መብት አለውና።
ችግሩ ያለው የት ነው አትሉም? ... የማስታወስ ችሎታዬ ካልከዳኝ ባለፈው ምርጫ ተቃዋሚዎችን ደግፋችኋል የተባሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የተለያየ እንግልት እንደደረሰባቸው ትዝ ይለኛል። የገዥውን ፓርቲ በትር በመፍራት የተቃዋሚዎችን ዓላማ ደግፈው የሚወጡ ተመሳሳይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከሌሉ ግን ችግር አለ ማለት ነው።
በፎርቹን ጋዜጣ የቀረበውና የሚጎረብጠው አስተሳሰብ በአትዮጵያ የአበባ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ፀጋዬ አበበ የተነገረው ነው። ገዥውን ፓርቲ መደገፉ እንዳለ ሆኖ፤ የደገፉበት ምክንያት ግን ፕሬዝዳንቱ የምርጫን ምንነት መገንዘባቸውን የሚያጠራጥር ነው።
“የንግድ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጭንቀት የንግድ እንቅስቃሴው ከምርጫው በኋላ እንዳይሰናከል ነው” ይላል የሰጡት ምክንያት።
አቶ ፀጋዬ ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ አይመስልም። መገመት ግን አያዳግትም። አንድም ተቃዋሚዎች ሥልጣን ከያዙ ሀገር ይበጠበጣል የሚለውን የገዥውን ፓርቲ ሃሳብ እየተጋሩ ነው። ይህም መጭው ምርጫ ሥልጣን በሠላም የሚተላለፍበት አይሆንም ከሚል ድምዳሜ የደረሱ አስመስሎባቸዋል።
ሌላው ደግሞ ገዥው ፓርቲ አለማም አጠፋም ሥልጣኑን መቀጠሉ ለንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚበጅ ነው። ይኽኛው አስተሳሰብ አደገኛነቱ የሚያመዝን ነው። ምክንያቱም በአገዛዙ የተለየ ተጠቃሚ ስለሆኑ ወይንም በሌላ ምክንያት ’ከማላውቀው ሰይጣን ይሻለኛል ...’ ማለቱ የ’እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ አይነት ስግብግብነት ነው። እልፍ ሲልም ከገዥው ፓርቲ ጋር ድብቅ አጀንዳ እንዳለ የሚያሳብቅም ይመስላል።
ይህ በእንዲህ እያለ ታዲያ ኢህአዲግ ሌሎች የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሳሳይ የገንዘብ መዋጮ ቢያደርጉ በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን መጠርጠር ደግ ነው። ”በቂመኝነት ተወዳዳሪ የለውም” ከሚባለው ፓርቲ ክፉ ክፉውን ማሰብ የሚከፋ አይደለም። በርግጥ ይህንኑ አስቀድመው የሚጠረጥሩት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንዲህ በግላጭ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊነታቸውን ያሳውቃሉ ማለት ዘበት ነው።
ምናለ በምርጫው የመጨረሻ ውጤት ላይ እምነት ቢኖረን? ምርጫው ፍትሃዊና ነፃ ይሆናል እያልን ከሆነ እኮ ውጤቱን በፀጋ መቀበሉ ቀላል ነው። ያ ደግሞ ያለምንም ግርግር የሚጠናቀቅ ነው።
ከምርጫ 97 ድንጋጤ በኋላ ገዥው ፓርቲ ያኔ የሆነው እንዳይደገም ሲሠራ መሰንበቱ ብዙ ጊዜ የተነሳ ሐቅ ነው። ከእስካሁኑ አካሄድ እንደምንረዳው ኢህአዲግ መጭውን ምርጫ እንደሚያሸንፍ የሚጠራጠሩት በጣም ጥቂት ናቸው። ለዚህም ይመስላል የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በግላጭ ለመደገፍ የተነሳሱት።
ፎርቹን እንደዘገበው ገዥውን ፓርቲ ይበልጥ ለማጠናከር በቅርቡም 10 ሺህ የሚሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን ያካተተ ተመሳሳይ የገንዘብ ማዋጣት ይከናወናል።



