አሥራት አብርሃም

በጊዜ ምንገባው

ማምሸቱን የተውነው

ሌባ ወይም ሰይጣን

አይደለም … የፈራነው

ፅልመት ተገን አርገው

Aregawi Gebreyohannes, አረጋዊ ገብረዮሐንስማጅራት የሚመቱ

ገዥዎች ስላሉ ነው።

ይህ ግጥም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ ተቀዋሚ ፖለቲከኞች ስጋት የሚያመላክት ነው። የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት ቀን ህዝቡ እያየ በተቀዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ሲብስባቸው ወይም ሲደነግጡ ካልሆነ በስተቀር ጥቃት ለማድረስ አይደፍሩም። ማታ በጭለማ ከሆነ ግን እንድትመታ ወይ ማጅራት መቺ ገዝተው፣ ወይም ከአሁን በፊት በሆነ ነገር የተጣላህን ሰው ፈልገው፣ “አይዞህ! እንደፈለክ አድርገው!” ብለው ይልኩብሃል። ዕድለኛ ከሆንክ ተደብድበህ በሕይወት ትተርፋለህ። እስካሁን አራት የዓረና-መድረክ ተወዳዳሪዎች በዚሁ መልክ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው ከሞት ብቻ ተርፈዋል። ድንገት ጎደሎ ቀን ከገጠመህ ደግሞ ሞትህ የግድ ይሆንና ልክ እንደ አረጋዊ ገብረዮሐንስ የሠላማዊ ትግል ሰማዕት ሆነህ ትሞታለህ።

 

ለምሳሌ ከፍተኛ ድብደባ ከተፈፀመባቸው የዓረና-መድረክ ተወዳዳሪዎች፤ አቶ አያሌው በየነ የተባለ በወቅሮማራይ የምርጫ ክልል መድረክን ወክሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር በወታደሮች ተቀጥቅጦ፣ ንብረቱንም ተቀምቷል።

 

አቶ ስሙር አባዲ በቆላ ተምቤን በአግበ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር ከገጠር የመጡት ዘመዶቹን ሸኝቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ የፌደራልና የዓብይዓዲ ከተማ ፖሊሶች እንዳይሆን አድርገው ከደበደቡት በኋላ “ሞቷል” ብለው ጨለማ ላይ ጥለውት ሄዷል።

 

አቶ አወል ኢብራሂም የተባለ የዓቢይ ዓዲ ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ በመዝናኛ ቦታ እያለ የሰከሩ በሚመስሉ ሰዎች ተደብድቧል።

 

መምህር ገብረፃዲቅ ደስታ የተባለ በሰንቃጣ የምርጫ ክልል የሚወዳደር ደግሞ አሁን በሚኖርበት በሽሬ ከተማ “ሀገር አማን ነው” ብሎ ወደ ቤቱ ሲገባ የባለቤቱ የቀድሞ “ጓደኛ” ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን አድብቶ ደብድቦት ሂዷል። በእርግጥ አሁን ወደ ምርጫው ከገባን ጀምሮ እየደረሱብን ያሉትን ጥቃቶች ሁሉም እንዘርዝር ብንል የተነሳንበትን ሃሳብ ሳንገልፅ ጊዜው ያልቅብናል። በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ የዓረና-መድረክ አባል ሆነህ መገኘት ለሁሉም ዓይነት ጥቃቶች የተጋለጥክ እንድትሆን ያደርገሃል። ላንተ የሕግ ከለላ የሚሰጥህ አካል ፈፅሞ አታገኝም። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደህ “ጥቃት ደረሰብኝ” ካልክ መሳቂያ ነው የምትሆነው። ለምሳሌ አቶ አወል ኢብራሂም ተደበደብኩ ብሎ ለፖሊስ ሲያመለክት የወንጀል መርማሪው ፖሊስ “ይህ መንግሥት ያንተ መንግሥት አይደለም። ከፈለክ ለመራራ ጉዲና ሄደህ አመልክት” ነው ያለው። አወይ ጉዳችን! እኛማ መንግሥት አለን፤ በመጠኑም ቢሆን የሕግ ልዕልና አለ ብለን ነው እንጂ፤ እንዲህ በጫካ ሥርዓት የምንተዳደር መሆናችን ብናውቅማ … መቼ እንዲህ ተዘፋዝፈን እንገኝ ነበር!

 

ወደ ተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ስናመራ ለመሆኑ አረጋዊ ገብረዮሐንስን ማን ገደለው? ለምንስ ተገደለ? ከግድያው ጀርባ ያለውስ ዓላማ ምንድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው። በእርግጥ ለሁሉም በአረጋዊ ገብረዮሐንስ አሟሟት ዙሪያ ለሚነሱት ጥያቄዎች የሚሆን መልስ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። በሂደት ዘመንና ሁኔታዎች ሲመቻቹ ከቀጥተኛው ገዳዩ ጀምሮ እስከ ላይ እንዲገደል ትዕዛዝ እስከ አስተላለፉት የክልሉ ባለሥልጣናት ድረስ ያለውን ሰንሰለት የሚጋለጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

 

እዚህ ላይ እኔ ለመግለፅ የምሞክረው እስካሁን ድረስ የተገለጠው ሐቅና ግድያው የተፈፀመበትን ሁኔታ ወይም አፈፃፀሙን በተመለከተ ጥቂቱን ነው።

 

በነገራችን ላይ ከአረጋዊ ጋር የቆየ እውቂያ ነው ያለን። ዓረና ከመፈጠሩ በፊት ልክ የዛሬ 5 ዓመት በ1997 ዓ.ም. እሱ የንግዱን ሥራ እያካሄደ ጎን ለጎን ይማር ስለነበረ፤ ለተወሰነ ጊዜ መምህሩ ሆኜ ነው የተገናኘነው። በሽሬ ከተማ “ባድሜ ዘመናዊ የፀጉር ማስተካከያ” የሚል ከፍቶ ነበር የሚሠራው። ከዚያ ወዲያው ወደ አድዋ መምህራን ኮሌጅ በመዛወሬ ተለያየን። ዕጣ ክፍላችን ሆኖ መሰል ሁለታችንም ከሁለት ዓመት በኋላ ሽሬ የዓረና አባላት ስብሰባ ሄጄ እሱም አባል ሆኖ እዚያው እንደገና ተገናኘን።

 

አረጋዊ ምንም ወጣት ቢሆን በሳል አስተሳሰብ የታደለ፣ በንግድ ሥራ ራሱን ችሎ የሚተዳደር ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበር። ምንም እንኳ የብዙ ቤተሰብ ኃላፊነት ቢኖርበትም የዓረና አባል ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በምዕራብና በማዕከላዊ የትግራይ ዞኖች ያሉትን አባላት በማንቀሳቀስና በማስተባበር ፈፅሞ ታይቶ የማይታወቅ የአዳዲስ አባላትን ንቅናቄ መፍጠር ችሏል። ከዚህም በአሻገር ድርጅቱ ያለበትን የገንዘብና የሰው ኃይል ውሱንነት ተገንዝቦ ማንንም ሳይጠብቅ የራሱን ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ተጠቅሞ የተሰለፈለትን ዓላማ ግቡን እንዲመታ ብዙ ለፍቷል።

 

የእሱን አርኣያ በመከተል ብዙ ወጣቶች በድፍረት ድርጅቱን ተቀላቅለው በብዙ አካባቢዎች ዓረና በሁለት እግሩ እንዲቆም አስችለዋል። በዚህ ጥንካሬውና በአደረገው አስተዋፅዖ ነው በ”ነበለት” ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች መድረክን ወክሎ እንዲወዳደር ታጭቶ የነበረው። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን ከብዙ ውጣ ውረድና እንግልት ጋር ነበር። በየጊዜው በፀጥታ ኃይሎች እየተያዘ ለሰዓታት ያህል “ወረቀት በተንክ፤ ሰው አነጋገርክ” እየተባለ ታስረዋል። እኛ መቀሌ ላይ ስናመለክት ደግሞ ወዲያው ይለቀቅና እንደገና ደግሞ በሌላ ቦታ ይይዙታል። እንደገና አቤት ብለን ይለቀቃል። እንደዚያ ነው አብዛኛው የእኛ እንቅስቃሴ። የተለመደ ነገር በመሆኑም ከዚያ የከፋ ሕይወትን የሚጠይቅ ነገር እንዲህ በቀላሉ ያጋጥማል ብለን አብዛኞቻችን አላሰብንም።

 

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አረጋዊ ላይ ይደርሱ የነበሩት ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች በሌሎች አባሎቻችንም ላይ ይደርሱ ስለነበረ ብዙም የተለየ ትኩረት አላደረግንበትም።

የካቲት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. ግን ከወደ ሽሬ የተሰማው መርዶ አዕምሮን የሚያደነዝዝ ህሊናን የሚያስት ነበር። አረጋዊ በጩቤ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን የሚገልጽ መርዶ። እኔ በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ በአንድነት ቢሮ እያለሁ ነው የሰማሁት። እዚያ ለመቆየት የነበረኝን ፕሮግራም ሰርዤ ወዲያው ነበር ወደ ትግራይ የተመለስኩት። አባቴ ድንገት መነሳቴ ገርሞት ሲጠይቀኝ ስጋት እንዳይገባው ብዬ ስለጉዳዩ የነገርኩት ነገር አልነበረም። ኋላ ነገሩን በዜና ሲሰማ በጣም ነው የወቀሰኝ። እንደሰማሁት ከሆነ ከዚያ በኋላ እንቅልፍ የለውም። “የልጄን መርዶ ከዛሬ ነገ ይነግሩኛል” እያለ ራሱን ለጭንቀት ዳርጓል።

 

የህወሓት ጭካኔ ታጋይ ሆኖ ያውቀዋል። በጭለማ ዋሻ ውስጥ እንዳይሞት ትንሽ የሚቀመስ ምግብ እየሰጡ እኛን “ሳታስፈቅድ ወደ ቤተሰብህ ሄድክ” ብለው አስረውት ከሞት በተዓምር ያመለጠበትን አጋጣሚ ምንም ዘመኑ ቢረዝም አይረሳውም። ዛሬ ለእኔም ትውልድ ደርሰው እነዚህ ሰዎች በልጁ ሕይወት ላይ መፍረድ የሚችሉ መሆናቸውን ሲያስብ እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ ኣባል የሆንኩበትን ቀን እየረገመ መኖር ዕጣ ክፍሉ ሆኗል።

 

ወደ ጉዳዩ ልመለስና የአረጋዊ ነገር እርግጥ ሆኖ እርማችንን አወጣን። በብዙ አባሎቻችን ዘንድ ቁጣና እልህ ጎልቶ ይታይ ነበር። “እናንተ ናችሁ ሕግ አለ ... ምንትስ እያላችሁ እያስገደላችሁን ያላችሁት” ያሉኝ አባላት ነበሩ። በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ፍፁም ተስፋ መቁረጥ ይታይ ነበር። ወዲያው አባሎቻችንን የማረጋጋትና የማጠናከር ሥራ ባንሰራ ኖሮ ሁኔታዎች እጅግ በጣም አስቸጋሪ ይሆኑ ነበር። መቼም የአረጋዊ ሞት የእያንዳንዳችንን የግል ሕይወት በእጅጉ የነካ ጉዳይ ሆኖ ነው ያለፈው።

 

አሁን ዙሪያ ጥምጥሙን መጓዝ ትቼ ወደ ጉዳዩ በቀጥታ ልግባና የአረጋዊን አሟሟት በተመለከተ ታላቅ ወንድሙ አቶ ዓለም ገብረዮሐንስ ካሰፈሩት ጽሑፍ እነሳለሁ። ይህን የምልበት ምክንያት ጽሑፉ ሁሉም የሚያውቀውና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሳይቀር እንዲደርሳቸው ተደርጎ በሰነድነት የተያዘ በመሆኑ ነው።

 

“የወረዳው መርማሪ ፖሊስና አቃቤ ሕግ ግድያው “በመጠጥ ቤት ሂሳብ ክፈል አትክፈል” በሚል የተነሳ ተራ ጠብ ምክንያት የተፈፀመ በማስመሰል ሌሎች ተባባሪዎችን ወደ ጎን በመተው በቀጥታ በጩቤ ወግቶ የገደለውን ግለሰብ ላይ ብቻ ማትኮሩ አግባብነት የሌለው ነው። በሟች ቤተሰብ እምነት ምንም እንኳ በቀጥታ ወንጀሉን የፈፀመው በጩቤ የወጋው ግለሰብ ቢሆንም የግድያው አፈፃፀምና ዓላማ ግን በመጠጥ ቤት በተነሳ የሂሳብ ንትርክ የተፈጠረ ሳይሆን ሌላ መነሻ ያለው ነው የሚል ነው።” ይህም በየካቲት 22 ቀን 2002 ዓ.ም. ማታ ስድስት ሰዓት አካባቢ መብራህቶም ጉዕሽ የተባለው ግለሰብ ወደ ሟች መጠጥ ቤት ገብቶ ትንሽ ቁጭ ካለ ኋላ ምንም ነገር ሳያዝ ተመልሶ ወጥቶ ሄዷል። ትንሽ ቆይቶ ግን ገዳዩን ፅጌ ብርሃነ እና ክብሮም ገብሩ የተባሉ ግለሰቦች መጥተው ቁጭ አሉ። በመጀመሪያ ወጥቶ የሄደው መብራህቶም ጉዕሽና ምላው በየነ ገብተው ከእነዚያ ራቅ ብለው እንደማይተዋቁ ሆነው ተቀመጡ። እንደገና ትንሽ ቆይቶ ተክሌ ማዕሾ የተባለ ሌላው ተባባሪ መጥቶ ለብቻው ተቀመጠ።

 

ከዚያ አምስቱም ቦታ ቦታቸውን ይዘው እየጠጡ ሳለ ሟች መጥቶ “ጊዜው በጣም ስለመሸ የያዛችሁትን መጠጥ ጨርሳችሁ ወደ ቤታችሁ ሂዱ እኛም መተኛት እንፈልጋለን” ሲላቸው እነርሱ መጠጣት እንደሚፈልጉ ስለገለፁለት ጀነሬተሩን አጥፍቶ በምትኩ ሻማ አብርቶላቸው ለሠራተኛዋ አስረክቧቸው ወደ መኝታው ሄደ። ከዚያ ኋላ ሁሉም ወደ አንድ ጠረጴዛ ተሰባሰቡና ቁማር መጫወት ይጀምራሉ። ከሌሊቱ 8 ሰዓት አከባቢ እርስ በርስ የተጣሉ በማስመስል የቢራ ጠርሙሶችን ወደ መሬት መከስከስ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ሟች የጩኸት ድምፅ ሰምቶ ወደ ቡና ቤቱ ተመልሶ ይገባልና “ምንድነው የተፈጠረው?” ብሎ ሳይጨርስ ፅጌ ብርሃኔ የተባለው ግለሰብ በጩቤ ሆዱን ወጋው። እንደገና ማጅራቱ ላይ ደገመው። ሟች ወደ መሬት ሲወድቅ ከኋላ እንደገና በመዞር ትልቁን የእግሩን የደም ስር በያዘው ጩቤ ቆረጠው። ይህ ሁሉ ሲሆን እዚያ የነበሩት ሌሎች ቆመው ግድያው በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ይመለከቱ ነበር። የሚረዳ ሌላ ሰው እንዳይመጣም ለመካላከል የተመደቡ ነበር የሚመስሉት።

 

ጉዳዩን ያላወቀ አንድ የአካባቢው ሚሊሽያ ጩኸት ሰምቶ ወደዚያ እያመራ ሳለ አንዱን ተባባሪ መንገድ ላይ አግኝቶት ነበር። “ምንድነው ጩኸት የምሰማው?” ብሎ ሲጠይቀው “እኔ አላውቅም ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነው።” ይለዋል። ኋላ እሱም እንደነበረበት ሲያረጋግጥ ግን ተከታትሎ እሱም ከሌሎቹ ጋር ሊይዘው ችሏል። ቀንደኛውን ገዳይ ግን ህዝቡ ነው ሊያመልጥ ሲል ተባብሮ በነጋታው የያዘው።

 

በግድያው የተሳተፉት ግለሰቦች ብዛት አምስት ቢሆኑም፤ የወረዳ አስገደ ፅምብላ ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ ግን ግድያው በቀጥታ በጩቤ ወግቶ የገደለውን ብቻ በመያዝ እነዚያ ደግሞ ምስክሮች እንዲሆኑ በማድረግ ጉዳዩን በቻለው አቅም ሁሉ ለማድበስበስ ብዙ ጥረት አድረጓል።

 

ከዚህም በአሻገር መንግሥት ጉዳዩ የግል ፀብ ለማስመሰል ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሰርቷል። ጉዳዩ በዳኛ ተይዞ እያለ የወረዳው አስተዳዳሪ ግድያው የግል ጠብ መሆኑን ሲገልጥ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዴ “በጠብ መካከል ሊገላግል ገብቶ ነው የተገደለው” ሲሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “በደንበኛው ነው የተገደለው” ሲሉ በዳኛው ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ሃሳቦችን በሚዲያዎቻቸው ሲያሰራጩ ነበር። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ የማስታወቂያ ሚንስትሩ ለውጭ ሚዲያዎች የሰጡት መግለጫ ነው። አቶ በረከት ስምዖን “Aregawi was killed in bar fight” ነበር ያሉት። በሀገራችን መዋሸት ነውር ነው። ባህላችንም አይደለም። አንድ ሰው ሚንስትር ሆኖ ሲዋሽ መስማት ደግሞ ጦሱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአዲሶቹም ትውልዶች የሚተርፍ ነው። የሚዋሹ መሪዎች ያሉት ህዝብ ምን ዓይነት ትውልድ እንደሚያፈራ መገመት ይቻላል። በመሰረቱ አረጋዊ የተገደለው በራሱ ቤት ውስጥ ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንዲያ ቢሆንስ “መጠጥ ቤት የተገኘ ይገደል” የሚል ሕግ የለም። እንደዚህ ዓይነት ክርክር የምናመጣ ከሆነ ደግሞ ጀግናው ኃየሎም አርኣያም የተገደለው መጠጥ ቤት እንደነበር ሁላችንም የምንዘነጋው አይመስለኝም። ስለዚህ ዋናው ነጥብ መሆን ያለበት ግድያው ሆቴል ውስጥም ይፈፀም ቤተክርስቲያን ውስጥ የአፈፃፀሙ ሁኔታና ዓላማ ነው።

 

ከዚህ አንፃር የአረጋዊ ገዳይ ወደ አረጋዊ ግሮሰሪ ጩቤ ይዞ መግባቱ ግድያውን ለመፈፀም ሆን ብሎ ቀድሞ ተዘጋጅቶ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። እንዲያውም ጩቤው በምን መልክ እንዳገኘውም ጭምጭታ እየተሰማ ነው።

 

ሌላው ነጥብ ሌሎቹ ተባባሪዎች ሰው እንደ በግ ሲታረድ እያዩ ለመግታት ወይም ለመጮህ ምንም ዓይነት ጥረት ያለማድረጋቸው የሌሎችም እጅ እንዳለበት ሌላው ጥሩ አመላካች ነው።

 

እንደገና የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በደንብ ሳያጣራ የሌላውን አፍ ለማዘጋት የተፈለገ በሚያስመስል መልኩ በፍጥነት ገዳዩን በ15 ዓመት ሌሎቹ ተባባሪዎች ደግሞ በነፃ አሰናብቶ ምስክር እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። ይህ ግድያ የሕግ ባለሞያዎች እንደነገሩን ከሆነ የጭካኔ አገዳደል በመሆኑ ከፍ ሲል በሞት ዝቅ ሲል ደግሞ በዕድሜ ልክ እስራት ነው የሚያስቀጣው።

 

አሁንም ቅድም የጠቀስኩት ተመሳሳይ ግድያ ለንፅፅር እንመልከት። የደህንነት ኃላፊው የአቶ ክንፈ ገብረመድህን ገዳይ እና የኃየሎም ገዳይ ሁለቱም በጥይት ነው ግድያውን የፈፀሙት ነገር ግን ሞት ነው የተፈረደባቸው። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ እዚህ ሀገር ሁለት ዓይነት ሕግ እንዳለ የሚያሳይ ነው። አንዱ ለገዥዎች የሚሰራ ሕግ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ለተራው ዜጋ የሚሰራው ሕግ!

 

አንዲት ቀበጥ የድምፅ ወያኔ ጋዜጠኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ስታቀርብ “ጉዳዩ በሕግ ተዘግቶ እያለ እናንተ እንደዚህ ማለታችሁ በዳኝነቱ ሥርዓት ላይ እምነት እንደሌላችሁ አያመላክትም ወይ?” ብላኝ ነበር ባለፈው የፕሬስ መግለጫ በሰጠንበት ጊዜ! የአረጋዊ ጉዳይ ገና ነው። ፍትሕ አላገኘም። እዚህ ሀገር ገለልተኛ የሆነ የዳኝነት ሥርዓት እንደሌለ ምስክር መጥራት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ሕግ ቢኖርማ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን በእስር ቤት ባልተሰቃየች ነበር። ፍትሕ ቢኖርማ አቶ ስየ ታግለው ባፀደቁት ሕገ መንግሥት ላይ በግልፅ የተቀመጠውን ዋስ የማግኘት መብት ተነፍገው ለዓመታት በእስር ባልማቀቁ ነበር። ብዙ ብዙ ሌሎችም ዜጎች በምሳሌ ማምጣት ይቻላል። ስለዚህ የአረጋዊ ጉዳይ ገና ነው። ከአስር ዓመታትም በኋላ ተጠናክሮ የሚቀጥል ትክክለኛ ፍትሕ እስኪገኝ ድረስ የምንታገልለት አጀንዳ ነው እንጂ እንዲሁ በቀላሉ የምንተወው ነገር አይሆንም። አለበዚያማ የሁለቱ ጓደኛሞቹ ታሪክ ነው የምንደግመው።

 

አንድ የትግርኛ ተረት አለ። ሁለት ጓደኛሞች ወደ ሩቅ ሀገር በእግር ሲጓሱ መንገድ ላይ ይመሽባቸውና በአንድ ዛፍ ስር ጎን ለጎን ይተኛሉ። ሌሊት አንደኛው የሆነ ነገር ሲያኝክ ይሰማና ጓደኛውን ይቀሰቅሰዋል፤ “ኧረ የሆነ ድምፅ ይሰማኛል። ፈጥነን እንነሳ” ይለዋል። ያኛው በሽኩሽኩታ “ወንድሜ ዝም በል! እንዳታስጨርሰን! ጅብ እግሬን እየበላኝ ነው።” አለው ይባላል። ከእግር መበላት ወዲያ ዝም ማለት የት አለ! ቢያንስ ለሌላው ምሳሌ በሚሆን መልኩ እየጮሁም፣ እየታገሉም መበላት ይሻላል እንጂ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ