ቃል (ፊልጶስ)
ቃል
ፊልጶስ - ከሆላንድ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ቃልና የቃል ምሥጢር
ይከብዳል አሉ ከሰማይ ከምድር፤
በቃል ነውና “ይሁን!” ተብሎ የሆነ
ሁሉም ፍጡር፣ ሁሉም ነገር የታመነ።
ወይ ጉዴ! ...
የአፍ ወለምታ ልማዴ! ...
”ቃል ቋቅ! ...” ባለበት ዘመን፣ ”ቃል” አልኩ እንዴ?
ለነገሩም ”የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” ላሉት
ይጭነቅ እንጅ ለአበው፣ ቃል የሰው ማንነት-ሕይወት
የኃይማኖት ማተብ-ግማድ አድርገው ላመኑት፤
ለ’ኔ ዘመንም፣ የአፍ ወለምታ ታሽቶ በአፍ ወለምታ
ይቀርባል ”ቃል” ሆኖ ለወዳጅ፣ ልሳን ተከፍቶ ልብ ሳያመነታ።
ተክሊል ካባ ተላብሶ፣ መኮፈሱም ሆነ ‘መምበር’ መጨበጡ
ቱጃርነትም ሆነ ውዳሴ-መዝሙር፣ ዘምሮና ፅፎ-ቦርሾ መደመጡ
”ቃል” ካላበሉ አይታሰብም ሐቅን አንቆ ካልረገጡ።
ታዲያ ምን ከብዶኝ ”ቃል” ማለቴ ...?
ምን ”ኅሊና” አለ በሰውነት አከላቴ ...?
”የተናገሩት ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ልጅ ይጥፋ” እንዳሉት
እንድ ቅድመ-አያት ወገኖቼ እንደአለፉት
”ቃል” የለኝ ”ሐቅ” የሚነገር በአንደበት
”በስጋ” ተወለድኳቸው እንጅ የእነርሱን የመንፈሥ-ምግባር አልወረስኩት።
የዘምኑ ”ቃል ... ቃለ-ቀሊል” ተናጋሪ - ሰሚም አያቅማማም
”እህ! ...” ባይ ጆሮ ጠቢ እንኳ’ በአድባር-በሰፈሩ ቢጠፋም
የገደል ማሚቶ ያስተጋባውን፣ አነብናቢ የወሬ ቋት አያልፈውም።
ይሁን እንጅ ”ቃል” ግን ሕያው ነውና ትውልድ-ዘመን አይሽረው
አነብናቢ - ጆሮ ጠቢ እንጅ ከሳሚና ጠፊው።
የእኔ ብጤውስ አነብናቢ፣ ጆሮ ጠቢ የገደል ማሚቶ
‘ረክሶ - አርክሶ፣ ገምቶ ከሚኖር አግማምቶ፤
ይሻለው ነበር ቢጠፋ በቃሉ
ሞት የኋላ-ኋላ መሆኑ እየታወቀ ”ፍፃሜ - ለኩሉ”
”ቃል”’ ብሎ ... በቃል መኖሩም ሆነ መታመኑ
እንደ ጊዜው ስለሆነ እንደ ትውልድ ዘመኑ፤
በመቅደስ ቤቱ ሳይቀር በመድረክ ተውኔቱ
”ቃል ቋቅ! ...” ባለበት ዘመን ”ቃል” ማለቱ
በ’ርግጥ የራስ እንጅ የሌላ አይደልም መቅሰፍቱ።
- - - - // - - - -
ፊልጶስ - ከሆላንድ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



