እንባ ይብዛበት እንዴ? (ጌታቸው አበራ)
እንባ ይብዛበት እንዴ?
(ለክቡር ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ስንብት)
ጌታቸው አበራ - ሚያዝያ ፪ ሺህ ፩ ዓ.ም. / አፕሪል 2009 (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ለሀገሩ ክብር በእንባ እየታጠበ ፍቅርን ላስተማረ፣
ግብሩ ተከፈለ፣ የሚሊዮኖች እንባ በፍቅር ተቸረ፣
ቃሉን የጠበቀ ላገር ለወገኑ በክብር የፀና፣
እንባ ይብዛበት እንዴ?! የምዕተ-ዓመት ጀግና!
የዝምድናን አዚም የሕይወትን ምስጢር በድምፁ ለውሶ፣
በመለኮት ኃይል ለኢትዮጵያዊ ሁላ ነበር ለካ አጉርሶ?
ጉድ ነው ያልታሰበ በእናት ሀገር ታሪክ ፈጽሞ ያልታየ፣
ተጣብቆት እሚኖር የገዛ አካሉ ሥጋ እንደተለየ ...፣
ሰውነቱ ርዶ መናገር ተስኖት ሁለት ዓይኑን ጨፍኖ፣
በመላ ዓለም ዙሪያ ሐበሻ አለቀሰ ካንጀት ተንሰቅስቆ።
የራዲዮ፣ የቲቪ ... ሪፖርተር ሥራ አጣ ዘገባ አስጨነቀ፣
ጥሌ የጨበጣትን ማይክራፎን ፈርቶ ሁሉ ተሳቀቀ፣
መች ጠፍቶ እሚጠየቅ በስልክ በስቲዲዮ ሰልፉማ ተመመ፣
ስለእርሱ እሚያስረዳ “ባለሙያ ታጣ” እንባ እየቀደመ፣
በሲቃ ታብተው ቃላትም አደሙ፣
ዜና ጋዜጠኞች እንባ አስተረጎሙ!
ባለዝና ሀብቱን ዕነቁ ድምፅ ዕሴቱን
ሳይሰስት ሳይሳሳ ሲለግስ ኖረና፣
በስተመጨረሻ ወለዱን አስቦ በእንባ አስከፈለ እርግፍ አረገና!
ምድርን ሲያንቀጠቅጥ ገኖባት የኖረ የመድረኳን አምባ፣
ከዕይታ ሲሰወር አሻፈረኝ ብሎ ከሥሯ ሲገባ፣
ፍቅር የተራበ ሕይወት ተጠማ ... ቀን ጎደለበት ምነው አያነባ?!
አዛውንት፣ ወጣቱ ... መላ ህዝበ-ኢትዮጵያ
ለመከራው መግቻ ለኀዘኑ መጽናኛ ...
ለደስታው ጡዘት ለፍቅሩ መዝናኛ፣
ከውልደት እስከ ዕድገት የሕይወት መንፈሥ ድምፅ ሲመገብ የኖረው፣
ድምፅ-አልባ ሆነና ታላቁን ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን በእንባ ስንቅ ሸኘው!
ጌታቸው አበራ - ሚያዝያ ፪ ሺህ ፩ ዓ.ም. / አፕሪል 2009 (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)



