“ካፊርስ አንተ ነህ” (ዳዊት ከበደ ወየሳ)
ይሄ የምታዩት፣ ካገሩ የወጣ፣ ኮበላ እና ጉብል፤
ቢሆንበት እንጂ፣ ነገሩ አጓጉል፣ ወጥቶ ‘ሚኮበልል።
ባህሩን በታንኳ፣ በርሃውን በ’ግሩ፣ ምድሩን በመኪና፤
ያልፍልኛል ብሎ፣ ድንበሩን ሲሻገር፣ ሰው አገር ሲያቀና።
መች ጠልቶ አገሩን፣ መች ከድቶ ወገኑን፣ መች ሻረ ማተሙን፤
በክርስትና ስም፣ እንደመዳኒአለም፣ አፈሰሰ ደሙን።
ሁሉም በአምላክ ፊት፣ እኩል የሰው ፍጡር፣ ጥቁር እና ቀዩ፤
ኢትዮጵያዊ እንጂ፣ መጠሪያ ስማቸው፣ በዘር አልተለዩ።
እያሱ እና ባልቻ፣ ከጨርቆስ ተነስተው፣ ሲሄዱ ሊቢያ፤
ዳንኤል ከትግራይ፣ ሌላው ከወለጋ፣ አንደኛው ጉራጌ፣ ሁሉም ከኢትዮጵያ፤
ጀማል እስላም ሆኖ፣ ከክርስቲያኖቹ፣ አትለዩኝ ባለ፤
እስላም ነን በሚሉ፣ ግብረ ሰይጣን ሰዎች፣ አብሮ ተገደለ።
በህይወቱ ሳለ፣ ጎሳ እና ዘር ሳይል፣ ሃይማኖት ሳይለየው፤
በረመዳን አብሮ፣ ፋሲካን አክብሮ፣ ባንድነት የቆየው፤
ሰውም አገር ሄደው፣ አንድ ላይ ሲሞቱ፣ አትለዩን ሲሉ፣
ያስቀናል ሞታቸው፣ ከሞት በላይ ሆነው፣ ሰማዕት ሲባሉ፤
እንደጌታ ክብር፣ ሳይገሉ ሲሞቱ፣ በክርስትና ስም፤
ለቅሷችን ላልሞቱት፣ እንባ ለሌላ እንጂ፣ ለጽድቅ አናለቅስም።
ሃበሻ ደግ ነው፣ ብለው ያሞገሱት፣ ነብዩ መሃመድ ዳግም ቢመለሱ፣
እስላም ነን በሚሉት፣ ግብረ ሰይጣ ሰዎች፣ እንደምን ባዘኑ፣ እንዴት ባለቀሱ።
ሃበሻ ተይዞ፣ ሃይማኖት የሌለው፣ “ካፊር” ተባለና፣ ሞት በሱ ሲፈረድ፤
ከባህር ዳርቻ፣ “አላህ ኩበር” ተብሎ፣ አንገቱ ሲታረድ፤
ክርስቶስ ቢታዘብ፣ ነብያችን ቢያዩ፣ ይህን ክፉ ነገር፤
ላኢላህ አኢለላህ፣ “ካፊርስ አንተ ነህ፣” ብለው ይሉት ነበር።
ካፊርስ አንተ ነህ፣ ሃይማኖት የሌለህ፣ የ’ስላም አረም ተክል፤
ሃበሻን የማትወድ፣ ሌላ ‘ማታከብር፣ እስላም የማትወክል፤
ይሉት ነበር ነቢይ፣ በህይወት ቢኖሩ፣ “ጠብቅ ቃል ኪዳኔን፤
አብሮ የኖረን ህዝብ፣ አበሻን አትንካ፣ አትግደል ወገኔን።”
ጆሆቫ፣ ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ክርስቲያኑ፣ አብሮ ‘ሚኖርባት፤
እግዚአብሄርም ይላል፣ እጃችሁን ዘርጉ፣ ኢትዮጵያን አትንኳት።



