ሣልህ ኦምራን

ዓባይ አመል አለህ ባልክበት አትቆምም

ህዳሴውን ሰምተህ መኩራትህ አይቀርም

የላይ የታች ብለው ሰዎች ቢፋተጉ

አንተ ግድ አይሰጥህ በጦር ቢፋለጉ

ከላይ ጣና መልካህ መፍሰስህ አይቀሬ

ማስገበሩም አይተው የታጠቀው ሡሬ

 

ቢተረትብህም ባማራ በትግሬ ባረቡም ምላስ

ከሄድክ መሄድ ነው አታቅ መመለስ

ሁሉን ታጠጣለህ ድንበር ሳትቀልስ

ፍቃደኛም ሆነህ ገባህ ካዳራሹ ከህዳሴው ዳስ

 

ጤናን የማይጎዳ ውሃ ታጠጣለህ

መስኖ ላመቻቸም ላትክልት ትስማማለህ

ከሌላው አመልክን የለየው ድንበር መቁረጥህ

በየሄድክበት በደረሰክበት ስም እየሰጡህ

 

አሣም አለህ አሉ ሥጋው የጣፈጠ

ቀምሸው ባወራሁ ቀማሹ በለጠ

ብህዳሴም ታጭተህ ኤሌክትሪክ ለመስጠት

በተሰጠህ ጸጋ ልግስናህ ተካበ አካፍለህ ለማብላት

 

ዓባይ ድምጽ ፈጠረክ አሉህ፣ ወሬ ጀመርክ አሉህ

በሚያውቀው ቅላጼ ዓባይ ተናገረ

እየተንዷዷ እየተንጫጫ መዝሙሩን ዘመረ

አዳም ወይ ሰውነት ባወቀ አላማችሁ

ውሃ ዘመድ አይሆን፣ ማ በነገራችሁ

መሬት ዘመድ አይሆን ምነው ባወቃችሁ

ሥትሰሩብን ብቻ ዝምድና አበጃችሁ

ወንዙና ባህሩ ፈለጌን ይከተል

እንደኔ ለሰው ልጅ ቸርነት ይታገል

እንዲህ አለ እያሉህ! ዓባይ ድምጽ ፈጠረክ አሉህ! ወሬ ጀመርክ አሉህ

 

በመንቃትህ ምጥቀት ዓባይ ልብ ገዛህ

ደሞዝ ተቆርጦልህ ከበዛው አባዛህ

የሰጡህን መንገድ መከተል ጀምረህ

የቀዬህን መሬት ማስቆፈር ተስማማህ

 

ነዋይ ሲፈስብህ ሞተር ሲጮህብህ

ያዋቂዎች ስሌት ሂሳብ ሲሠራብህ

አገር የሚመሩ ነገር የሚያረቡ ወሬ ፈላጊዎች

ትካሻቸው ጭነት አይን ያላቸው ሰዎች

ያገር የውጭ አገር ተመራማሪዎች

በያይነት በያይነት አገኘህ ጎብኚዎች

 

የተመራመሩ እውቀቱ ያላቸው

እንዴት አደርክ አሉህ

ምን ሠሩብህ አሉህ

ካንተ ፍሰት ውበት ካጓጓዝህ ክህሎት

ከኃይልህ ኃይል ወስደው

ኤሌክትሪኩን አገናኝተው መቅኔህን አጎልብተው

ለራስም ሊያበሩበት ሊሠሩበት

ለጎረቤት በንዋይ ሊለውጡት

 

ዓባይ ስም አወጣህ ስምህ ተጨመረ

በአለሙ ቋንቋ ላንተ ተነገረ

 

ጥል መሳይ ፈጠሩ ማፍቀርም አወሩ

አንድም መጉዳትህን አንድም መጥቀምህን

የኛ ነውም አሉህ

የሁላችንም ነህ የምንልም አለህ

የፍጥረት ሚስጥር ነህ በቅተህ ታባቃለህ

 

ዓባይ ምን ገዶህ! አንድ ቦታ አትቆምም

ከመነሻህ መጓዝ ከመድረሻህ መድረስ መጓዝህ አይቀርም

ለተፈጠርክለት ላላማህ ጭራሽ አትቦዝንም

 

ውሃማ ለመሆን ያ ወንድሜ ውሃ ነው ቀይ ባህር

ጉዞ የሌለበት መሄድ የሌለበት በቁሙ የሚኖር

ባይሆን አለው አመል መሰርሰር መቆርቆር

አንዳንዴም መደንፋት በማዕበል ማስደንበር

ዘርና ዘመዱን ወገኑን የማይጦር

እንደኔ አትክልት የማይቀበል ዘር

ተሰድጀ ልኑር ብሎ የመረጠን ሳይደርስ የሚያስቀር

ወንድም ከወንድሙ አቆራርጦ የሚኖር

ብለኸዋል አሉ ጨው ተፍቶ የሚያድር

 

ዓባይ ወንድሞችህ አቤት መብዛታቸው

ካንተ አመል የነሱ ለይቶ ያስቀራቸው

በተወለድኩበት ልሙት ላርግ ያለ

ኧረ ወንድም አለህ አዋሽ የተባለ

ያገሬ ልጅ አዋሽ እኔ ልደፋልህ

ጉልበቴ ደካማ መሥረግ አላስተውህ

አሸዋ የዋጠው የመሥረግ ሚስጥሩ

ፍቅር ቢኖረው ነው ለውዲቷ ሀገሩ

በኢትዮጵያዊነቱ ለዘላለም ኩሩ

ብለኸዋል አሉ ባወጋኸው በወግህ አወሩ

 

ዓባይ ድንበር ቆርጠህ መሄድህ ነው ሚስጥር

ለኔ ነው አይሉህ ለኛ ማለት በቀር

አመልህ እውቅ ነው አያሙህ በድንበር

መሄድህ መጓዝህ እያጠጣህ መብረር

ከጊዜ ከሰዓት ካዲስ ፀሐይ ጮራ

ሁልጊዜ መሄድ ነው ማየት አዲስ ጎራ

ህዳሴው የሚባል ይዘሃል ቁም ሥራ

ላመልህ ጭማሪ ከፊት አመል ጋራ

 

ዓባይ አመል አለህ ባልክበት አትቆምም

ህዳሴውን ይዘህ መክበርህ አይቀርም

በዋጋ በተመን አትከራከርም


ሣልህ ኦምራን

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ