ለቅሶ እንድረስ በአበራ ለማአበራ ለማ
(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
ቀብር ውጡ ወዳጆቼ - ጌታ ብዕር አረፈ
ደራሲው ሰው ሆነ - ፈጣሪነቱን ተገፈፈ፤
በመጋኛ ተቦትልኮ - በዘር ሀረግ ተጠርንፎ
ጌታ ብዕር ተሻረ - ካባ ማዕረጉን ተገፎ
የት ይደርሳል ያልነው ጎበዝ - ተስፋ ያልነው ሽል ጨንግፎ፤

 

ቀብር ውጡ ወዳጆቼ - ልባችሁ ባዘን የቆሰለ

ፈጣሪው ሰው ሁኖ - ብጤ ፈጣሪን ከሰለለ፤

የብዕር አምላክ ቢቆጣ - በየቤቱ ቢገነፍል

ዘር ማንዘር ብሎ ነገር - የብዕር ጌታን ሲገድል

ማን ይችላል ወዳጆቼ - ማን ይዳኛል ይህን በደል?

 

ቀብር ውጡ ወዳጆቼ - እግዚኦ ብቻ ነው 'ሚበጀው

ለካስ ብዕርም ይሞታል - ፈጣሪ አምላኩ ሲበድለው

ደራሲ ፈጣሪነቱን ትቶ - የዘር እርሻ ካረገው፤

ቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ - ብዕር ተረታ በሞቱ

ፈጣሪም ሰው ሆነ - ሰው ለሥጋው በማድላቱ፤

 

ቀብር ውጡ ወዳጆቼ - የብዕር ሞት የቆጫቸሁ

የቦለቲካ ሾተላይ - ስልጡን ብዕሩን የነሳችሁ፤

የብሩህ ቀለሙ ጌታ - የጥበብ እስትንፋሱ መገኛ

ወጣቱ መልከ ጸዴቅ - ወዳጄ ልቤው ብዕረኛ፤

ነገሩ ሁሉ ከሆነ - ጌታም ለሥጋው አደላ

ሰውነቱን ማወቅ እንጂ - ፈጣሪነቱማ ተከላ፤

 

የጥሁፋችን መጣምር - የጥበብ ጌጡ ተስፋ

እንዲህ ተመንገድ ቀርቶ - ተጃችን ላይ ታንቀላፋ፤

ለቅሶ እንድረስ ጎበዝ - ዓለም ሲያሳየን ገመና

የብዕር ሞትን እያየን - ለማንም አይበጅ ጽሞና፤

 

አዎን! ... ፈጣሪው ሰው ሆነ - ለሥጋ ሥጋው እያደላ

ብዕር ሥጋ ሆነ - ሰው ሥጋውን እየበላ፤

የዘር ቦለቲካን እንርገም - የተስፋን ብዕር ለማዳን

ከዘር ጥላቻ እንመንጥቀው - ይድን ይሆናልና አንድ ቀን፤

ቀብር እንውጣ ወዳጆቼ - ለብዕር ሞት እናልቅሰው

ጥላቻን እንጥላው -

ደረት መተን፣ ሙሾ ሞሸን እንቅበረው!


አበራ ለማ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ