ሕመምሽ አመመኝ (አስራደው ከፈረንሳይ)
አሥራደው (ከፈረንሳይ)
አንቺን ስከረክም - አንቺኑ ስኳኩሌ፤
ደስታሽን ሳነሳ - ሃዘንሽን ስጥሌ፤
እራብሽ ሲርበኝ፤
ጥማትሽ ሲጠማኝ፤
ሲያምሽ እየታመምኩ፤
ስትድኝ እየዳንኩ፤
አንቺን እያነሳሁ፤
አንቺኑ እያሰላሁ፤
እኔን እኔን ሳሌሆን - አንቺን አንቺን እያልኩ፤
ያባቴን ስም ትቼ - ባ'ቺ ስም እየማልኩ፤
ከሳሁ መነመንኩኝ - ሸክምሽ ከበደኝ፤
ጭንቅሽ አስጨንቆ - ሃዘንሽ ተጫነኝ፤
መከራሽ በርክቶ - ሕመምሽ አመመኝ።
ጉስቁልናሽ በዝቶ፤
ችግርሽ በርክቶ፤
ሰብዕናሽ ተረስቶ - ሃዘንሽ ቅጥ አቶ፤
ሞ - ትሽ አልል አለሽ፤
አ - ለሽ አልል የለሽ፤
አንቺን ሳንቆራጥጥ - ሳነሳ ሳስቀምጥ፤
በመከራሽ ስበግን - በችግርሽ ሳምጥ፤
ከፊትሽ ሳነበው - ጭንቅሽ አስጨንቆኝ፤
መከራሽ በርክቶ - ሕመምሽ አመመኝ።
ሆነና!
ማስፈራሪያ ፊትሽ - መለመኛ ስምሽ፤
አንገትሽ ተራቁቶ - ተቆርጦ ማተብሽ፤
አንድ ሁለት ተብሎ - ሲቆጠር ጎድንሽ፤
አንጀትሽ ተጣብቆ - ሲሟገት ከጀርባሽ፤
የልጅ ያለህ ብለው - ሲያለቅሱ ጡቶችሽ፤
ወቀሰኝ ሕሊና፤
ታዘበኝ ሰብዕና፤
አመመኝ ሕመምሽ፤
ደቆሰኝ ሃዘንሽ፤
በራብሽ ተራብኩኝ - ጥማትሽ አስጠማኝ፤
ካንቺ በመራቄ - ሕሊና ወቀሰኝ፤
መከራሽ በርክቶ - ሕመምሽ አመመኝ።
ሃዘንሽ አስከፋኝ፤
ደስታሽ እራቀኝ፤
ፈገግታሽ ናፈቀኝ፤
መከራሽን ጠላሁ፤
ምቾትሽን ተመኘሁ፤
ጥምሽን ልጠማ - እራብሽን ልራበው፤
ሸክምሽን ልሸከም - ጀርባሽን ይቅለለው፤
ካንቺ በመራቄ - ሕሊና ወቀሰኝ፤
አገሬ ልንገርሽ - ሕመምሽ አመመኝ፤
አገሬ ልንገርሽ - ሕመምሽ አመመኝ፤
አገሬ!
የአገራቸው የኢትዮጵያና የሕዝቧ ጉዳይ ለሚያስጨንቃቸው አገር ወዳድ ወገኖች ሁሉ ማስታወሻ ትሆን ዘንድ የተቋጨች። ሐምሌ 8 ቀን 2005 ዓ.ም. (15/07/2013)
(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)



