ዋለልኝ እግዜር

በጨለማው ዘመን፣ በአስራ ሰባቱ

የሰው ዘር ተዋርዶ፣ በሆነበት ከንቱ

በግፍ የተሞላ፣ ነበር ግርፋቱ።

በዚህ የተነሳም፣ ሽብር በማየሉ

መውጫውን ዘይዷል፣ ሁሉም በየቅሉ።

 

 

አብዛኛው ተይዞ፣ በፍርሃት ቆፈን

ከሁሉ አስበልጦ፣ አድሮ መገኘቱን

ብሶቱን አምቆ፣ አቀርቅሮ አንገቱን

ሊያሳልፍ ሞክሯል፣ ንፋሱን ወጀቡን።

በጣም የባሰበት፣ እጅጉን የሰጋም

ይህንን መከራ፣ ያለ አላይ አልሰማም

በቅታው ይቺ ዓለም፣ ገብቷል ወደ ገዳም።

 

የደነበረውም ሜዳውን አቋርጦ፣ ተራራውን ወጥቶ

ቁልቁለቱን ወርዶ፣ ወንዙንም ተሻግሮ

ፊቱንም ሳያዞር፣ ሳያሰማ ሮሮ

ኮብልሏል ከአገር፣ እልም ብሎ ጠፍቶ።

 

ብርታቱን ያገኘው፣ አሰምቶ ፉከራ

እያለ ወደፊት፣ ፋኖ ተሰማራ

ሊባጀን በደሙ፣ ከሳት ከመከራ

ውሃ አንጠልጥሎ፣ ባንዲት ትንሽ ኮዳ

ብረቱን አንግቦ፣ ወ’ቷል ወደ ሜዳ።

 

ጥቂት የማይባል ምውት፣ ለስጋው የራራ

የገዛ ወገኑን፣ አ’ርጎ ባላጋራ

በፍጹም ዘንግቶት፣ እራሱ መሆኑን ነገ ባለተራ

ባንድ አልጋ ተኝቷል፣ ከጨቋኞች ጋራ።

….. // …..

ጊዜው ደረሰና፣ የግፍ ዋንጫ ሞልቶ

ከውስጥም ከውጭም፣ ተንጦ ተገፍቶ

ይመስል የነበረው፣ የተሳሰረ ድር

ሆኖ የእምቧይ ካብ፣ የድቡሽት ላይ ክምር

ሲወድቅ ሥርዓቱ፣ ላይገኝ ቅሪቱ

መድረሻው ጠፍቷቸው፣ ደቀመዛሙርቱ

እንደ ጉም በነኑ፣ ጠፉ ተበተኑ

አይደለንም ብለው፣ ከዱ በጭፍኑ።

…..//…..

ወንበር የነጠቁት፣ አዲሶቹ አንጋቾች

ስንጠብቃቸው ይሆናሉ ብለን፣ መድህን ቤዛዎች

ሳይውሉ ሳያድሩ፣ ገልጠው አሳወቁን

ጽንሰ መሠረቱ መተዳደሪያቸው፣ ከአራዊት መሆኑን።

ከፋፍለው ሊገዙን፣ በዘውግም ከለሉን

ከላይ ከመለኮት የተቀበልነውን፣ በኃይልም ገፈፉን ነጻነታችንን

ሊያስረሱን አስበው፣ ሰው መሆናችንን።

….. // …..

መቅተል የለመዱ፣ ሰውን ማንገላታት

መግረፊያው ልምጩ፣ ያለፈው ሥርዓት

ተቆራርጦ ሲወድቅ፣ በአንክሮት ስላዩት

ቆርጠው ተነስተዋል፣ ብለው ጥጃ ጨንገር

ልጡ አለንጋ’ሚሆን፣ እንጨቱ ሲሰበር

በዚህ የተገኘ፣ አቤት ያለ አሳር

ያደማል አለንጋው፣ የእንጨቱን ሰንበር።

እንዲያው በደፈናው፣ ማለቱ ይቀላል

ግፍና መከራው፣ ከሯል ተባብሷል

ሦስት ትውልድ ባንደ’ዜ፣ ማስለቀሱን ይዟል።

….. // …..

ምን ያመጣ ይሆን፣ መጻኢ ዕድላችን

ሲሆን የኛ ነገር፣ እንዲያው ቁጭ ብሎ መናፍቅ ያለፈን

ከማንሳት ቀንበሩን፣ በግድ በላያችን የተጫነብንን።

ዋለልኝ እግዜር

ኅዳር 24 ቀን 2005 ዓ.ም. - ዋሺንግቶን ዲ.ሲ.

ማስታወሻ በ1983 ዓ.ም. ከአንድ አርሶ አደር ጋር፣ በጊዜው ስለተከሰተው ለውጥ፣ አንስተን ስንጨዋወት የነገረኝን በማስታወስ የከተብኩት ነው። “የአለፈው መንግሥት የሚገርፈን በልምጭ ነበር፤ የአሁኑ ግን በጥጃ ጨንገር ሆኗል” ነበር ያሉኝ፤ የሥርዓቱን ማንነት በቅፅበት ጀንበር የተረዳ፣ የአንዲት ትንሽ መንደር ቀለም ያልቀመሰ አርሶ አደር። “ልምጭ ሲገርፉበት እየተቆረጠ ያልቃል፤ የጥጃ ጨንገር ግን የውስጡ እንጨት ሲሰበር ልጡ አለንጋ ስለሚሆን፣ ግርፋቱም ይረዝማል፣ ጉዳቱና ሕመሙም እየበረታ ይሄዳል” በማለት ነበር የቋጠሮውን ፍቺ የጠቆመኝ። እንዲህ አይነት መረዳት ምንኛ መታደል ነው!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ