ጀግና ውለጅ እባክሽ (አስራደው)
ጀግና ውለጅ እባክሽ
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
የምሑር መሃይም ተባይ አላዋቂ፤
የመሃይም ኩፍስ አስመሳይ አዋቂ፤
ያንበሳ ልክስክስ ልፋጭ የሚያላምጥ፤
የጅብ ባለጊዜ ታፋ መራጭ ከሽንጥ፤
የቁራ ዕርግብ መሳይ ሠላምን አብሳሪ፤
የፈረስ አዝጋሚ የግመል ስጋሪ፤
ፍርደ ገምድል ዳኛ ፈራጅ በቂም በቀል፤
ንጹሕ ሰው ታሳሪ በፈጠራ ወንጀል፤
የባዕድ ባለቤት የነባር ባይተዋር፤
ሥልጡን ሥራ ፈቶ ሞያ ቢስ ሲገብር፤
ልማድ ሆኖ ቀረ አቀርቅሮ መኖር፤
በተወለድንበት በጦቢያ ምድር።
ያቀረቀረ ራስ ቀና እንዲል ካንገቱ፤
ተመልሶ እንዲከብር የሰው ሰውነቱ፤
በፈጠራ ወንጀል ዜጋ ሳይከሰስ፤
ሰብዕና ተንዶ ፍትህ ሳይገሰስ
ለባዕድ ተሸጦ ሳይሟጠጥ ምድርሽ፤
ሳይሰጉ እንዲኖሩ ተባብረው ልጆችሽ፤
በሠላም በፍቅር ባንድ ላይ በምድርሽ፤
ከወደቅሽበት ማጥ ካዘቅት እንዲያወጣሽ፤
ጥላሸት የነካው እንዲታደስ ክብርሽ፤
እንደ ቴዎድሮስ እንደ ቋራው ልጅሽ፤
ያንድነት ምልክት ሠንደቅ እንዲያለብስሽ፤
እምዬ ጦብያ ጀግና ውለጅ እባክሽ!!
እምዬ ጦብያ ጀግና ውለጅ እባክሽ!!
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለአንድነትና ለሠላም ለቆሙ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ትሁንልኝ።
አንድ ቀን



