ሕሊና (አውራሪስ ጥላሁን ውቤ)
ሕሊና
(አውራሪስ ጥላሁን ውቤ)
የተማርኩ መስልኝ ለጤና ያደላሁ
አታክሌ ስመገብ ጥሬ እየቀላቀልሁ።
ለዚህ ለከርሳሙ ለስግብግብ ሆዴ፥
ላይ እታች ማለቴ ብሶ ማጎብደዴ።
ለውስኑ ዕድሜዬ ያለ ቅጥ ሥጓጓ፥
ሞትን ችላ ብዬ ለችግር ስሰጋ፥
የራሴን ይሉኝታ እያሳጣሁ ዋጋ፥
እውነቱን ሲነግረኝ እኔ በር ስዘጋ።
አንድ ቀን ሳይታክት ህሊና ሲወቅሰኝ፥
ነጋ ጠባ ሳይል ሁሌ ሲያስታውሰኝ።
ለማን እንደምኖር ምን እንደምሠራ፥
ዓይኔ ምን እንደሚያይ ልቤ አውቆ እንዲራራ።
ሰው መባሌን ሳይሆን ሰው መሆኔን እንዳውቅ
እረፍቴን ሲነሳኝ ተጨንቆ ሲያስጨንቅ።
ይህ የውጭ አካሌ ገዝፎ የሚታየው
በጉራ በትዕቢት ዓለም የሚቀጨው
በረባ ባልረባ ገንዘብ የሚረጨው
መታየትን እንጂ ማየት የተሳነው።
ሰው ያለ ሕሊናው ሰው ሳይሆን ከብት ነው
ሕሊናውን ካጣ የሰው ልጅ ባዶ ነው።
አውራሪስ ጥላሁን ውቤ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



