“መተካካት” (አስራት አብርሃም)
“መተካካት”
አስራት አብርሃም
ፈረሰኛ
ፈረሰኛ
“ድሮ ቀረ”
አንበል እኛ፤
ዛሬም አለ
ፈረሰኛ!
በአባ ዳኘው
በአባ መላ፤
ተተክቶ
ተተክቶ
አባ ምታው
አባ ዱላ።
ፈረሰኛ
ፈረሰኛ
“ድሮ ቀረ”
አንበል እኛ፤
ዛሬም አለ
ፈረሰኛ!
በአባ ታጠቅ
በአባ ጠቅልል፤
ተተክቶ
ተተክቶ
አባ ቁረጥ
አባ ገንጥል።
ፈረሰኛ
ፈረሰኛ
“ድሮ ቀረ”
አንበል እኛ፤
ዛሬም አለ
ፈረሰኛ!
በዮሐንስ
በአሉላ
በአባ በዝብዝ
በአባ ነጋ፤
ተተክቶ
ተተክቶ
ግራኝኛ
የሚያወጋ፤
አባ በትን
አባ ቀጋ።
ፈረሰኛ
ፈረሰኛ
“ድሮ ቀረ”
አንበል እኛ፤
ዛሬም አለ
ፈረሰኛ!
የሚዘምር
ሳህልኛ
የሚጋልብ
ትሮይኛ!!
አስራት አብርሃም



