ጥላ - ሁን (በአርቲስት ሰርካለም ተፈሪ)
ጥላ - ሁን (በአርቲስት ሰርካለም ተፈሪ)
ተስገበገብን መሰለኝ መለየትህ አጓጓን
ምን ታደርገው
ያንተን ህመም ያንተን ሲቃ እኛ አልታመምን።
ስራህ ብኩን ሳይሆን እንቶ ፈንቶ
ስምህ ገኖ ፍሬህ በዝቶ።
በልዮ ገጽ ፈገግታ ነጸብራቅ፣
የዘፈንን ምስጢር ሀያልነት፣
የጠነከረን ልብ መሰልጠቁ
ማራራቱ ነበር ማርበድበዱ፣
ማጠንከሩ ነበር ማዋደዱ።
ከሁሉ ልብ ስትገባ ስትጫጭር፣
ስታዝናና፣ ስታነባ፣ ስታስቅ።
በለሆሳስ ስታዜም፤ ስትናገር፣
እድሜ አይል፤ ትንሽ ትልቅ፤
ከሁሉ ልብ ሲንቆረቆር።
የጥበቡን ጥበብ አየሁ ባልተ፣
የፍቅርን ሀያልነት፣
ለነፍስህ ነፍስ ስትዘራ፤
ስትል የህይወቴ ህይወት፣
የዛሬውስ ፍቅር አንጀቴን አራሰው፣
ይገርማል ይደንቃል አወይ ሰውና ሰው፤
አወይ ሰውና ሰው ስትል፣
ከሁሉ ልብ ገብተህ ባ’ሳብ፣
የተወጠረን ስታረግብ፤
ስትመስጥ ስታባንን፣
አረ አንተስ ኑር ህያው ሁን።
ተስገበገብን መሰለኝ፤ መለየትህ ጎዳን፣
ምን ታደርገው ያንተን ህመም እኛ አልታመምን።
እንዲያው ዜማ፣ ምክር ተግሳጽህ፣
ነበር ሞገስ ጥላነቱ፤
ብናዝን አብረን አልሄድን ጎዳን እንጂ መለየቱ።
አዎ ሩጫህን ጨረስክ አንተ የጥበብ ጀግና
ያገር ቅርስ ባለሟል ባለ አደራ፣
አንተ የጥበብ ሰንደቅ ጎተራ።
ዳግም ወገን ላንተ ሊሮጥ፣
ግን ዘገየ ላይመልስህ ላያስመልጥ፤
ከሞት መንጋጋ ሊፈነቅል፣
ምን ታደርገው የወደደ ጅል እማይደል።
ጥላሁን ዳግም ባትናገር ባታዜም፣
ትንሽ ብትጀግን ጥሩ ነበር እድሜህ ቢረዝም፣
አዎ ሩጫህን ጨረስክ።
(ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም በሞት ለተለየን ድንቅ የጥበብ ሰው ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ 1ኛ አመት መታሰቢያ)



