ምኑን ፍቅር ሆነ?!

አስራደው - ከፈረንሣይ

ካላንከተከተ ካንጀት ካላሳቀ፤

በንባ ካላጠበ በላብ ካልጠመቀ፤

ካላጮማጮመ ካላከሳከሰ፤

ካላነባበረ ስሜት ካላኮሰ፤

ስጋን ምቾት ነስቶ ካላርገፈገፈ፤

አጥንት አንቀጫቅጮ ካላንዘፈዘፈ፤

ሰውነት አግሎ ስሜት ካላፈላ፤

በፍቅር ረመጥ ካልማገደ ገላ፤

ካላምቦገቦገ ባይምሮ ፍላጎት፤

በልብ ካረጨ የወንድነት (የሴትነት) ስሜት፤

የፍቅር አውታታ ጅላጅል ከሆነ፤

ምኑን ተፈቀረ?! ምኑን ፍቅር ሆነ?!

 

እንቅልፍ አሳጥቶ ካላንጎራደደ፤

ምግብ አስጠልቶ በራብ ካላረደ፤

ትንፋሽ አሳጥቶ ደምስር ካልወጠረ፤

ካላፈታተገ ብልጭታ ካልጫረ፤

ካላስፈነደቀ ጮቤ ካላስመታ፤

በደስታ ስቃይ በስቃይ ደስታ፤

አይምሮን መርምሮ፤

አንጀት አሳርሮ፤

በሃሳብ ካልናጠ፤

በቁጭት ካላጠ፤

ምኑን ተፈቀረ?! ምኑን ፍቅር ሆነ?!

የፍቅር አውታታ ጅላጅል ከሆነ።

 

እያቁነጠነጠ እያቅበጠበጠ፤

ፀጉር ካላስነጨ ጨጓራ ካላጠ፤

ትንፋሽ እጥር እጥር፤

ልብን እንቡር እንቡር፤

እግር ፈጠን ፈጠን አርጎ ካላስሮጠ፤

ምቾት አሳጥቶ ካላንቆራጠጠ፤

ልብ ካልሸረሸረ ናላ ካላዞረ፤

ደም ስር አሳብጦ ስሜት ካልነዘረ፤

ክሩ ካላለፈ በመርፌ ቀዳዳ፤

ጠበል ካልተረጨ ፍቅር ካልተቀዳ፤

በረመጥ ካልፈጀ አንድዶ በጋራ፤

ወገብ ካልፈተሸ ካልነቀረ አራራ፤

በምኞት አጉኖ (ለግቶ) በማግኘት ካልካሰ፤

በስጋ ፈትኖ በነብስ ካልፈወሰ፤

የፍቅር አውታታ ጅላጅል ከሆነ፤

ምኑን ተፈቀረ?! ምኑን ፍቅር ሆነ?!


አስራደው - ከፈረንሣይ

የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. (Feb. 23//2010)

(በፍቅር መንደርደር ጎራ ብለው የፍቅር ጭስ ላጨሱ ሁሉ ማስታወሻ።)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ