ሐይቲ (ጌታቸው አበራ)
ሐይቲ
ጌታቸው አበራ (ጥር 2002 ዓ.ም. / ጃንዋሪ 2010)
ጠዋት ፀሐይ ወጥታ፣
ብርሃን ተሞልታ፤
ቀዬው ደጁ ደምቆ፣
ሕይወትን ሰንቆ …፤
የፊቱን አሻግሮ …፣
ርዕዩን ቀምሮ፣
“ነገም ሌላ ቀን ነው” ብሎ ሳያበቃ፣
ዛሬ “ሌላ” ሆነበት ተፈፀመ፤ በቃ!
ሲሯሯጥ ገሚሱ፣
ለዚያች የዕለት ጉርሱ፤
ልጁን ስሞ ወጥቶ፣
ሥራ ተሰማርቶ …፤
ላይመለስ ከቶ …፤
ቤተሰብ ተቀምጦ፣
ጠረጴዛ ሞልቶ፣
ራት እየተበላ፣
ጣሪያ ተደፋበት …
የሰው ልጅ ተከላ።
ማን አሰበውና
ይህንን ፈተና፤
በሕመም በስቃይ …፣
በረሃብ በጠኔ …፣
ፍርስራሽ ተጭኖት፣
ሣምንት … አሳለፈ …
የሰው ልጅ በመዐት።
አገር አማን አድሮ፣
አገር ሠላም ውሎ፣
ሳይታሰብ ድንገት፣
ባንዴ ከመ-ቅጽበት፣
እንዲህ … ሆኖ ቀረ የሐይቲ ዕጣ፣
ተፈጥሮ ሲቆጣ።
ጌታቸው አበራ
ጥር 2002 ዓ.ም.
(ጃንዋሪ 2010)
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሜቶ፣ በቅርቡ በድረ-ገጾች ላይ ባሰራጨው የዕርዳታ ጥሪ ጽሑፍ ላይ “ሐይቲያውያን በችግራችን ጊዜ (1934 እ.ኤ.አ.) ከጎናችን ቆመው ነበር፤ እኛስ አሁን በችግራቸው ጊዜ ልንደርስላቸው አይገባምን?” እንዳለው ሁሉ፤ እምንችል በቀይ መስቀልም፣ በዩኒሴፍም፣ … በኩል የእርዳታ እጃችንን ዘርግተን ከሰቆቃው የቲቪ ምስል ዕይታ በኋላ፣ ሠላማዊ እንቅልፍ ተኝተን ለማደር እንሞክር።



