እንኳን ደስ አለዎት አቶ መለስ (ፍሬሠላም አዱኛ)
እንኳን ደስ አለዎት አቶ መለስ
ፍሬሠላም አዱኛ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጨቅላ ሕፃን የታቀፈች፤ በጠኔ የደረቀ
ለማልቀስ አቅም የከዳት፤ ሰውነቷ የደቀቀ
ኢትዮጵያዊት እናት አየሁ፤ ከሞት ጋር የተፋጠጠች የተስፋ ስንቋ ያለቀ።
ከፊት ለፊቱ እያየ፤ የወደቁ እንስሳቱን
አጥንታቸው ቆዳቸውን፤ የደበቀው ሕፃናቱን
አየሁት ያገሬን አባት፤ በሰመመን ሲያወራ
ዝንቦቹን እሽ ለማለት፤ ጉልበት ያጣ አባወራ።
እንባማ ዛሬ ከየት ይመጣል?
ለካስ በእንባም ለመደለል፤ መከራ ለከትን ይሻል
ምናልባት በደህናው ጊዜ፤ የደም እንባ አልቅሰዋል።
እረ ወገኔ!
ወገንህን እኮ ችጋር ፈጀው፤ በረሃብ አለንጋ ተቀጣ
ፈጣሪም ፊቱን አዞረ፤ የመሪዎቻችን ግፍ ቅጥ አጣ
ኧረ ምን እየሆንን ነው፤ ከዚህ በላይ ምንስ ይምጣ?
ጦም ውሎ ማደሩንማ፤ ከተሜውስ ከማን ያንሳል
በልቶ መዋል ቢያዳግተው፤ ጥጋበኞች አይቶ ይውላል
ቀን የገጠመ ዕለትም፤ ሽሮ ማጣፈጫ አጥንት ከጎረቤቱ ይዋሳል።
ለማንኛውም አቶ መለስ፤ ምስጋናዬ ይድረሰዎ!
በቀን ሦስቴ እንደሚበላ፤ ቃል የገቡለት ህዝብዎ
በሦስት ቀን አንዴም አልቻለ፤ እርሶዎን እንኩዋን ደስ አለዎ!
በሁለት ዲጂት ያደገውም፤ የመጠቀው ኢኮኖሚ
ይኸው እዚህ አድርሶናል፤ እንኳን ደስስስ … አሎት በድጋሚ።
በርግጥ በርሶ ዘመን፤ ከቀደሙት ሲወዳደር
10 ሚሊዮን ብቻ ነው፤ የተራበው ወገን ቁጥር
ደስታዎ እንዳይደበዝዝ፤ በፍፁም የለውም ወደር።
ፈረንጆቹም ተሳስተው እጃቸውን ከዘረጉ፤ በደንብ አርገው ያስረዱልን
ርስዎ የሚመሯት ሀገር፤ የጥጋብ ሀገር መሆኗን
ህዝቦን የመመገብ ግን፤ የነርሱ ድርሻ መሆኑን
እርጥባን ከመብት ቆጥሮ፤ ለጋሾችን ማስፈራራት
ሰምተን አናውቅም ለሚሉቱ፤ የለማኝ ሉዓላዊነት
ጆሮዎን ዳባ አልብሰው፤ ልመናዎትን ይግፉበት
እርዳታውም በደንብ ይግባ፤ ካድሬዎችዎም ይምቧቹበት
ደስታዎ ኀዘናችን ነው፤ እርሶን እንኳን ደስ አለዎት!!!
ፍሬሠላም አዱኛ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



