በማትያስ ከተማ

EMDGB Stockholmደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሃንስ (ገሞራው) እና ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ገጣሚ አበራ ለማ ተገኝተዋል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 24 ቀን 2002 ዓ.ም. December 3, 2009)፦ ከሁለት ዓመት በፊት በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሙዚቃና ድራማ ቡድን ቅዳሜ ኖቬምበር 28 ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት 6 ሰዓት ድረስ የቆየ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ ዝግጅት አቀረበ። በዝግጅቱ ላይ ደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉገብረዮሐንስ (ገሞራው) እና ደራሲ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ተገኝተዋል።

 

የዚህ የሙዚቃ ዝግጅት አባላት የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በኖታ ስልት ያጠኑ የመጀመሪያ ተመራቂዎች ሲሆኑ፣ ይህ አይነቱ ጥናት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አዲስ አይነት ጅምር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

 

ይህንን የሙዚቃ እና የድራማ ቡድን የመሰረቱት አቶ ዘነበ በቀለ ናቸው። አቶ ዘነበ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በፕሮፌሠር አሸናፊ ከበደ መምህርነት የሙዚቃ ትምህርት ተምረው ከተመረቁት ጥቂት ተማሪዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን ወ/ሪት መስከረም አየለ በዝግጅቱ ላይ አስረድታለች።

 

ወ/ሪት መስከረም ጨምራ እንደገለፀችው አቶ ዘነበ በቀለ ከኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ መምህርነት በተጨማሪ የሙዚቃ ትምህርታቸውን ለማሻሻል በሶቭየት ሕብረት የአራት ዓመት የትምህርት ቆይታ አድርገዋል። በርካታ የሙዚቃ መማሪያንና ማስተማርያ መጻሕፍት የጻፉና ከዘጠና አንድ በላይ ኢንስትሩሜንታል ፒስስ ኖታዎች የሠሩ ናቸው።

 

አቶ ዘነበ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ይህ የኢትዮጵያ ሙዚቃና ድራማ ቡድን በዚህ የሁለት ዓመት ቆይታው የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በኖታ ስልት ሊጫወቱ የቻሉ ባለሙያዎችን እንዳፈራ አስታውቀዋል።

 

ስለዚህም ሲያስረዱ የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሣሪያዎች እስካሁን ድረስ በልምድ ስንጫወትባቸው እንደቆየን ገልጸው፤ አሁን የታየው ውጤት አኩሪና ለባህላዊ ሙዚቃችንም ዕድገት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ አስረድተዋል።

 

አቶ ዘነበ በማከልም እጅግ አስቸጋሪ ጊዜና ትዕግሥትን የሚጠይቀውን ይሄን ጥናት የወሰዱትን ተማሪዎች አድንቀው፤ በትምህርቱ ወቅት የታዩትንም ችግሮች አብራርተውዋል። ሆኖም የኅብረተሰቡ ድጋፍ ከታከለበት ተጨማሪ ባለሙያዎች ማሠልጠንና አኩሪ ውጤትም ለመጨበጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

 

ከእሳቸው ንግግር በመቀጠል ሙዚቀኞቹ በግልና በሕብረት በባህላዊ መሣሪያ የተቀነባበሩ ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን አሰምተዋል። በዚሁ የመጀመሪያ ክፍል የሙዚቃ ዝግጀት ማጠናቀቂያ ላይ ተደናቂዋ ገጣሚ መስከረም አየለ ”የሙዚቃው ንጉሥ” በሚል ርዕስ ስለአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ የተገጠም ግጥም ስታቀርብ፤ ድምጻዊ ዣን ስዩም ሄኖክ ከሙዚቃው ዝግጅት በተጨማሪ ያዘጋጀውን ግጥም አንብቧል።

 

በመቀጠልም በክፍል ሁለት መግቢያ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው ከኖርዌይ በመምጣት በቦታው የተገኙት ደራሲ አበራ ለማ ነበሩ። ”ግጥም ምንድነው?” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ ”እውነትም እኛ ልዩዎች ነን” የሚል ግጥም አቅርበዋል።

 

ደራሲ አበራ ”ግጥም ምንድንነው?” በሚለው ገለጻቸው፤ ግጥም እንዴት ይገጠማል ምን አይነትስ የአገጣጠም ስልቶች አሉ ከሚል በመነሳት የብዙ ገጣሚያንን ግጥሞች እንደምሳሌ እየጠቀሱ አዳማጩን ባረካና ባስደሰተ ሁንኔታ ትምህርታዊ ገለጻ ሰጥተዋል። በግጥማቸውም ታዲሚውን በመደነቅ ተመስጦ እንዲቆይ አድርገዋል። ”ደፋሩ ጋዜጠኛ” በመባል የሚታወቁት አበራ ለማ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሊቀመንበር በመሆን ከማገልገላቸውም በላይ የአዕምሮ መጽሔትና ጋዜጣ አዘጋጅም ነበሩ።

 

ሌላው ስማቸውን ሲያስጠራና ሲታውስላቸው የሚኖረው ደግሞ ታላቁን ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን የኖርዌጅያን የደራሲያን ማኅበር ያዘጋጀውን በነፃ ሃሳብን የመግለጽ መብት (ፍሪደም ኦፍ ስፒች አዋርድ) ሽልማት እንዲያገኙ ማብቃታቸው መሆኑን ከወሪ/ት መስከረም መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

 

ደራሲ አበራ ለማ ባሁኑ ወቅት ነዋሪነታቸው በኖርዌይ ሲሆን፣ የኖርዌጂያን ደራሲያን ማኅበር የፈጠራ ስነጽሑፍ እና የኢ-ልቦለድ ደራሲያን አባል እንዲሁም የኖርዌጅያን ፔን አባልና የስለጽሑፍ ማዕከል አባልም ናቸው።

 

ደራሲ አበራ ካቀረቡት ግጥም በመቀጠል የሙዚቃ ተጫዋቾቹ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎችን በሕብረት አሰምተዋል። በማያያዝም ለዚሁ ዝግጅት በእንግድነት ከእንግሊዝ በመምጣት በቦታው የተገኘችው ፍሬሕይወት አዲስ ተጋብዛ ወደመድረክ በመቅረብ ያላትን ሃሳብ ገልጻ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅንን ግጥም አንብባለች።

 

የክፍል ሦስት የሙዚቃ ዝግጅት መነሻ ሆኖ የቀረበው የደራሲ የባለቅኔና የገጣሚ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ሥራ የሆነውና ”በረከተ መርገም” የተባለው ግጥም ነው። ”በረከተ መርገም” በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ከአርባ ሁለት ዓመት በፊት የግጥም ውድድር በተደረገበት ጊዜ ቀርቦ አሸናፊነት ያገኘ ነው።

 

በዛን ወቅት በረከተ መርገም ሲነበብ በቦታው ላይ ተገኝተው የነበረውን ሁኔታ የገለጹ እማኝ የጻፉት ጽሑፍ በአቶ ፋሲል በቀለ ቀርቧል። ገሞራውን አገኘሁት የሚል ደራሲውን የሚገልጽ ግጥምም የተነበበ ሲሆን፣ መስከረም ደራሲውንና በረከተ መርገምን አስተሳስራ ያቀረበችው ጽሑፍና ግጥምም ተደምጧል።

 

በመጨረሻም ስመ ገናናው ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ የተሰማቸውን ስሜትና ስለበረገተ መርገም ማብራሪያ ሰጥተው የሙዚቃ ዝግጅቱ ቀጥሏል።

 

በዚህ የሙዚቃ ዝግጀት ኢትዮኦፕሬታን ይዘው የቀረቡት አቶ ንጉሡ ታምራት ለየት ባለ የዘፈን ሥራውና በዘለሰኛ ጨዋታው የሚታወቀውና ጉድ በተባለው አልበሙ ዝናን ያተረፈው ዣን ስዩም ሄኖክ እና ቆየት ባሉ ዜማዎች በመታገዝ የራሱን ግጥሞች አክሎ የተጫወተው ደረጀ በድምፅ ባቀረቡት ጨዋታ ተመልካቹን አስደስተዋል።

 

ይሄንን የኢትዮጵያን ባህላዊ መሣሪያ በኖታ ስልት አጥንተው ህዝቡን ሲያዝናኑት ያመሹት ደረጀ ሰሙንጉሥ፣ ፋሲል ማርሸት እና ሰብለ ሲሆኑ፤ በዚህ በአይነቱ አዲስ በሆነ ሥልጠና አኩሪ ውጤት ያስመዘግውቡና ለውጤት የበቁ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ታውቋል።

 

ከትውልድ ወደ ትውልድ በተላለፉ ቁጥር እንደቆየ የወይን ጠጅ ተውዳጅነታቸውና ተደናቂነታቸው እየጨመረ የሚሄደው የፕሮፌሠር አሸናፊ ከበደ ”እረኛው ባለዋሽንት” የተባለው የሙዚቃ ቅንብር እና የባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ”በረከተ መርገም” በአንድ መድረክ ሊገኙ መቻላቸው ሌላው አስደሣች ሁኔታ ነበር።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ