ግርማ ጌታቸው ካሳ

ኢሕአዴግን እንደ አንድ የሚመለከቱ፣ ሁሉን አባላቶቹን በጅምላ የሚፈርጁ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ኢሕአዴግ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች አሉ። አንዱ የገነባውን አንዱ ያፈርሳል። አንዱ ሲያነሳ አንዱ ይጥላል። አንዱ ሰላማዊ ሰልፍ ሲፈቅድ፣ አንዱ በጎን የዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ይጋፋል። አንዱ የታሰሩ የሕሊና እስረኖች እንዲፈቱ ሲፈልግ፣ ሌላው "እዚያው ቃሊቲ ይበስብሱ" ይላል። አንዱ በጎና ቀና ሕሊና ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ የጠመመና የጫካ አስተሳሰብ ያለው ሆኖ ይገኛል።

 

በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ተቃርኖ ሰሞኑን በጉልህ ለማየት ችያለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ግፍ ለመቃወም፣ በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ኤምባሲ ያመራሉ። ወዲያው የደህንነት ሰራተኞች ባዙቃቸውን እና ዱላቸውን ይዘው፣ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ይልቅ፣ ሰልፈኞችን መደብደብ ጀመሩ። ብዙዎች ታሰሩ።

ሰልፉ፣ የደህንነት ሰራተኞችና ፖሊሶች ሳይቀሩ ሊቀላቀሉት የሚገባ ሰልፍ ነበር። በሰልፉ የተነሳው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ያዋረደ ጉዳይ ነው። ነገር ግን፣ የዜጎቻችን መብት ተረግጦ በሳዑዲ የተፈጸመውን ድብደባ ለመቃወም፣ በአገሩ የወጣው ሕዝባችን ተደብድቦ ተመለሰ።

በዚህ ጉዳይ ላይ፣ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ቃለ አቀባይ፣ አቶ ሽመለስ ከማል፣ አስተያየት ሰጥተውበታል። "ሰላማዊ ሰልፉ ሕገ-ወጥ ነው። ፍቃድ አልተሰጣቸውም። በኢትዮጵያዊያን መካከል ፀረ-ዐረብ ስሜት (anti-Arab sentiments) እንዲኖር ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ስለዚህ ፖሊስ እርምጃ ወስዷል" ነበር ያሉት።(1)

አቶ ሽመልስ እንዲህ ማለታቸውን ከአልጀዚራ ዘገባ ሳነብ፣ ልክ ወላፈን በፊቴ ያለፈ ይመስል በጣም ደነገጥኩኝ። ለማመን አልቻልኩም። ደቂቃዎች እያለፉ፣ ፍም ላይ እንደተጣደ ምጣድ፣ ውስጤ መንደድ ጀመረ። የኢትዮጵያውያን ስሜት ተጎድቶ ባለበት ወቅት፣ ቆስለን ባለንበት ወቅት፣ ግፍ ለፈጸሙብን ዐረቦች ስሜት የምንቆረቆርበት ጊዜ ነውን? ይህ አይነቱ የኢትዮያውያንን ስሜት ክፉኛ የሚጎዳ አስተያየት ከአንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል፣ ያውም የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ይጠበቃልን? በእውኑ እንዲህ አይነት፣ ለሕዝብ ስሜትና ክብር ፍጹም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ናቸውን የሚገዙን?

"በቂ የጥበቃ ኃይል እንዲኖር ዝግጅት ስላላደረግን፣ ሕዝቡም በንዴት ውስጥ ስለሆነ፣ የሳዑዲ ኤምባሲን የማቃጠል ተግባር ሊፈጸም ይችላል" የሚል ስጋት ኖሯቸው ሊሆን ይችላል፣ ሰልፉን በኃይል ያስቆሙት። ነገር ግን አንድ የዘነጉት ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ሕዝብ መሆኑን ነው። ላለፉት 5 ወራት በተለያዩ የአገራችን ግዛቶች በርካታ ሰልፎች መደረጋቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ። አንድም ድንጋይ አልተወረወረም። አንዲትም ንብረት አልጠፋችም። እንደውም በደሴ ሰልፈኞቹ ለፖሊስ አበባ ያድሉ ነበር። በርግጥ ሕዝባችን የተከበረ፣ የሚያኮራ፣ ጨዋ ህዝብ ነው።

አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ለማድረግ፣ በሕጉ መሰረት ባለሥስልጣናት ቢያሳውቁም፣ አሁንም ሕገ መንግሥቱ ተንዶ፣ ሰልፍ ማድረግ እንደማይችሉ ነው በደብዳቤ የተነገራቸው። እንኳን ሌሎች ድርጅቶች ሰልፍ ሲጠሩ መከልከል ቀርቶ፣ በዚህ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ፣ እራሱ ኢሕአዴግ ሰልፍ መጥራት ነበረበት። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሰይፉ ኃይሉ፣ በቅርቡ በለቀቁት ጽሁፍ "why not the government has arranged even public demonstration at least in our major cities to condemn the event and send message to the world?" ሲሉ ነበር የጠየቁት።(2)

አሁን ደግሞ ወደ ሌላ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን ልውሰዳችሁ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድርስ አዳኖም። ኅዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ከሳዑዲ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ጊዜያዊ ማረፊያ ድረስ በመሄድ እንዳጽናኑና እንዳበረታቱ ፋና ዘግቧል። በርግጠኝነት ማረጋገጥ አልቻልኩም፣ ግን ዶክተሩ፣ ስደተኞች፣ የአገራቸውን መሬት በአይሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው እንደተቀበሏቸው የሚገልጹ አንዳንድ አስተያየቶች ፌስቡክ ላይ አንብቤያለሁ። ከአጥር አልፎ ሕዝብ ጋር መቀላቀል ማለት ይሄ ነው!!

ቅዳሜ ኅዳር 7 ቀን ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ አዲስ አበበ በተደረገ ሦስተኛው የዓለም አቀፍ ፋሚሊ ፕላኒንግ ኮንፍራንስ ላይ ያደረጉትን ንግግርም ማንሳት እፈልጋለሁ። "ዜጎቻችን ወደ አገር ሲመለሱ፣ ነገሮች በተስተካከለ ሁኔት እንዲሄዱ ለማድረግ እንሞክራለን። ሳዑዲዎች ሕገ-ወጥ ናቸው (ከአገር ውጡልን) ቢሏቸው፣ ግድ የለም፤ የሚሄዱበት አገር አላቸው። አጠንክሬ ላረጋግጥላችሁ፣ ዜጎቻችን በአክብሮት እንቀበላቸዋለን" ነበር ያሉት። ከአንድ ጨዋ፣ የተማረ፣ በሳል መሪ የሚጠበቅ ግሩም ንግግር! በአቶ ሽመልስ ከማል አይነቶቹ የደማው ልቤ ትንሽ ታደሰ።

ምን አለ ኢሕአዴግ እራሱን ከሽመልስ ከማሎች አጽድቶ ቴዎድሮስ አዳኖሞችን ቢያበዛ? ምን አለ ባለሥልጣናቱ የሚሰብርና ለሕዝብ ንቀት የሞላበት ንግግር ከሚናገሩ፣ የሚያሰባብስ፣ የሚያንጽ፣ የሚገነባ ንግግር ቢናገሩ? ምን አለ ዜጎችን በማሰቃየት፣ በመደብደብ፣ ሽብርተኞች እያሉ በማሰር፣ በማንገላታት ከሚደሰቱ፣ ዜጎች ሲጠቁ ማዘን ቢጀመሩ? ምን አለ እንደ እንስሳ ከሚሆኑ እንደ ሰው ቢሆኑ?

እንግዲህ እነቴዎዶሮስ አዳኖም የሚያረጉትን እያበረታታን፣ የተለየ ትዕዛዝ እየላኩ፣ ዜጎችን የሚያስደበድቡ፣ የዜጎችን መብት የሚረግጡና በዜጎች መጎሳቆል የሚደሰቱ፣ የአገዛዙ ባለሥልጣናትን ለማጥራት ሁላችንም ተባብረን መስራት ይኖርብናል። እነዚህ ግለሰቦች ለኢሕአዴግም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እርግማን ናቸው!!!! አገራችንን እንዲያምሱና እንዲያወኩ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በተለይም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እነዚህ ሰዎች የድርጅታቸው ጠንቅ፣ ድርጅታቸው የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርጉ መሆናቸውን አውቀቁ፣ እነርሱ ላይ ዘመቻ እንዲጀምሩ አሳስባለሁ።

በመጨረሻ አንድ ነገር ጣል ላድርግና ላቁም። በዚህ ወቅት የ"ጠቅላይ ሚኒስትራችን" ኃይለማርያም ደስአለኝ መሰወር ነው። እኝህ ሰው ዝምታን ለምን መረጡ? ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ፣ "አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ "እስረኛ" ናቸው" በሚል አውራምባ ታይምስ ላይ ባወጣው ጽሁፉ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሕዝብን ትርታ እንዲያዳምጡ፣ ከአማካሪዎቻቸው አጥር እንዲወጡ፣ እንደመሪ አገር መምራት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል።(3) ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በ3ኛው የአፍሮ-ዐረብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት (ሳዑዲዎችም ያሉበት) ወደ ኩዌት ትላንት ኅዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. አምርተዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በቀጥታ የተባበሩት መንግሥት ክላይሜት ቼንጅ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ዋርሶው ፖላንድ ያመራሉ። (የዓለማችን የአየር ሁኔታ በወገኖቻችን ላይ ከደረሰው ግፍ በልጦ ማለት ነው)

አቶ ኃይለማርያም የተማሩ ሰው ናቸው። በዚህ ወቅት ከአገር ምንም አይነት መግለጫ ሳይሰጡ፣ ሕዝቡን ሳያበረታቱ፣ ከአገር ውጭ መውጣታቸው፣ ምን ያህል ተሰሚነታቸውን እንደሚጎዳ ያጡታል ብዬ አላስብም። ታዲያ ምን ነክቷቸው ነው እራሳቸውን እንደዚህ የሚያገምቱት? ወደፊት በስፋት የምንነጋገርበት ይሆናል።

ግርማ ጌታቸው ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 
ኅዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም

(1) http://ethioforum.org/arrests-at-anti-saudi-protest-in-ethiopia-aljazeera/ 
(2) http://aigaforum.com/articles/what-we-learn-saudi-ethio.php 
(3) http://www.awrambatimes.com/?p=10948 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ