የ2012 ዓ.ም. 25ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች
ከየካቲት 16 - 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ ሃያ አምስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከየካቲት 16 - 22 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ እንደ ወትሮው ሁሉ ባሳለፍነው ሳምንት በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተለያዩ ክዋኔዎች የተስተናገዱበት ነው። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በመንግሥት ምሕረት የተደረገላቸው 63 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ መደረጉ ብዙ ያነጋገረና ቀዳሚ ጉዳይ ኾኖ ነበር።
ይሁንና በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት፣ የመንግሥትም ቀዳሚ ጉዳይ ኾኖ ብቅ ያለው በህዳሴ ግድብና በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ሲደረግ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ነው። ከዚህ ድርድር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ አንፃር ድርድሩ እየሔደበት ያለበትን መንገድ በመቃወም፤ በዋሽንግተኑ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ አሳውቃለች። ኾኖም በዚህ ድርድር ላይ የአሜሪካ መንግሥት ጣልቃ ገብነትን አመላካች ነው የተባለው የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ መሰማት ግን፤ ያሳለፍነው ሳምንት አውራ ዜና ኾኖ ሊታይ ችሏል። ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ፈጣን መግለጫ ሠጥታለች። በዚህ ዕለት የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ አንዳችም ስምምነት አይፈፀምም በማለት በድጋሚ የኢትዮጵያን አቋም ያንፀባረቀበት ሳምንት ኾኗል።
እንደቀዳሚዎቹ ሳምንታት ሁሉ ዶክተር ዐቢይና ፓርቲያቸውን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች መካሔዳቸውን የቀጠሉበት ነበር። ኢዜማ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታና ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ ያለውን አቋም በመሪው በኩል ያስተላለፈበትም ሳምንት ነበር። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እወቁልኝ ብሎ ባስተላለፈው መልእክት ፓርቲዎች ምዝገባቸውን የሚያጠናቅቁበትን ቀን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለዚህም ቀነ ገደብ አስቀምጧል።
የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት እንዲኾኑ የተሾሙት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ሹመቱን ላለመቀበል መወሰን፤ በዶ/ር ዐቢይ የሥልጣን ዘመን የመጀመሪያው ሹመቱን ያልተቀበሉ ግለሰብ ከመኾናቸውም በላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመን የተፈጠረ አዲስ ክስተትና ከሳምንቱ አነጋጋሪ ወሬዎች አንዱ ኾኗል። የብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ውስጥ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት እየተዘጋጀ መኾኑን ማስታወቁ በሳምንቱ አዳዲስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ብዙ ያነጋገረ ጉዳዩ አሳሳቢ እየኾነ ስለመጣ፤ በአገር ደረጃ የኮሮና ሻይረስን ለመከላከል ስድስት ሚኒስትሮች ያሉበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የአብን የአመራር ለውጥም ከሳምንቱ ዜና አንዱ ነው። ባልተለመደ ሁኔታ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የአገሪቱን ከተሞች ለሰዓታት በጨለማ ውጦ ነበር። ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት መንሥኤውን ለማወቅ ያልተቻለ ቢኾንም፤ ችግሩ በተፈጠረ በማግሥቱ የተሠጠው መግለጫ ከግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጋር የተያያዘ መኾኑ ተገልጿል።
ከኢኮኖሚ ዜናዎች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የባንኩን ብድር ያልመለሱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚንቀሳቀስ መግለጹና የቀደመውን የብድር አሠጣጥ የባንኩ ፕሬዝዳንት ኮንነዋል። 171 የሚሆኑ ለእርሻ ብድር የወሰዱ ሰዎች ከእርሻቸው ቦታ መጥፋታቸውና ቦታው ላይ ያለመገኘታቸውንም ገልጿል። የኢትዮ ቴሌኮም የብሮድባንድ አገልግሎት የዋጋ ቅናሽም ሌላው ተጠቃሽ ቢዝነስ ነክ ዜና ነበር። በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተጠናከረው ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል።
የብልጽግና ፓርቲና በትግራይ የሚከፍታቸው ጽሕፈት ቤቶች
ብልጽግናና ሕወሓት በትግራይ
ከሰሞኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እንደ አዲስ ነገር ሊታይ የሚችለው ሌላው ዜና የብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል በሁሉም ወረዳዎች ጽሕፈት ቤት የሚከፍት መኾኑን በይፋ መገለጹ ነው። ይህ እርምጃ ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ውስጥ ከሕወሓት ጋር ብርቱ ተፎካካሪ ይኾናል የሚል እምነት አሳድሯል።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ዘመን በሠጡት መግለጫ፤ የብልጽግና ፓርቲ በትግራይ በሁሉም ወረዳዎች ቢሮዎች ለመክፈት እየተዘጋጀ መኾኑን ነው።
ኃላፊው አቶ አወሉ አብዲ ለጋዜጣው ከሠጡት ሰፊ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለውም፤ ብልጽግና አገር አቀፍ ፓርቲ በመኾኑ ከትግራይ ክልል ጋር በሚኖረው ሕገ መንግሥታዊ ግንኙነት መሠረት አደረጃጀቱን በማስፋት በቅርቡ በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጽሕፈት ቤቶችን የሚከፍት መኾኑን ነው።
የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም በማስታወስ በክልሉ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ እየሠራ ነው። ፓርቲው በትግራይ ክልል ብዙ ደጋፊዎች እንዳሉትና በሕወሓት ውስጥ ያሉት ከግማሽ በላይ አመራሮች የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ መኾናቸውን ጭምር ኃላፊው ገልጸዋል።
ከብልጽግና ፓርቲው በተቃራኒ የቆሙት ጥቂት ኃይሎች መኾናቸውን የሚገልጹት አቶ አወሉ፤ እነዚህ ጥቂት ተቃራኒ ኃይሎች ሕዝቡን በየቤቱ በመሣሪያ የሚያስፈራሩት ቢኾንም፤ ሕዝቡ እንደማይቀበላቸውም ተናግረዋል። “ምክንያቱም በትግራይ ክልል ያለው ሕዝብም የፓርቲውና የለውጡ ደጋፊ ነው” በሚል መግለጻቸውን ይኸው የአዲስ ዘመን ዘገባ ያመለክታል።
ሕወሓት ራሱን ከውሕደቱ ማግለሉ መብቱ ነው። “ይሄ በጣም ልንኮራበት የሚገባ ነው። ያመኑበትንና የራሳቸውን አቋም የገለጹበት ሁኔታ ስለኾነ እንደ ችግር የሚታይ አይደለም። ነገር ግን ብልጽግና ባለው አገራዊና ክልላዊ አደረጃጀት፤ የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ እንዲቋቋም ተደርጓልም” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አዲሰ አበባ ላይ ተከፍቷልም ብለዋል። “ይህ አገራዊ ፓርቲ በሁሉም ክልሎች ላይ ተንቀሳቅሶ የራሱን ዓላማ ለሕዝቡ የሚሸጥበት ሁኔታ ይኖራል” በማለትም ኃላፊው መግለጫቸውን ያመላክታል። (ኢዛ)
የህዳሴ ግድብና ወቅታዊ ትኩሳቱ
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ከጀመረች ከስምንት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። በአሁኑ ወቅት የግድቡ ሥራ ከ70 በመቶ በላይ ተጠናቋል። የግድቡ ሥራ ሲጀመር ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብቷን ተጠቅማ ሲሆን፣ የተፋሰስ አገሮችንም መብት ሳትዘነጋ ስለመኾኑ ግልጽ ነው። የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ አመለካከት ጭምር ነው።
ለዚህም ነው በተለይ ግብጽና ሱዳንን ያካተተው የሦስቱ አገራት የጋራ የምክክር መድረክ ተፈጥሮ በግድቡና በአጠቃላይ የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ሲመክሩ የቆዩት። የግብጽ አደነቃቃፊ ሁኔታዎች የተደጋገሙ ቢኾንም፤ ይህንን በዘዴና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመያዝ ዛሬ ላይ ተደርሷል። በዚህ የምክክር መድረክ የበረከቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ያሉት ቢኾንም፤ ሒደቱ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ኖሮት ለማጠናቀቅ ግን ጊዜ ወስዷል። በተለይ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ውይይት አጠናቀው ሁሉንም የሚያስማማ ሕጋዊ ሰነድ አዘጋጅቶ ለመፈራረም ቀላል ሊሆን ስላልቻለ ድርድሩን ማራዘሙ አልቀረም።
ምናልባት ወደ ስምምነት ለመድረስ በቅርቡ ታዛቢ ባለበት ድርድር እንዲደረግ በመስማማትና የውይይቱን ቦታ በዋሽንግተን ዲሲ ጭምር እንዲካሔድ ምክንያት ኾኗል። በሦስትዮሹ ውይይት በታዛቢነት እንዲገኙ ይሁንታ የተሠጣቸው የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በተከታታይ የውይይት መድረኮቹ ላይ እንደተባለው በታዛቢነት ሚናቸው ተገኝተዋል። ከታዛቢነት ውጭ ሚና የሌላቸው መኾኑ ታውቆ በዚሁ አግባብ ውይይቱ ሲካሔድ ቆይቷል። የዓባይ ወንዝና የህዳሴ ግድብን ተከትሎ ሊኖር የሚችለው የውኃ አጠቃቀም ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ወሳኝ የኾነው የሕግ ረቂቅ ላይ ተግባብቶ የጋራ ውሳኔ ለመወሰን ግን ቀላል ባለመኾኑ፤ አሁንም ጉዳዩ ተረጋግቶ ማየትን ጠይቋል። በስተመጨረሻም ለዚህ ገዥ የሚኾነውና አገራቱ ሊፈርሙ ይገባል ተብሎ የቀረበው ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያን የሚጐዳ መኾኑ እየታወቀ ሲመጣ፤ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ሊደረግ በነበረው የሦስትዮሽ ምክክር ላይ ላለመገኘት ኢትዮጵያ ውሳኔ ላይ እንድትወስን አስገድዷታል።
ይህንን ውሳኔዋን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ስታሳውቅ በዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያን የሚጐዳ አንዳች ነገር እንደማትፈጽም ለሕዝብ በማሳወቅ ጭምር ነው። ከዚህ ጐን ለጐን በዚሁ ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ልዩ መልእክተኞች ወደ ግብጽ አምርተው ድርድሩን አዘግይቶ ለመቀጠል ሐሳብ ያለው መልእክት ለግብጽ ፕሬዝዳንት እንዲደርስ ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ይህ ባለበት ሁኔታ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ ያወጣው አንድ መግለጫ ውስጥ ያሰፈረው ሐረግ፤ አሜሪካ ታዛቢ ኾና ገብታ አዛዥ ናዛዥ ለመኾን ትሻለች እንዴ? በሚል ከኢትዮጵያ ወገን ቁጣ እንዲቀሰቀስ አድርጓል። ይህ መግለጫ አሜሪካ ለግብጽ ያደላች ስለመኾኗ የታየበት ነው።
አሜሪካ በዓባይ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ስለመኾኑ ሌሎች ምልክቶች ነበሩና ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ተቃውሞ ሰልፍ እስከመውጣት የደረሱበት ነው። ነገር ግን ከዚህ ተቃውሞ ማግስት ከአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት የወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመሙላት የግድ ፍቃድ መጠየቅ ወይም ሦስቱ አገራት ስምምነት ሳያደርጉ ውኃ የመሙላት ሙከራ ማድረግ የማትችል ስለመኾኑ የሚያመለክት ነበርና ይህ አካሔድ አደገኝነቱ ለሁሉም ግልጽ በመኾኑ በኢትዮጵያ በኩል ፈጣን ምላሽ የተሠጠበት ኾኗል።
እንደተጠበቀውም የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ መግለጫ በእጅጉ ማዘኑን በመግለጽ፤ አስቸኳይ መግለጫ አውጥቷል። ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ በአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፖርትመንት ሴክሬታሪ የወጣው መግለጫ ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረበት በማስተወቅ፤ ይህ መግለጫ የወጣውም ስብሰባው እንዲተላለፍ ኢትዮጵያ አሳውቃ እያለ መኾኑም የአሜሪካ መግለጫ ላይ ያላትን ቅሬታ አጉልታለች።
“የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሠረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሠረት የምታከናውን ይሆናል” በማለት ኢትዮጵያ ያወጣችው መግለጫ ያመለክታል።
አያይዞም በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ መንግሥት ፈርሞበታል የተባለው ረቂቅ የሦስቱን አገራት የድርድርም ሆነ የሕግና ቴክኒክ ቡድኖች ውጤት ያለመኾኑን በመጥቀስ፤ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም ብሏል።
የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅ መመሪያና ደንብ የሚዘጋጀው በሦስቱ አገራት ብቻ ስለመኾኑ ቀድማ ማሳወቋንም በዚሁ መግለጫ ጠቅሳለች።
በመጨረሻም በሦስቱ አገራት የተጀመረውን ድርድር ለመቀጠልም ቁርጠኛ መኾኗን አሳውቃለች። ከዚህ መግለጫ በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም፤ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያ ፍላጐትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያደርግ በግድቡ ዙሪያ ከተወያየ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ አስታውቋል።
በህዳሴ ግድብና በዓባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ላይ ኢትዮጵያ ደጋግማ እንዳሳወቀችው፤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ምንም ዐይነት ነገር የማታደርግ መኾንዋንና የግድቡን ግንባታም ለሰከንድ እንደማታቆምም አስታውቃለች። ይህም አቋሟ የሕዝቡን ይሁንታ አግኝቷል።
በሰሞናዊው የህዳሴ ግድብና የዓባይ ውኃ አጠቃቀም እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ሰሞናዊ መግለጫ ላይ ምሁራን አስተያየት እየሠጡ ሲሆን፣ በጥቅል ሲታይ የአሜሪካ መግለጫ ግልጽ ጣልቃ ገብነትን ያሳየና ለግብጽ የወገነ ተግባር መኾኑን ነው።
የሦስቱ አገራት ጉዳይ እንዲህ ባለ መልኩ ሳምንቱ ያለፈ ቢኾንም ቀጣዩ እርምጃ ወዴት ይጓዝ ይሆን? የሚለው ጥያቄም ለሁሉም የቤት ሥራ መኾኑ አይቀርም። (ኢዛ)
የ63 ተጠርጣሪዎች መፈታትና አንደምታው
ባሳለፍነው ሳምንት ከወቅታዊ ፖለቲካ ክንውኖች መካከል መንግሥት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ ለነበሩና ሙስናን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ 63 ግለሰቦችን ከእስር መልቀቁ ነው። ከለውጡ ወዲህ ተይዘው፣ ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት እነዚህ ተጠርጣሪዎች የተፈቱት የተመሠረተባቸው ክስ ተቋርጦ ነው።
በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መግለጫ የሠጠበት ሲሆን፣ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ከተፈቱት ውስጥ የቀድሞ የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተርን ጨምሮ በቢዝነሱ ዓለም የሚታወቁ ግለሰቦችም በዚህ ሰሞናዊ የመንግሥት ምሕረት መዝገብ ውስጥ ተካትተዋል።
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረቱባቸው የሚገኙበት ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ብክነትና ሙስና የተፈጸመበት መኾኑ በሚጠቀሰው በሜቴክ ጉዳይ የተከሰሱ ይገኙበታል።
እንደ ብዙዎቹ አስተያየት እነዚህ በከባድ ሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች በተሠረተባቸው ክስ ፍርድ ያገኛሉ ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን፤ መንግሥት ክሳቸውን አቋርጦ ለቋቸዋል።
ከእስር የተለቀቁት ከእነዚህ ግለሰቦች ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ግጭት ከማስነሳትና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የተከሰሱ የሚገኙበት ሲሆን፣ በተለይ ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ ባለቤቶችና የኤጀቶ አባላት፣ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴና አባላት ጭምር ይገኙበታል።
እንደ መንግሥት እምነት እነዚህ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት የተመሠረተባቸው ክስ ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ነው።
በሌላ በኩልም በተከሰሱበት ወንጀል የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ መኾኑ ታምኖ ውሳኔው እንደተላለፈ አመልክቷል። ብዙዎች በእስር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩ ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ሊያካትቱ ይችላል ተብሎ የገመቱ ቢኾንም፤ ባሳለፍነው ሳምንት ከተፈቱት እስረኞች ውስጥ ስማቸው አልተካተተም።
ይህ የመንግሥት ውሳኔ እንደተባለው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ይቅር ባይነት ለማመልከት ታስቦ የተተገበረ ቢኾንም፤ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ግን በሙስና የተጠረጠረን ሰው እንዲህ ባለ መንገድ መልቀቅ ነገ አደጋ አይኖረውም ወይ? የሚል ሥጋታቸውን እንዲያንጸባርቁ አድርጓል።
አንዳንድ ታሳሪዎችም ቀድሞም መታሰር የለባቸውም ነበር፤ ክስ ለመመሥረት በቂ መረጃ አልነበረም የሚል አስተያየት የሠጡም ነበሩ። በሌላ በኩል የመንግሥት እርምጃ ተገቢ መኾኑን ገልጸው በሙስና ዋና ዋና ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ግን በተገቢው መንገድ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አስተያየት አንዳንዶች ሠጥተዋል።
የግለሰቦቹ መፈታት በተለይ ለቤተሰቦቻቸው መልካም የመኾኑን ያህል፤ በተከሰሱበት ወንጀል በእርግጥም ሙሉ ለሙሉ ነፃ ናቸው ብሎ ለመገመት አዳጋች እንደሚኾንባቸው የሚገልጹት ደግሞ፤ የመንግሥት ውሳኔ ብዥታ እንደፈጠረባቸው ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ከተሠጡ አስተያየቶች ለመገንዘብ ተችሏል። (ኢዛ)
የዮሐንስ ቧያለው ያልተለመደ ውሳኔ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተለያዩ ተቋማትን የሚመሩ በርካታ ሹመቶችን ሠጥተዋል። ይሁን እንጂ ከሾሟቸው መካከል ሹመቱን ላለመቀበል ይፋዊ መግለጫ በመሥጠት ሊጠቀሱ የሚችሉት የቀድሞው የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው። ከሁለት ሳምንታት በፊት ከክልሉ ኃላፊነት ለቀው ለፌዴራል መንግሥት እንደሚሾሙ ሲገለጽ በአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ብዙ አሟግቶ ነበር።
አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ አራቱ የክልሉ ባለሥልጣናት ወደ ፌዴራል መሔድ የለባቸውም ብለው ሲሞግቱ የነበሩ አባላት፤ ዋነኛ ምክንያታቸው ክልሉ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል ከሚል መነሻነት ቢኾንም፤ የእነዚህ ባለሥልጣናት ወደ ፌዴራል መሔድ የፓርቲ ውሳኔ ስለኾነ ይህንን መቀበል ይገባል ተብሎ፤ የእነርሱ ሽኝት የአዳዲስ የክልል ተሿሚዎቹ ሹመት በአብላጫ ድምፅ ተወስኗል።
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ወዲያው በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አቶ ዮሐንስ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም የተሰየመውን አካዳሚ እንዲመሩ ይሾማሉ ብለው ጠቁመው ነበር። እነዚሁ ማኅራዊ ሚዲያዎች አቶ ዮሐንስ ግን ይህንን ሹመት እንደማይቀበሉ መላምት መሥጠታቸውም ተጠቅሶ ነበር። እንዲህ ካሉ መረጃዎች በኋላ አቶ ዮሐንስ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ኾነው መሾማቸው ተገለጸ። ከዚያም በማግስቱ አቶ ዮሐንስም ይህንን ሹመት ለመቀበል እንደሚቸገሩ በይፋ የዶ/ር ዐቢይን ሹመት ባለመቀበል አቋማቸውን በመግለጽም በፓርቲው የመጀመሪያ ሰው ስለመኾናቸው ተረጋገጠ።
ይህ እርምጃ አሁን ባለው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው የራሱ የኾነ አንደምታ ቢኖረውም፤ አቶ ዮሐንስ ይህንን ሹመት ላለመቀበል የሚቸገሩበትን ምክንያት እንዲመሩት በሹመት የተመደቡበት ተቋም ስያሜ ጋር የተያያዘ መኾኑን ከሠጡት መግለጫ መገንዘብ ተችሏል።
በአንፃሩ ግን የአቶ ዮሐንስ እርምጃ በብዙዎች ዘንድ በመልካም እንዲታይ ያደረገው በሠጡት አስተያየት ላይ ፓርቲያቸውን ለማገልገል ቁርጠኛ መኾናቸውን መግለጻቸው ነበር። በሌላ የኃላፊነት ቦታ ቢመደቡ ሊሠሩ የሚችሉ መኾኑን አስረድተዋል።
በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እንዲህ ባለ ደረጃ ከታሰበ፤ መቻቻልን ለማስፈንና ይቅር ባይነትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳርፍ፤ እንደ አንድ ለውጥ ፈላጊና ለውጡን ለማምጣት እንደታገለ ፖለቲከኛ ውሳኔያቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ኾኗል። ባሳለፍነው ሳምንትም በዚህ ዙሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩ የነበሩ አስተያየቶች ይህንኑ ያመላከቱ ሲሆን፤ ቀጣይ ማረፊያቸው ግን ገና አልለየም። (ኢዛ)
የድጋፍ ሰልፎች
ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት እንደኾነው ሁሉ በዚህም ሳምንት በተለይ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞችና ወረዳዎች ብልጽግና ፓርቲና ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለመደገፍ ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሳተፍ የተካሔዱት እነዚህ ሰልፎችን የዶክተር ዐቢይ አሕመድን አመራር የሚደግፍ፣ ፓርቲያቸውን የሚያወድስና ዶክተር ዐቢይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወኑትን የተለያዩ ተግባራት በማንሳት ያመሰገኑበት ትዕይንቶች ናቸው።
ባለፈው ሳምንት የድጋፍ ሰልፎቹ ከተደረጉባቸው አካባቢዎች መካከል አሶሳ፣ ሞጆ፣ ባሌ ሮቤ፣ በቆጂ፣ ጊምቢና ወሊሶ ይገኙበታል። እነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ለብልጽግና ፓርቲ ይሁን ተብሎ የተለያዩ በዐይነትና በገንዘብም ድጋፍ ስለመሠጠቱ የተወሳበት ሲሆን፤ ዶክተር ዐቢይ ምስጋና ያቀረቡበት መልእክት ተላልፎ ነበር።
እነዚህ ሰልፎች በብዙዎች ያልተጠበቁ ቢኾንም የሰልፈኛው አመለካከት ደግሞ በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደገፍ እንዳለባቸው አመላካች መኾኑን የሚገልጹ የመኖራቸውን ያህል፤ አንዳንዶች ደግሞ ሰልፎቹ የሚካሔዱት ለምርጫ ቅስቀሳ በፓርቲው አደራጅነት የተከናወነ ነው ይላሉ። እንደ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ ደግሞ ሰልፈኞች ገንዘብ ተከፍሏቸው የወጡ መኾኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል። በአንፃሩ ደግሞ አቶ በቀለ ገርባና አንዳንዶች የሠጡትን አስተያየት በእጅጉ በመኮነን፤ “ይህ ሕዝብን መናቅ ነው” በማለት የሰሉ ትችቶችን ሰንዝረዋል። ገለልተኛ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ሰሞናዊ ሰልፎቹ ወቅታዊውን ፖለቲካ የቀየረ ፅንፍ ይዘው ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መልእክት የሠጠና ያስተላለፈ መኾኑን ይጠቅሳሉ። ዶክተር ዐቢይና ፓርቲያቸው ጠንከር ብሎ የወጣ መኾኑንም ያሳየ ነው ብለዋል። (ኢዛ)
ልማት ባንክና አየር ላይ የቀረው ብድሩ
ከአገሪቱ ባንኮች በተበላሸ ብድር ክምችቱ አቻ የሌለውና አሁን በይፋ እንደተረጋገጠውም ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ የተበላሸ ብድር ያለው ይህ ባንክ፤ በተለይ ለእርሻ ከሠጠው ብድር ውስጥ አብዛኛውን ማስመለስ ከሚቻልበት ደረጃ የደረሰ መኾኑ ይታወቃል። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ባሳለፍነው ሳምንት እንደገለጹት የባንኩ የተበላሸ የብድር ምክንያቶቹ የተለያዩ መኾኑንና ባንኩን ሪፎርም ለማድረግ ወደኋላ መለስ ተብሎ የተደረገ ፍተሻ ማረጋገጡን ነው።
ባንኩ የብድር አሠጣጡና የብድር አስተዳደሩ ደካማ ከመኾኑም በላይ፤ ብድር ሲሠጥ ማረጋገጥ የሚገባውን ሥራ ያልሠራ ጭምር መኾኑ ነው። በብድር አሠጣጡ ውስጥ ባለሥልጣናት ጭምር እጃቸውን ያስገቡ እንደነበር፣ የባንኩ ሠራተኞችም ባልተገባ መንገድ የተፈቀደውን ብድር እንዲለቀቅ በማድረግ የባንኩን የተበላሸ ብድር ከፍ እንዲል ማድረጋቸውን ሁሉ ገልጸዋል።
ባንኩ በብድር የሠጠውን ገንዘብ ለማስመለስ ለብድር ማስያዣ የዋሉ ንብረቶችን የማፈላለግ ሥራ ውስጥ ሲገባ፤ በተለይ ለእርሻ ብድር ከወሰዱትና መሬት እደላቸው ወዳለበት ሲኬድ ወደ 171 የሚኾኑትን ባለሀብቶች ማግኘት ያለመቻላቸውና መሬቱን ጥለው እንደሔዱ ማረጋገጥ መቻሉን ተገልጿል።
እነዚህንና ሌሎች ብድር መመለስ ሲገባቸው ጥለው ጠፉ የተባሉትን ተበዳሪዎች በሕግ ለመጠየቅ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊው ምርመራ ተጠናቅቆ በፍትሐብሔርና በወንጀል ለመክሰስ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፤ ይህም በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል። የተገኙ ንብረቶችንም በመያዝ ወደ ሦስተኛ ወገን ለማስተላለፍና ለማስወገድ ባንኩ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከብድር አሠጣጥ ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ባንኩ ክፍተት ያለባቸውን አሠራሮች በማረም፤ የቀድሞ አሠራሮቹን በመቀየር አዲስ የተበላሸ ብድር እንዳይኖር እየሠራ መኾኑንም የባንኩ ፕሬዝዳንት በሠጡት መግለጫ አስታውሰዋል። ከዚህ በኋላ ባንኩ ያለበትን የተበላሸ የብድር መጠን በየዓመቱ ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት በአራት ዓመት ውስጥ የተበላሸ የብድር መጠኑን ወደ 10 በመቶ ለማውረድ እየሠራ ነው። ባንኩ የነበረበትን ችግር ለማቃለል ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ብዙ ስለመሥራቱ ተገልጿል። ባንኩ የሚመራበትን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት መተግበር መጀመሩንም ባንኩ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ለውጥ እያሳየ መምጣቱን፣ 40 በመቶ የነበረውን የተበላሸ ብድር በ2012 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ወደ 34 በመቶ ማውረዱን ገልጿል። ይህ ብቻ ሳይኾን ባለፈው ዓመት 740 ሚሊዮን ብር ቢከስርም፤ ዘንድሮ በግማሽ ዓመቱ 950 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉንም አስታውቋል። በተበላሸ ብድሩ 40 በመቶ የደረሰበትና በቢሊዮን የሚቆጠር ያበደረው ገንዘብ ሊመለስ እንደማይችል እየተገለጸ፤ ይህንን ያህል ትርፍ ማስመዝገቡ እንዴት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ የባንኩ ፕሬዝዳንት በሠጡት ማብራሪያ፤ አዲስ የተበላሸ ብድር እንዳይኖር መሠራቱ ከጤነኛ ብድሮቹ ያገኘውን ገቢ ማሳደጉና ሌሎች ምክንያቶችንም በመጥቀስ፤ ባንኩ በስድስት ወር በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ አግኝቷል ብለዋል። (ኢዛ)
ኢትዮጵያን በጨለማ የዋጠው ምሽት
የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ በኢትዮጵያ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጦ ነበር። ከምሽቱ ወደ 12 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ከተሞች የተስተዋለ ሲሆን፤ በዚያ ምሽት ለኤሌክትሪክ አገልግሎቱ መስተጓጐል ይሄ ነው የሚባል ምክንያት ሊሠጥ አልቻለም። ቢኾንም ችግሩን ከማፈላለግ ጐን ለጐን የተቋረጠውን ኃይል ለማስጀመር የተለያዩ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቆ፤ በአዲስ አበባና በአካባቢው ከ3 - 5 ሰዓታት በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ሥርጭት በየደረጃው እንዲለቀቅ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚጠቁመው ችግሩ ከግለልገል ጊቤ ሦስት ከሚቀርበው የኃይል መስመር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መኾኑን አስታውቆ፤ አሁን ችግሩ ተቀርፏል ብሏል።
ይሁንና በዕለቱ የተፈጠረው የኃይል መቆራረጥ በርካታ ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል። እንደ ባቡር ያሉ አገልግሎቶችም በኃይል እጥረቱ ባሉበት ቦታ ቆመው ምሽቱን አሳልፈዋል። በተለይ በዚያው ምሽት የኃይል መቋረጡ ምክንያት ያለመታወቅና በዚህን ያህል ደረጃ እንዲህ የኃይል መቋረጥ ተከስቶ ስለማያውቅ ብዙዎችን ሥጋት ላይ ጥሎም ነበር። (ኢዛ)
ኮሮና ደጃፍ ላይ ነው
የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ሥጋት ወደ መኾን ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ዘግይቶም ቢኾን በዓለም የጤና ድርጅት ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት 60 አገራትን ያዳረሰ ሲሆን፣ ከ2 ሺህ 933 በላይ ሰዎችን ገሏል። በቫይረሱ የተያዙ ደግሞ ከ85 ሺህ 674 በላይ ደርሷል። (እስከ 22/6/2012 ዓ.ም.)
ይኼ ቫይረስ በተከሰተበት ጊዜ በጥቂት አገራት የተስተዋለ ሲሆን፣ ዛሬ የዓለማችንን ወደ አንድ ሦስተኛ የሚኾኑ አገሮችን ወደ መድረስ ደረጃ ደርሷል። ዳር ዳር ሲል የነበረው የዚህ ቫይረስ ሥርጭት ጉዳይ አፍሪካ ውስጥም ገብቶ ለኢትዮጵያ ሥጋት ወደመኾን ደረጃ ደርሷል። የቫይረሱ ሥርጭት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በማስቆም ብቻ መከላከል ይቻላል ለማለት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል። ይህ ጉዳይ በተለይ በዚህ ሳምንት አንድ ተጠርጣሪ ቻይናዊ “ገብቷል፤ አልገባም” የሚለውን ነገር አጠራጣሪ እስከማድረግ የተደረሰ ሲሆን፤ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ይህንን ተጠርጣሪ በመመርመር ነፃ መኾኑን አረጋግጧል።
እስካሁንም በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቃ ያለመገኘቱም መልካም ቢኾንም፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚችለውን ለማወቅ ከባድ ነው። ለዚህም ይመስላል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ይህንን ቫይረስ ለመከላከል ይቻል ዘንድ አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሟል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው አምስት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ክትትል የሚያደርግ በብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላት ኾነው የተሰየሙት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የገቢዎች ሚኒስትሩ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሸዴ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው።
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው በማቆያ እንዲቆዩ የተደረጉት 20 ሲሆኑ፣ ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸው ታውቋል። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት የአንድ ተጠርጣሪ ጉዳይ ብዙ አነጋግሮ ነበር።
የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. አንድ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠር ግለሰብ ወደ መቆያ መግባቱን የጤና ሚኒስቴር ካስታወቀ በኋላ፤ የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው አነጋግሮ ነበር። በዚያን ዕለት ወደ ማቆያ የገባው ቻይናዊ ከአምስት ቀን በፊት ከቻይና ቤጂንግ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ መኾኑን ተከትሎ፤ ቫይረሱ አለበት የሚል ጥርጣሬ ቢያሳድርም፤ በዕለቱ ማምሻው ላይ በደረሰው የምርመራ ውጤት ነፃ መኾኑ መታወቁ ነገሮች አረጋግቷል። ይሁንና የጉዳዩ አሳሳቢነት ታምኖ ክትትሉን ለማጠናከር እየተሠራ ነው። (ኢዛ)
የኢዜማ ወቅታዊ ምልከታና ሥጋት
በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ኢዜማ በቀዳሚው ሳምንት አጋማሽ ላይ “የኢትዮጵያ የለውጥ ሒደት፣ የቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፋይዳና የተደቀኑ አደጋዎች” በሚል ርዕስ 19 ገጽ ያለው መልእክት አስተላልፏል።
ኢዜማ በይፋ ከተመሠረተ ወዲህ እንዲህ ባለ ሁኔታ የተደራጀ መልእክት ሲያስተላልፍ የመጀመሪያው ነው ሊባል ይችላል።
በራሱ ምዘናና ግምገማ ወቅታዊውን የአገር ጉዳይ የደረሰበትን ያመላከተበት፣ በፖለቲካ ጨዋታው ውስጥ አሉ ያላቸውን ችግሮችንም የዳሰሰበትና ምልከታውን ያካተተበት ነው። ከመጪው ምርጫ 2012 ጋር ተያይዞ ያለውን ሥጋት ያተተበት፣ ገዥው ፓርቲ እየፈጸመ ነው ያላቸውን ተግባራትም በዚሁ ሰፊ ምልከታ ውስጥ ያካተተ ሲሆን፤ የመፍትሔ ሐሳቦችንም የጠቆሙበት ነው።
በፕሮፌሰር ብርሃኑ በኩል የተላለፈው ይህ መልእክት በመግቢያው ላይ ከለውጡ ወዲህ የታዩ መልካም ጅማሬዎችን በመጠቆምና አሁን እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስ የተከናወኑ ያላቸውን እውነቶች ያሳየበት ነው።
ኾኖም አሁን በተግባር እየታየ ባለው የፖለቲካ አውድ ውስጥ እያጋጠሙ ናቸው ያላቸውን ችግሮች በሚያመላክተው የመልእክቱ ክፍል ውስጥ ከጠቀሳቸው ውስጥ የፅንፈኝነት ሁኔታ አንዱ ነው። በተለይ ለቀጣዩ ምርጫ ሳንካ ይኾናሉ ብሎ ካስቀመጠው ውስጥ፤ በብሔር የተደራጁ ፅንፈኛ ኃይሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል የሚፈጥሩትን ችግር ነው።
እነርሱ “ክልላችን” በሚሉት አካባቢ ከሚያራምዱት ውጭ ያለን ማንነታቸውንም አመለካከት ወይም ድርጅት ላለመስማት በመፈለግ፣ ወይንም ሕዝቡን እንዳይሰማ ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአብነት ጠቅሰዋል። ይህም ለመድሎ ምክንያት እንደኾነ በመጥቀስ፤ ይህ ዐይነቱ አካሔድ ደግሞ ለመፈናቀል ጭምር ምክንያት እንደሚኾንም መልእክቱ አስቀምጧል።
በታችኛው እርከን ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች የሚፈጥሯቸው እክሎች፣ እንዲሁም በከፍተኛው ባለሥልጣናትና በገዥው ፓርቲ እውቅና ሠጥቷቸው የሚፈጸሙ ክልሎችም የኢዜማ ሥጋቶች ናቸው ብሏል።
ከገዥው ፓርቲ አንፃር ደግሞ በተለይ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለገዥው ፓርቲ ማስመረጫ ገንዘብ ማሰባሰብ በሚል እየተሔደበት ያለው መንገድ ጨምሮ ይኼ ባለ19 ገጹ መልእክት የተለያዩ የሕብረተሰብን ክፍሎች በንዑስ ርዕስ ከፋፍሎ መልእቱን ያስተላለፈበት ነበር። ቀጣይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ መልካም ይኾን ዘንድ ሕዝቡ፣ ምሁራን፣ ወጣቱ፣ የንግዱ ሕብረተሰብ፣ የፀጥታ ኃይሎችና ለመሳሰሉት ሊፈጽሙ ይገባል ብሎ ያመነበትን መልእክት ያስቀምጣል።
ለምሁራን ባስተላለፈው መልእክት “ይህ የለውጥ ሒደት ይዞት የመጣውን እድል በድጋሚ እንዳናጣው ከፍተኛ ሚና ይጠበቅባችኋል” ብሎ፤ ለዚህ ደግሞ በነፃነት እንዲሠሩ ጠይቋል። ለንግዱ ሕብረተሰብ ደግሞ ለውጡ በትክክል ከሔደ እውነትም በእጅጉ ተጠቃሚ ትኾናላችሁ ብሎ ከአድርባዮች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል። የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ሊፈጽሟቸው ይገባል ብሎ ያመነበትንም በዚሁ መልእክቱ ላይ አስተላልፏል።
በተለይ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሉ አባላት “ሕግ ማስከበር ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታችሁ ቢሆንም፤” በተለዩ ሁኔታዎች ሕግ ሲጣስ ይህንን የማስከበር ኃላፊነታችሁን ተወጡ ብሏል። ሕጋዊ ስብሰባዎች በነውጠኞች ሲስተጓጉሉና የሕዝብ የተለያዩ የሐሳብ አማራጮችን የመስማት መብቱ ሲጣስ እያያችሁ ዝም ማለት የለባችሁም ብሏል። ሞያዊ ግዴታችሁን ያለመወጣት ለአገር አደገኛ በመኾኑ፤ እንደ ዜጋም እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፎላቸዋል። (ኢዛ)



