Ethiopia Zare's weekly news digest, week 23, 2012 Ethiopian calendar

ከየካቲት 2 - 8 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ ሦስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከየካቲት 2 - 8 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ከተሰሙ ዜናዎችና በአገራዊ አጀንዳነቱ በቀዳሚነት ሊቀመጥ የሚችለው በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በህዳሴ ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ በዋሽንግተን ዲሲ ሲደረግ የነበረው ውይይት ውጤት አልባ ኾኖ መጠናቀቁ ነው። ተደራዳሪ አገራቱ ከቀደሙ ጊዜያት በተለየ በተከታታይ አዲስ አበባ፣ ካርቱምና ካይሮ፤ ከዚያም ዋሽንግተን ድረስ በመመላለስ ያደረጉት ውይይቶች አንዴ ተስፋ ሠጪነታቸው ሲነገር፤ በሌላ ወቅት ደግሞ ተስፋ የተደረገባቸው ነገሮች እንዳልኾኑ ሲሆኑ ቆይተው፤ መጨረሻውን ለመገመት ያዳገተ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት ግን በመጨረሻ መስማማት ላይ ያደርሳል የተባለው የሕግ ማዕቀፍ ላይ ስምምነት መታጣቱ የሳምንት ትልቁ ዜና እንዲኾን ያደርገዋል።

ከዚህ ቀዳሚ ክስተት ጋር በተያያዘ የሱዳን አቋምና ድርድሩን በታዛቢነት ለመከታተል በአሥራ አንደኛው ሰዓት የተቀላቀሉት የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥትም በዓባይና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ አስደሚሚ አቋም ይዘዋል መባሉ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲሠጠው ኾኗል። ለስምምነት የቀረበው የሕግ ማዕቀፍ ኢትዮጵያን የሚጐረብጥ እንደኾነም ተነግሯል። ይህም በኋላ ላይ እጃቸውን አስገቡ የተባሉት የዓለም ባንክና የአሜሪካ አቋም ጨዋታውን አራት ለአንድ የሚል አስተያየት እንዲሠጥበት አድርጓል። እሱም ኢትዮጵያ በአንድ ወገን፤ ሱዳን፣ ግብጽ፣ የዓለም ባንክና አሜሪካ በአንድ ወገን ኾነዋል የሚል አመለካከት በመያዙ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚነካ ሰነድ ላይ ለመፈረም ብዕር አላነሳም ብሏል።

ከወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር በቅርብ ኦፌኮን በመቀላቀል በፖለቲከኛነት ብቅ ያለው የአቶ ጃዋር መሐመድ የዜግነት ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ በዜግነት አመላለሱና ሒደቱ ላይ ማብራሪያ ይሠጠው ዘንድ ይመለከተዋል ያለውን መንግሥታዊ ተቋም ለመጠየቅ የተገደደው በዚሁ ሳምንት ነው። ይህ ጉዳይ ከዜግነት ጥያቄውና አፈታቱ ባሻገር፤ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚታይበት የሕግ የበላይነትም የሚፈተንበት ይኾናል ወደሚል እየሔደ ሲሆን፣ ኦፌኮም ጥያቄም እንዲነሣበት በማድረግ ውስብስብ ያሉ ነገሮች ጐልተው የታዩበት ነው። ምርጫ ቦርድ እፈልገዋለሁ ያለው ማብራሪያ ደግሞ እንዲሠጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው።

ጅማና የአካባቢው ነዋሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት በተከታታይ አደባባይ ወጥተው ለዶክተር ዐቢይ ድጋፋቸውን የሠጡበት ሰልፎች በተለየ የሚታይ ወቅታዊ ክስተት ነው። እንዲህ ላለው ሰልፍ መነሻው ደግሞ የኦፌኮ አመራሮች በተለይ አቶ ጃዋርና የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ወደ ጅማ ብቅ እንደሚሉ ከመሰማቱ ጋር የተያያዘ እንደኾነ ይጠቀሳል። በተለይ በጅማ ስታዲየም የተደረገው ዶክተር ዐቢይን አትንኩብን የሚልና እነ አቶ ጃዋርን የሚቃወሙ ድምፅ የተሰማበት ነበር። ይኸው የጅማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ያካሔዱት ተከታታይ ትዕይንተ ሕዝብ፤ ኦፌኮ በጅማ ሊያደርግ የነበረው ስብሰባ እንዲሰረዝ ምክንያት ሲሆን፣ በሳምንቱ ውስጥ በስፋት ያነጋገረ ነበር። እንደ ጅማ ሁሉ በአዳማም ተመሳሳይ ዓላማ ያለው የድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል።

ምርጫው ደረሰ በሚባልበት በዚህ ሰዓት ምርጫ ቦርድ ከውልደቱ ጀምሮ ይጠቀምበት የነበረውን የመለያ ዓርማውን ከዚህ በኋላ አልጠቀምበትም ብሎ በአዲስ መለዮ እንደሚቀርብ አሳውቆ፤ ወቅታዊ እኔነቴን የሚል ዓርማ ያለውን አዲስ ዓርማ ያስተዋወቀው በዚሁ ሳምንት ነው። ከዚህ ሌላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን የከለሰውና መጪውን ምርጫ በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የመከረበት ነው። እንዲህ ያሉ ሒደቶች ላይ ቦርዱ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ በምርጫውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አሁንም ጥርት ያለ ነገር ያለመኖሩን የሚጠቀሙ አስተያየቶች ግን፤ ከተለያዩ ወገኖች እየተሰማ ነው። በአነጋጋሪነታቸው ሲገለጹ የነበሩ የጥላቻ ንግግርና የኤክሳይዝ ታክስ አዋጆች የጸደቁትም በዚሁ ሳምንት ነው።

ከአንድ ሳምንት በፊት ከአስመራ የተሠራጨው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ቃለምልልስ አብዝቶ ኢትዮጵያን የሚመለከት ነበርና የብዙዎችን ዓይንና ጆሮ አግኝቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ የአቶ ኢሳይያስ መግለጫ ተከትሎ ከሕወሓት አካባቢ የተሠማው የመልስ ምት የሚመስል መግለጫ ጉዳዩ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል። ሕወሓት 45ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በትግራይ ክልል እያከበረ ሲሆን፤ የመዝረያ በዓሉን የካቲት 11 ያካሒዳል። ባልደራስ ስብሰባና ከአዲስ አበባ ወጥቶ በባህርዳር ያደረገው ውይይት ከሳምንቱ ዜናዎች የሚካተቱ ሲሆን፤ ኦነግ ወደ 400 አባሎቼ ታሰሩ ብሎ መግለጫ የሠጠበት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቡዳቢ ጉዞና ንግግር እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ያመቻቸው የተለያዩ ጉዳዮችና ለሁለት አሥርት ዓመታት ሲጠየቅ የነበረውን የኦርቶዶክስ የቤተክርስቲያን መገንቢያ ቦታ ማስፈቀዳቸው ጉዞዋቸው የተሳካ እንዲኾን ያስቻለ መኾኑ ተገልጿል። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከዚህ በኋላ ትዕግሥት አይኖረኝም የሚለው የዓቃቤ ሕግ መግለጫ ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሲሆን፤ በአንዳንዳቹ ላይ የተጠናከረውን ትንታኔና ምልከታ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የህዳሴ ግድብና የከሸፈው ድርድር ከዚያስ?

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብና በጥቅል የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ በየአገሮቹ የቡድን አለቆች እየተመሩ በጠረጴዛ ዙሪያ እየመከሩ መኾኑ መነገር የጀመረው ዛሬ አይደለም። የዓባይ ውሃ እነዚህን ሦስት አገሮች ብዙ አነጋግሯል። በየአገሮቻቸው ፍላጐት አንጻር ቃላት ተለዋውጠውበታል። ተለዋዋጭ አጀንዳዎች እየቀረቡለት ተፋጭተዋል። አንዱ ሌላውን አውግዟል። አንዴ ተስማሙ ሲባል በሌላው ወቅት ደግሞ ያለስምምነት ሲለያዩ ቆይተዋል።

የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ወዲህ ደግሞ በእነዚህ አገሮች መካከል ተደረጉ የሚባሉ ድርድሮች ቁጥር የበዛ ኾኗል። ይበልጡኑ ደግሞ ከጥቂት ወራት በወዲህ እነዚህ አገሮች በተወካይ ተደራዳሪዎቻቸውና በባለሙያዎቻቸው በኩል የሚደረጉት ውይይት በቀናት ልዩነት ሳይቀር ደጋግሞ በመገናኘት የሚካሔድ ሲሆን፣ ድርድሮቻቸውን ሦስተኛ ወገን እንዲያዳምጠው ጭምር ፈቅደው ሲነጋገሩ ከርመዋል።

የአገራቱ የድርድር አጀንዳዎች በብዙ ቴክኒካል ጉዳዮች የታጨቀ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየአገራቱ በዙር የሚደረግ ውይይትን ዋሽንግተን ድረስ እንዲሔድ ያደረገው የግድቡ የውኃ አሞላል እንዴት ይሁን የሚለው አጀንዳ ቀዳሚ ጉዳይ ከኾነ በኋላ ነበር። በዚህ ጉዳይ ግብጽ አጀንዳውን በተለያየ መንገድ እየለወጠች ድርድሩ ሥር እንዳይዝ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ዙሪያ የሚደረገው ምክክር ወደ አንድ ውጤት ያመራል ቢባልም፤ ባሳለፍነው ሳምንት የተሰማው ዜና ግን አገራቱ የወራት አታካች ድርድሮች ውጤት አልባ መኾኑ፤ ከዚህስ በኋላ የሚለውን ጥያቄ አስነስቷል።

የዋሽንግተኑ ውይይት ያለውጤት መበተኑ ደግሞ እነዚህ አገራት እንደገና ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለማድረግ ከባድ ሊያደርገው ቢችልም፤ በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመገመት ቢከብድም፤ አንዳንድ መረጃዎች አሜሪካ ሌላ ሐሳብ ይዛ ለመቅረብና ድርድሩን እንዲቀጥል ትሻለች እየተባለ ነው።

አገራቱ በዋሽንግተን ለቀናት ያደረጉት ድርድር ውጤት ያሳየበት ዋነኛ ምክንያት እስካሁን በዝርዝር ያልወጣ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ሰነድ ላለመፈረም ተገዳለች። ብዙዎች ይህ ቀድሞ የተሰናዳ ሰነድ ኢትዮጵያን እንደሚጐዳ እየገለጹ ነበር። የኢትዮጵያ አቋም ግን ግልጽ ነው። በሕግ ማዕቀፉ ላይ በሚደረገው ድርድር ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያን የሚጐዳ ስምምነት እንደማይፈረም ሲገለጽ ነበርና፤ ባሳለፍነው ሳምንትም ድርድር እንዳልተሳካ ከተገለጸ በኋላ የተሠጠው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋምም ይህንኑ አንጸባርቋል። በተለይ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ይፋዊ መግለጫ የተሠጠው ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የድርድሩን መክሸፍ አስመልክቶ የሠጡት ማብራሪያ፤ በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ቢኖር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሠጥና መርኅ ላይ የተመሠረተ ጥቅሟን ያስጠበቀ ድርድር የምታራምድ መኾኑን ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሠጥ መታወቅ እንደሚኖርበት አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በዋሽንግተን በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲካሔድ የነበረው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁ ግን የሚያሳስብ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። የህዳሴውን ግድብ በተለከተ አሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ መግባታቸውና አዝማሚያቸው ከኢትዮጵያ ፍላጐት ጋር በተቃራኒ ሊኾን ከቻለ ኢትዮጵያን ሊፈትናት ይችላል የሚል ሥጋት ማሳደሩ አልቀረም። (ኢዛ)

ጠቅላይ ሚኒስትሩና የድጋፍ ሰልፎች

ባሳለፍነው ሳምንት በተለየ ከታዩ ክስተቶች ውስጥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለመደገፍ በተለያዩ ከተሞች የተካሔዱ ትዕይንተ ሕዝቦች ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ የእርሳቸው ትውልድ ቦታ እንደኾነ በሚጠቀሰው በጅማና በአካባቢዋ የተደረጉት ትዕይንተ ሕዝቦች ለአንድ ቀን ብቻ የተካሔዱ ሳይሆን፤ በሳምንቱ ውስጥ ለተከታታይ ቀናት የተካሔዱ ነበሩ። በተለይ የካቲት 6 ቀን 2012 የተደረገው ሕዝብ በነቂስ የወጣበትና በከተማዋ ስቴዲየም የተካሔደ ነበር።

በብዙዎች ዘንድ እንደታመነውና ከሰላማዊ ሰልፉ መሪ መፈክሮች መገንዘብ እንደተቻለው የትዕይንተ ሕዝቡ መነሻ አቶ ጃዋር መሐመድ ወደ ጅማ ይመጣል፣ ፕሮፌሰር መረራም በተገኙበት ኦፌኮ ስብሰባ ያደርጋል የሚለው ዜና ከተሠራጨ በኋላ፤ የእነርሱን ወደ ጅማ መምጣት ለመቃወም ዓላማ ያለው መኾኑ አንዱ ምክንያት ነው። በዋናነት ግን ሰልፉ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለመደገፍና ከእርሳቸው አመራር ጋር መኾናቸውን የገለጹበት ነበር። “ከዐቢይ ውጭ ወደ ውጭ” የሚሉና ሌሎችም ድምፆች የተሰሙበት ነው። ብልጽግና ለኢትዮጵያ መፍትሔ መኾኑን ያመላከቱበት ሲሆን፣ እነ አቶ ጃዋርን የሚቃወሙበትን የተለያዩ መፈክሮች ያሰሙበት ነበር። እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ከታየ በኋላ አቶ ጃዋርና ፕሮፌሰር መረራ በጅማ ሊያደርጉ የነበረውን ስብሰባ እንዲሰርዙ አድርጓል።

ይህ ትዕይንተ ሕዝብ በሌላ መንገድ በአዳማ የተደገመ ሲሆን፤ የዶክተር ዐቢይ ምስል ያለበትን ቲሸርት በመልበስ ጭምር በስፖርታዊ እንቅስቃሴ የታጀበ ድጋፍ ተደርጓል።

በጥቅል ሲታይ በጅማም ኾነ በአዳማ የተካሔደው ትዕይንተ ሕዝብ ዶክተር ዐቢይንና እየተደረገ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ብሎም ብልጽግና ፓርቲን ለማበረታታት የተሰናዳ ስለመኾኑም ተገልጿል። የኦሮሞ ሕዝብ አቃፊና ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር ለዘመናት የኖረ በመኾኑ የጅማ ነዋሪዎች ከመንግሥት ጎን እንቆማለን ያሉበት ነበር። በድጋፍ ሰልፉ ላይ የጅማ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት ነበር።

ከጅማና ከአዳማ ሌላ በአጋሮ ከተማ ተመሳሳይ መልእክቶች የተላለፉበት ሰልፍ የተደረገ ሲሆን፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እሑድ የካቲት 8 ቀን ደግሞ ብልጽግና ፓርቲን ለመደገፍ በሱማሌ ክልልና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ሰልፎች ተካሒደዋል። (ኢዛ)

የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዞና ውጤት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ወዲህ ከአገር በመውጣት በተለያዩ ነገሮች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር መክረዋል። በተለይ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያካሔዷቸው የገጽ ለገጽ ውይይቶች የሚታወስ ሲሆን፤ በቅርቡም ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያውን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከተወካዮቻቸው ጋር ተነጋግረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ በማቅናት ለስብሰባ በተመረጠው የዱባይ ስቴዲየም ውስጥ ለኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል። በተለያየ መረሃ ግብር የተሰናዳው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዱባይ ፕሮግራም በመጀመሪያ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገሮች የተውጣጡ ወደ 250 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጋር በመገናኘት የተወያዩና ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሠጡበት ነበር። ሴቶችን ለብቻቸው ያነጋገሩበት ሌላው መድረክ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የዐረብ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በዱባይ ባረጉት ውይይት፣ የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት እየሠራ ያለውን የተለያዩ ሥራዎች የገለጹበት ነበር። በቀጥታ በአካባቢው ላሉ ኢትዮጵያውያን አሁን በውጭ የምትሠሩት ሥራ አንድ ቀን የሚለውንና አገራቸው ተለውጣ ይህ ታሪክ እንደሚቀር ተናግረዋል። እስከዚያው ድረስ ግን ጠንክረው እንዲሠሩ የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንም ጎታች ማንም ተጎታች ሳይሆን፤ ሁሉም በጋራ ከሠራ አገራችን መለወጥ እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በለውጥ ጐዳና ላይ ስለመኾንዋ ያተቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር ለመፍታት በትብብርና በጋራ መሥራት ስለሚያስፈልግ መደመር ያስፈልጋል ብለዋል። “ዛሬ ሁሉም ዜጋ በትብብር መሥራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ በመገኘታችን የዚህ ትውልድን ኃላፊነት ይጠይቃል” በማለትም በጋራ መሥራትና መተባበር ከተቻለ በቆራጥነት ከተንቀሳቀስን ሌሎች አገራት የደረሱበት መድረስ እንደሚቻልም አብራርተዋል።

መብታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ለማድረግ መንግሥት ከየአገራቱ መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጉን መግለጻቸው አንዱ ነው። መንግሥት እናንተ ስትከበሩ አገራችን እንደምትከበር ስለሚገነዘብ፣ መብታችሁንና ጥቅማችሁን ለማስከበር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል በማለት ቃል ገብተዋል።

ሌላው ብዙዎችን ያስደሰተውና ያስደመመው በዱባይ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የሚኾን ቤተክርስቲያን መገንባት የሚችሉበት ቦታ መፈቀዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቤተክርስቲያን መገንቢያ ቦታው እንዲፈቀድ ባደረገው ውይይት ከ15 ዓመት በላይ ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረጋቸውንና ይህንን ቦታ መረከባቸው የጉዟቸው ስኬት ከሚገለጽበት አንዱ ኾኗል። ለዚህም የተባበሩት ኤምሬቶችን አመስግነዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን 10 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ለማስቀጠር የሚያስችል ስምምነትም አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉት ውይይት ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች የቀረቡበት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። የሕግ የበላይነት ለምን አይከበርም የሚለው ጥያቄ አንዱ ነው።

ከጀኔራል አሳምነው ፅጌ ሞት ጋር ተያይዞ ለቀረበ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀኔራሉ ጋር የተያያዙ መረጃ የሠጡበትና እርሳቸውን አስገድለዋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም ጀኔራሉን ለማስፈታት የከፈሉትን መስዋእትነት ዘርዝረዋል። እንኳን እሳቸውን ሊያስገድሉ፤ እንዲያውም ጀኔራሉ እነዚያ የሞቱትን ሰዎች ይገላል ብለው ለሰኮንድ ተጠራጥረው እንደማያውቁ የገለጹት በተለየ የሚታይ ነው። (ኢዛ)

ምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ክለሳና ሰሞናዊ ክንውን

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ክንዋኔዎችን ይፋ ያደረገበት ነበር። አንዱና ዋነኛው የ2012ን አገር አቀፍ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መከለሱን አስታውቆ ይፋ አድርጓል። በተከለሰው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጫው ቀን ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ይኾናል።

ከዚህ ቀደም ወጥቶ በነበረው የጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጫ ቀን ተብሎ ተጠቅሶ የነበረው ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። በዚሁ በተከለሰው ፕሮግራም መሠረት ከዚህ ቀደም በጊዜያዊነት ተይዘው የነበሩ የጊዜ ሰሌዳ ክንውኖች የተወሰኑ መሸጋሸግ ተደርጐባቸዋል። ከዚህ ክንውን ባሻገር ቦርዱ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ ለውጧል።

ቦርዱ ዓርማውን የለወጠበት ዋና ምክንያት አሁን በለውጥ ላይ ያለውን የምርጫ ቦርድ ሊገልጽ የሚችል ዓርማ በማስፈለጉ ነው። ይህንንም ዓርማ በፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ ላይ ይፋ ተደርጓል። (ኢዛ)

ከዚህ በኋላ ዋ! ያለው መግለጫ

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት በእጅጉ ከሚተቹበት ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የሕግ የበላይነትን ማስከበር አልቻለም በሚል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሐሳቦች የተንሸራሸሩ ሲሆን፣ አሁን ሕግ ከማስከበር ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ትችቶች አልረገቡም። ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የወጣው መግለጫ በተለየ እንዲታይ አድርጐታል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ የበላይነት ማስከበር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልኾነ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተወሰዱ ስላሉት እርምጃዎች በማተትና ተወሰዱ ያላቸውን እርምጃዎችንም ጠቃቅሷል። በዋናነት ግን ለአገሪቱ ደኅንነትና ለሕዝቡ ሕልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም እንደያዘ ማመላከቱ፤ ሕግን በማስከበር ረገድ ጠንከር ያለ መግለጫ ተብሏል።

የሕግ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ጋር በተየያዘ በከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በጅምላ ጭፍጨፋና ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዚህ ድርጊት ተሳታፊ የኾኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ስለመደረጉ መግለጫው ያመክታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተበራከቱ የመጡ የወንጀል ተግባራት በተለይም በብሔር ወይም በክልሎች መካከል በግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጠር ግጭት መነሻነት ወንጀል የተፈጸመባቸው አካባቢዎች ዋና ዋና ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ የተደራጀ የምርመራና ክስ የመመሥረት ሒደት ላይ ስለመኾኑም ያሳወቀበት መግለጫ ነው።

መግለጫው በተለየ እንዲታይ የሚያደርገው ሌላው ደግሞ ወንጀሉ ተፈጸመባቸው ያላቸውን አካባቢዎች በስም ጭምር በመጥቀስ ማሳወቁ ነው።

የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊቶች መነሻ በማድረግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ስለመጀመሩ በማተት የሕግ የበላይነት እየሠራ ስለመኾኑ ያሳወቁበትም ነው።

በዚሁ መግለጫ ላይ በተጨማሪ ያመለከተው ሌላው ነጥብ ደግሞ “የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የፌደራል የፍትሕና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች እንዲሁም የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና የፍትሕና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ባካሔዱት አስቸኳይ ግምገማ ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ፣ በሃይማኖት ተቋማት ላይና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ሕዝቡን ይዞ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።” የሚል ይገኝበታል።

አያይዘውም “ከእንግዲህ ወዲህ ለአገራችን ደኅንነትና ለሕዝባችን ሕልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም ተይዟል።” ያለው መግለጫው፤ ከፍተኛ አመራሩ ባደረገው ግምገማ በየቦታው የሚፈጠሩ የወንጀል ድርጉቶች ዋነኛ ችግር የፖለቲካ አመራሮች እጅ ያለበት መኾኑን በሚገባ የተረዳ መኾኑን የሚጠቁም ነው። ይህን የማይገባ ተግባር ሲያስፈጽምና ሲፈጽም በዝምታ ሲያልፍ የነበረው አመራረ ከዚህ እንዲታረም ያሳሰቡት የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጫ በአገሪቱ በሚፈለገው መጠን የሕግ የበላይነት በማስከበር ዘንድ የነበረውን ፈተና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምንሻገረው እንደሚኾን እምነቱን ገልጿል። በመኾኑም “ሕገወጥ ተግባራትን የምንሸከምበት ጫንቃና በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ የማናቀርብበት ምንም ምክንያት የማይኖረን መኾኑን እንገልጻለን።” በሚል ማብራሪያ ከሠጠ በኋላ፤ ሕገወጦችን ያለምሕረት ለሕግ አቀርባለሁ ብሏል።

በመግለጫው ማጠቃለያም “ከወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የተጀመረው የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ለፍርድ የማቅረብ ሒደቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል፤ በዚህም የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ለድርድር አይቀረብም” ብሏል። በዚሁ መግለጫ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች የተሠጡ ሲሆን፤ ሕግን ከማስከበር አንፃር ጠንከር ብሎ የወጣ መግለጫ ነው ተብሏል። ነገር ግን ዋናው ነገር በተግባር መተግበሩ እንደኾነ ከተሠጡ አስተያየቶች መገንዘብ ተችሏል። (ኢዛ)

የሁለቱ አከራካሪ ሕጎች በፓርላማው መጽደቅ

በዚሁ ረቂቅ ላይ የነበሩ አንዳንድ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ሲሆን በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ አዲስ መኪኖች የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 ወደ 5 በመቶ እንዲጣልባቸው መደረጉ አንዱ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለቱ አነጋጋሪ በነበሩ ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል። በአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ፓርላማ ከሌሎች ረቂቅ አዋጆች በተለየ ብዙ ክርክርና ውይይት ተደርጐባቸው የጸደቁት እነዚህ ሁለት አዋጆች ውስጥ አዋጆች የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ሲሆን፤ ሌላኛው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ጋር የተገናኘው አዋጅ ነው።

በተለይ የኤክሳይዝ ታክሱ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት በተሠጠ ማብራሪያ ቀድሞ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ለረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የዋለ በመኾኑ፤ እንዲሁም የማምረቻ ወጪን መሠረት አድርጎ የሚሰላ በመኾኑ ግልጽነት የሚጎድለው በመኾኑ መሻሻሉ አስፈላጊ በመኾኑ የቀረበ መኾኑን ገልጿል።

ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደኅንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመኾኑ፤ ይህንን ከዚህ አዋጅ ጋር በማስተሳሰር ጥበቃ ለማድረግ መኾኑም ተብራርቷል። ከተወሰነ ዓመት በላይ ግልጋሎት የሠጡ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ፤ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በኾኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ በማስፈለጉም ነው ተብሏል።

ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ80 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲሁም፣ ከሁለት ዓመት እስከ አራት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ130 በመቶ ወደ 105 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበት ጸድቋል፤ ሌሎች ቅናሽ የተደረገባቸው ዘርፎች በዝርዝር ቀርበዋል።

ይህም በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀድሞ ከነበሩት ይዘቶች በርከት ያሉ ማሻሻያዎች የተደረጉበት መኾኑን ያሳየ ነው። በዚህ መሠረት የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁን በአራት ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ሊያጸድቀው ችሏል። በረቂቅ አዋጁ ይህንን አዋጅ በሚተላለፉት ላይ ያስቀመጠው ቅጣትም አለ አዋጁን የተላለፈ ከ3 - 5 ዓመት እስራት እንዲሁም ከ50 - 100 ሺሕ ብር ይቀጣል። (ኢዛ)

ሕገወጥ የመገናኛ መሣሪያዎች ተያዙ

በኢትዮጵያ ከሕገወጥ ተግባራት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ከምንሰማቸው ወንጀሎች መካከል በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጦር መሣሪያዎች በሕገወጥ መንገድ ስለመግባታቸው የሚያወሱ መረጃዎች ሲሰሙ ቆይተዋል።

እንዲህ ያለው ድርጊት የበለጠ አሳሳቢ እያደረገ የመጣው ሌላው ክስትት ደግሞ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ዕቃዎች ይዘት ከጦር መሣሪያ ጋር የተያያዙ የረቀቁ መሣሪያዎችና የቴሌኮም መሣሪያዎች መኾናቸው ነው። ከሰሞኑም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ይፋ ካደረገው መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ የመረጃና የመገናኛ መሣሪያዎች መያዛቸውን ነው።

እነዚህ የተያዙት መሣሪያዎች የቴሌኮም ማጭበርበር ለማከናወን የሚያስችሉ ሲሆን፣ ብዛታቸውም ስድስት ነው። “Sim box” የሚል መጠሪያ ያላቸው እነዚህ መሣሪያዎች፤ በሕገወጥ መንገድ ገብተው በቴሌኮም ማጭበርበር በሥራ ላይ ተሰማርተው ቢኾን ኖሮ፤ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ አገሪቱ ታጣ እንደነበርና ይህንን 68 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ኤጀንሲው አስታውቋል።

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ባለፉት ስድስት ወራት ከቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሣሪያዎች በተጨማሪ ለስለላ አገልግሎት የሚውሉ 60 ካሜራዎችን አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ተይዘዋል። (ኢዛ)

ለምርጫ ሒደት ችሎት

ባሳለፍነው ሳምንት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሊጠቀስ የሚችለው ዜና ከምርጫ ሒደትን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክርክሮች የሚዳኙበት ችሎቶች ሊደራጁ መኾኑ መሰማቱ ነው።

ይህንን ያስታወቀው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ከተሠራጨው መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው በአዋጅ ቁጥር 1162/2012 መሠረት ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉ የምርጫ ሒደት አከራካሪ ጉዳዮችን በዝርዝር ያስቀመጠ በመኾኑ፤ እነዚህን ዝርዝር ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ ፍርድ ቤቶች የምርጫ ጉዳዮችን የሚዳኙበት ችሎቶች ይቀናጃሉ። እነዚህን ችሎቶች ለማደራጀትም ከምርጫ ቦርዱ ጋር እየሠራ መኾኑ ተገልጿል።

በሚደራጁት ችሎቶች የሚታዩ ጉዳዮች መለየታቸውን የሚጠቁመው ይኸው መረጃ፤ በተጠቀሰው አዋጅ የሥነ ምግባር ጥሰት፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የድምፅ ቆጠራና ውጤት አገላለጽን፤ እንዲሁም ሌሎች ሊኖሩ የሚችሉ ምርጫን የተመለከቱ አከራካሪ ጉዳዮች ተዘርዝረው የተቀመጡ በመኾኑ፤ እነዚህ ችሎቶችም ይህንን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ናቸው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤቶችን የማደራጀትና በምርጫ የሚነሱ ክርክሮችን የሚያዩ ዳኞችን የመደልደል ሥራ ይሠራል ተብሏል። ይህም የመራጮች ምዝገባ ከመካሔዱ አንድ ወር በፊት በመፈጸም የምርጫ ሕጉ በሚያስቀምጠው አግባብ እንዲከናወን ለማድረግ ፍርድ ቤት ማከናወን ያለበትን ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ መኾኑም ተገልጿል። (ኢዛ)

አነጋጋሪው የኤርትራው ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ምልከታ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሠጡት ሰሞናዊ ቃለምልልስ በይበልጥ ኢትዮጵያን የሚመለከት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይና ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕወሓት እያደረገ ነው ያሉት ተግባር በቃለምልልሱ አንኳር ነጥቦች ነበሩ። የቃለምልልሳቸውም መክፈቻ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነበር። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተደረገ ካለው ለውጥ ጀምሮ ሐሳባቸውን ሠጥተዋል።

ይህ ቃለምልልስ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሠጡበት የነበረ ሲሆን፤ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ጉዳይና በዚሁ ጉዳይ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የተወሰነው ውሳኔ እስካሁን አለመተግበሩ እንደ አዲስ አጀንዳ መነጋገሪያ እንዲኾን ምክንያት ኾኗል።

አቶ ኢሳይያስም በሰሞኑ ቃለምልልስ ይህንን ጉዳይ አንስተዋል፤ ከሃያ ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረገውን ስምምነትና በሁለቱ አገሮች መካከል ለተፈጠረው መቀራረብ የዶ/ር ዐቢይ ሚናን በማወደስ የጀመረው ቃለምልልስ፤ ለሁለቱ አገሮች መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው።

በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥም ለአንድ ጠባብ ቡድን ውድቀት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መልካም እድል የፈጠረ አጋጣሚ እንደኾነም ያወሱበት ነው። ይህም ሰላምና ፍቅርን ለሁለቱ አገሮች አምጥቷልም ብለዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት እንዲህ ባለ መልኩ የገለጹት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ የባድመ ጉዳይ ግን በከፋ ሁኔታ ላይ ስለመኾኑ አመልክተዋል። ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት እንደኾነ የሚጠቀሰው የባድመ ጉዳይ አሁን የከፋ ሁኔታ ላይ የመገኘቱ ምክንያት ደግሞ፤ እርሳቸው የወደቀ ያሉት ቡድን ወይም ሕወሓትን ነው። ከገለጻቸው የተወረረው የኤርትራ ነፃ መሬት መመለስ እንደነበር ያመለከቱት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ፤ ይህ ግን ሊሆን አለመቻሉንና ለዚህም ምክንያቱ ሕወሓት ነው በማለት ስለሁኔታው ገልጸዋል።

“ድንበሩንና የባድመን ጉዳይ በተመለከተ ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደረገው ሕወሓት በፈጠረው ችግር ነው። አንድ ነጥብ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ደግሞ የከፋ ኾኗል።” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአቶ ኢሳይያስ ሰሞናዊ ቃለምልልስ ወደኋላ የነበረውን የኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ቀረጻንም የተመለከተ አስተያየት የያዘም ነበር። እንደ እርሳቸው ገለጻ በኢትዮጵያ የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት ሌሎች ከማየታቸው በፊት እርሳቸው ቀድመው እጃቸው ስለመግባቱና በተደጋጋሚ ከተመለከቱት በኋላ አስተያየት እንዲሠጡበት ተጠይቀው፤ በወቅቱ በሕገመንግሥቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት መሥጠታቸውንም ተናግረዋል።

በወቅቱ የተቀረጸው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚከፋፍል እንሚይኾን አስጠንቅቀው እንደነበረ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህ አቋማቸው በቃለምልልሱ ያነሱት ነጥብ በራስ መብት ሽፋን ኢትዮጵያንን በጐሣና በጐጥ የሚለያይ እንደኾነ ይገልጻሉ።

አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በዚህ ቃለምልልሳቸው ኢትዮጵያን በተመለከተ አስተያየት የሠጡበት ጉዳይ ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታደረገውን ምርጫ ነው። በፕሬዚዳንቱ እሳቤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ብርቱ ችግር ውስጥ ስለመኾኗ በመጥቀስ፤ በተለይ በዚህ ዓመት የሚካሔደው የኢትዮጵያ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሔዱ እንደ ግዴታ መወሰድ የሌለበት መኾኑን የሚያመለክት ሐሳባቸውን አንጸባርቀዋል። እርሳቸው ደጋግመው የወደቀው ኃይል የሚሉት ሕወሓት፤ አሁን በአገሪቱ ውስጥ እየታዩ ላሉ የብሔር ግጭቶችና ሌሎች ችግሮች መነሻ እንደኾነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሁኔታ መስቀለኛ መንገድ ላይ ስለመኾኑም የጠቀሱ ሲሆን፣ በኤርትራ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች መነሻቸው ኢትዮጵያ ስለኾነች የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል ማለታቸውን ቃለምልልሱን በመተርጐም ካሠራጩ ሚዲያዎች ለመገንዘብ ተችሏል። እንዲህ ዐይነት ይዘት የነበረውን የፕሬዝዳንቱ ቃለምልልስ ተከትሎ፤ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ምላሽ ስለመኾኑ የተነገረለትን መግለጫ ሠጥተዋል።

የድንበርና ተያያዥ በኾኑ ጉዳዮች ላይ በመግለጫቸው ከጠቀሱት ውስጥ፤ የትግራይ ክልል መንግሥትና ሕወሓት ከኤርትራ ጋር ባለው የድንበርና ተያያዥ ጉዳዮች ሕግና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ እንዲፈታ እንደሚሹ ነው።

የድንበር ጉዳዮች በፌዴራል መንግሥት የሚፈጸሙ መኾናቸውን፤ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ንግግር እንዲደረግና ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲፈጸም የሚሹ መኾኑ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ለመቋጨት እየተደረገ ያለ ጥረት ያለመኖሩን ዶክተር ደብረጽዮን አክለው ገልጸዋል።

የወሰን ችግሮችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ሕግጋቶች አሉ የሚሉት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ይህንን ለማድረግ መቀራረብ የሚያስፈልግ ስለመኾኑና ሳይቀራረቡ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አይችልም በማለት ገልጸዋል። ሁኔታውን በአግባቡ ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የኤርትራ ፕሬዝዳንትና የሕወሓት ሊቀመንበር የሠጡት አስተያየቶች ምንም ቢሆን የችግሩ ምንጮች እነርሱ እንደነበሩ፤ አሁንም ይህንኑ ጉዳይ በማንሣት መመላለሳቸውን የተመለከቱ አስተያየቶች ግን በተለያዩ የምልከታ ማዕዘኖች እየቀረቡ ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ