Ethiopia Zare's weekly news digest, week 20, 2012 Ethiopian calendar

ከጥር 11 - 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥር 11 - 17 ቀን 2012 ዓ.ም.):- ባሳለፍነው ሳምንት አነጋጋሪና ባልተለመደ ሁኔታ መግለጫ ጭምር የወጣበት ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ትእዛዝ የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነታቸው መነሳትና በቦታቸው አዲስ ሚኒስትር ከመተካት ጋር ተያይዞ የተከተለው እሰጥ አገባ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወ/ሮ ፈትለወርቅን ከኃላፊነታቸው ማንሳታቸውና በሌላ እንዲተኩ የማድረግ ሥልጣን ያላቸው ቢኾንም፤ ይህ እርምጃቸው በሕወሓት ተቃውሞ ያስነሣ ኾኗል። ተቃውሞው ደግሞ በመግለጫ ጭምር የተደገፈ ነበር። በዚህ መግለጫው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሕወሓት አባላት ከፌዴራል መንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ኾን ተብሎ እንዲነሱ የማድረጉ ተግባር ተገቢ እንዳልኾነ የሚጠቁም ነው።

ከአዲስ አበባ አስተዳደርም ተመሳሳይ እርምጃ በመወሰዱ ሕወሓት መግለጫ በማውጣት ኾን ተብሎ የሚሠራ ሥራ ነው በሚል ድርጊቱን ተቃውሟል። የሰሞኑ ሹምሽር አሁንም በሕወሓትና በሚዲያዎቹ ቀዳሚ ዜና በመኾን እየተራገበ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባላቸው ሥልጣን ሹምሽር አድርገዋል። ይህ አንድን ወገን የማግለል አይደለም በሚል የሚገልጹም አሉ። እንዲያውም እርምጃው አግባብ መኾኑንና ሕወሓትም ቢኾን ለተቃውሞ የሚያበቃ ምክንያት የለውም የሚሉም አሉ። ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል አሻፈረኝ ያለ ቡድን አባሎቼ ከሥልጣን ወረዱ ብሎ ለመናገር እንዴት ይችላል? ብለው ይሞግታሉ። ከሕወሓት በኩል ግን የሹም ሽሩ ሕግን ያልተከተለ ነው እያሉ ነው።

ከዚህ ሰሞናዊ ጉዳይ ባሻገር ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው ዜና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮምሽን የስድስት ወር ክዋኔውን በአዲሱ የኮምሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መቅረቡ ነው። ሪፖርቱ በፓርላማ ውስጥ ከወትሮ የተለየ አስተያየት የተሠጠበት ነበር። የፓርላማ አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡበት ከመኾኑም በላይ፤ ሪፖርቱ በአገሪቱ አሁን ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊካተቱ የሚገባቸው ጉዳዮች ስላሉ ይህ ተሟልቶ ይቅረብ ያሉበትም መድረክ ነበር።

ሌላው ተጠቃሽ ዜና መታገታቸው ከተሰማ ወደ ሁለት ወር የተጠጋቸው የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም እንቆቅልሽ እንደኾነ መቀጠሉና፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጀመሩበት ነበር ማለት ይቻላል። በተማሪዎቹ ጉዳይ ይነገረን የሚል ግፊት ጐልቶ የወጣበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይትና በዚህ ውይይት ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡትም በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በመድረኩ ላይ በተለይ ክልል እንሁን ከሚሉ ጥያቄዎች ጀምሮ ሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቀረቡበት ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ ነበር።

አራት ፓርቲዎች ጊዜያዊ ምዝገባ ማግኘታቸው፣ ጥምቀት በዓል አከባበርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የነበሩ የተለያዩ ክስተቶች፣ ካሳለፍነው ሳምንት የሚጠቀሱ ዜናዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲሱ ሹመት የመሥጠቱም ከሳምንቱ ዜናዎች የሚካተት ነው።

በ2012 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ክንውናቸውን የተለያዩ ተቋማት እያቀረቡ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት ሪፖርታቸውን ካቀረቡት መካከል የተወሰኑትን የምንመለከትበትና በሌሎች ሳምንታዊ ዘገባዎች ላይ የተጠናከረው ዘገባ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ያልተለመደ ድምፅ የተሰማበት ሹም ሽር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለካቢኔ አባላቶቻቸው የተለያዩ ሹመቶችን ሠጥተዋል። ሽረዋል። በፍቃዳቸው የለቀቁትን እንደ ዶ/ር አሚን አማን ያሉትንም አመስግነው ሸኝተዋል። እንዲህ ባለው ሒደት ወደ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ቀርተውታል።

ሰሞኑንም ለሦስት ሚኒስትሮች ሹመት ሠጥተዋል። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ከሠጡት ሹምሽር ጋር ተያይዞ ያልተለመደ ነው የሚባል ድምፅ ተሰምቷል። ከሦስቱ ሚኒስትሮች ሹመት በኋላ በመግለጫ ጭምር ተቃውሞ የቀረበበት የመኾኑ ጉዳይ ሁኔታውን የተለየ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመታቸው እስካሁን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩትን ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትን ዶ/ር አብረሃም በላይ ደግሞ የኢኖቤሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በማድረግ ካቢኔያቸውን እንዲቀላቀሉ አድርገዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በመኾን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ አባል በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ ከሚኒስትርነታቸው ተነስተው በምትካቸው፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ መላኩ አለበል ተሹመዋል።

እንዲህ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሹመት አሠጣጥ የተለመደ ቢሆንም፤ ከወትሮው የተለየ ያደገውና በመግለጫ ጭምር የተቃውሞ ድምፅ እንዲሰማ ያደረገው የወይዘሮ ፈትለወርቅ ከሚኒስትርነታቸው መነሳት ነው። የተቃውሞ መግለጫ ያወጣው ደግሞ ከብልጽግና ጋር አልሠራም ብሎ በይፋ ያስታወቀው ሕወሓት ነው።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር የኾኑት የወይዘሮ ፈትለወርቅ ከሚኒስትርነታቸው መነሳት ለሕወሓት ተቃውሞው መግለጫ መነሻ ቢሆንም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላው የሕወሓት አባል የሆኑትና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔም ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ መደረግ የሕወሓትን ተቃውሞ ድምፅ ከፍ አድርጐታል። በክልሉ ሚዲያዎችም ይኸው ጉዳይ በሰፊው እየተስተጋባ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ የሕወሓት አባላት ያለአግባብ ከኃላፊነት እየተነሱ ነው በሚል ሕወሓት ድርጊቱን አውግዟል።

የእነዚህ ሁለት የሕወሓት አባላት ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ሥልጣን መነሳትን ተከትሎ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ፤ ድርጊቱ ሕገወጥና ፀረ ዲሞክራሲ መኾኑን በመግለጽ በፓርቲ ደረጃ በያዝነው መስመር እንለያይ እንጂ በሕገመንግሥታችን የተቀመጠውን የፌዴራልና የክልል መንግሥት ግዴታና መብት አክብሮ እየሔድ መኾኑን በግልጽ ማስታወቁን ያስታውሳል። የሕወሓት መግለጫ አያይዞም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግ ድርጅቶችን ነው የመረጠው በማለት በአሁኑ ወቅት የሕወሓት አመራሮችና አባላት በመኾናቸው ብቻ ከፌዴራል መንግሥትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ኃላፊነታቸው መነሣት በፍጹም ተቀባይነት የለም በሚል ገልጿል። እንዲታረምም ጠይቋል። በመግለጫው ማሳረጊያም ይህ ካልኾነ ግን ይህንን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ ኃላፊነቱን የድርጊቱ ፈጻሚ ይወስዳል በሚል አመልክቷል።

በተመሳሳይ ዶክተር ሰለሞን ኪዳን ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በተለይ ለቢቢሲ በሠጡት ቃለምልልስ በእርሳቸውና በሌሎች የሕወሓት አባላት ላይ ተወሰደ ያሉትን እርምጃ ተቃውመዋል።

ይህንንም "አዲስ አበባ ላይ እንደ ኢሕአዴግ ነው የተወዳደርነው። ኢሕአዴግ እስካሸነፈ ድረስ ሕወሓት 25 በመቶ ቦታ አለው። እኩል የማስተዳደር ሥልጣን አለው። ይህንን አሠራር ማፍረስ ማለት የከተማውን መንግሥታዊ አስተዳደር መዋቅር ማፍረስ ማለት ነው" በማለትም እርምጃው ሕግና ሥርዓትን የተላለፈ ነው" ማለታቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

"ይሄ የፖለቲካ ሥልጣን ነው። ሕዝቡ ሕወሓትንና ፕሮግራሙን ነው የመረጠው። ሕወሓትን ሊወክሉ የሚችሉ ሰዎችን ሕወሓት ራሱ ብቻ ነው ሊያቀርብ የሚችለው። በስመ የትግራይ ተወላጆች መተካት አይቻልም። ይሄ አካሔድ ሕገ-ወጥ ነው። የብሔር ተዋጽኦ ነው ያስመሰሉት" በማለት ሒደቱን ስለመቃማቸው ተጠቅሷል። ሌሎች የትግራይ ክልል የሥራ ኃላፊዎችም ተመሳሳይ አስተያየት እየሠጡ ነው።

በእርግጥ ሕወሓት እንዲህ ያለውን መግለጫ ማውጣትና ኃላፊዎችም በዚህ ደረጃ ለምን ከኃላፊነት ይነሳሉ ማለት ነበረባቸው ወይ? ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ የብልጽግና ፓርቲን ባለመቀላቀሉ የእርሱ ተወካዮችን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ይዞ ለመቀጠል መፈለጉ ለምን? የሚሉትን ጥያቄዎችና ሌሎች ከዚሁ ጋር እንደመከራከሪያ በሚቀርቡ ነጥቦች ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሠጡ ይገኛሉ።

በተለይ በሕወሓት መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እርምጃ ትግራይን ከማግለል ጋር የሚያያይዙ ወገኖች እንደመኖራቸው ሁሉ፤ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ዙሪያ አስተያየት የሠጡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ ትግራይን ከማግለለ ጋር በፍጹም የማይገናኝ መኾኑን ነው። ራሱን ያገለለ ድርጅት እንዲህ ያለ ጥያቄ ማቅረብ እንዳልነበረበትም እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ። እንዲያውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ መዘግየቱን የሚናገሩም አሉ።

ዋናው ነገር ግን አግላይ ሥራ አልተሠራም የሚሉ በምሳሌ የሚያቀርቡት፤ ከሕወሓት የተወከሉት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ቢነሱም ሌላው የሕወሓት አባል ሚኒስትር ኾነው በካቢኔያቸው እንዲካተቱ ማድረጋቸው ሕወሓት በመግለጫው እንዳመለከተው አለመኾኑን ያመላክታሉ።

ሌላው በዚህ ዙሪያ አስተያየት የሚሠጡ ወገኖች በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከፍተኛ መኮንኖች ሹመት ሲያሠጡ 65 ከሚኾኑት ተሿሚዎች ውስጥ 13ቱ ከትግራይ ክልል መኾናቸው በራሱ ማዕከላዊው መንግሥት አግላይ አሠራር እየተከተለ እንዳልኾነ በመጥቀስ መግለጫው ለፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያነት ለማዋል የተፈለገ ነውም ይላሉ።

ከሰሞኑ ሹም ሽር ጋር ተያይዞ ለወጣው መግለጫና እየተራገቡ ባሉ አስተያየቶች መልስ ለመሥጠት ያለመ የሚመስል አጭር መግለጫ ከጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ወጥቷል። ይህም መግለጫ የከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ምደባ ከብሔርና ከማግለል ጋር እንደማይገናኝ አስታውቋል። ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ በሚኒስትር ደረጃ ሽግሽግና አዳዲስ ሹመቶችን የመሥጠት ሥራ መካሔዱን ያስታወሰው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መግለጫ፤ ይህም የተለመደና ለሥራ ቅልጥፍና የተሻለ አፈጻጸም ለማረጋገጥ ሲባል በየጊዜው የሚከናወን ሥራ ነው ብሏል።

"የአሁኑም እንደተለመደው መንግሥት የሥራ አፈጻጸምን፤ ብቃትንና ሲታዩ የነበሩ ጉድለቶችን ማረም፤ እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም ጉድለት ያለባቸውን በሌላ መተካትን መሠረት ያደረገ ሽግሽግ አድርገዋል፤ አዳዲስ ሹመቶችንም ሠጥቷል።" በማለት መግለጫው አመልክቷል። የመግለጫው ማጠቃለያም፤ "በመኾኑም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድን ብሔር ለማግለልና ከሥራ ለማፈናቀል የተደረገ አድርጎ የሚያቀርቡ አካላት ዓለማቸው ለነገሮች የተሳሳተ ትርጓሜ በመሥጠት ሕዝብን ማደናገር መኾኑን ማስገንዘብ እንፈልጋለን" በማለት በተሠጠው ሹመት ላይ የተስተጋቡ አስተያየቶች አግባብ አለመኾናቸውን አመልክቷል። (ኢዛ)

የሰብዓዊ ኮሚሽን ሪፖርት

ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት ጉዳይ በመኾን ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት የሚመለከተው ሪፖርት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደሥልጣን ከመጡ ወዲህ የሰብዓዊ መብት ፈተና የገጠመው መኾኑን የሚያሳየውን ሪፖርት ያቀረበው ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርታቸው ከሰብዓዊ መብት አያያዝና ጥሰት ጋር በአገሪቱ ተከሰቱ ያሉዋቸውን ጉዳዮች ከመዳሰስ ሌላ እርሳቸው ወደዚህ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ያቀረቡበት ነበር።
የቀረበውን ሪፖርት አስመልክቶ ኮምሽኑ በሠጠው መግለጫ ላይ በዋነኝነት ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና ለማደራጀት እየተወሰዱ ስላሉት የሽግግር ወቅት የለውጥ እርምጃዎችና የአፈጻጸም ስልቶች ለምክር ቤቱ አስረድቷል። በተለይም የተቋሙን የአቅም ውስንነት ለማሻሻል፣ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችና ተግዳሮቶችን ለማስወገድ እየተዘጋጀ ስለሚገኘው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ፣ ስለ አዲስ ኮሚሽነሮች አመራረጥ፣ እንዲሁም የኮሚሽኑ የበጀት፣ ፋይናንስና የሰው ሀብት አስተዳደር ነፃነት አስፈላጊነት ተገልጿል።

በሌላ በኩል ስለ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታና ሥጋት በአሁኑ ወቅት የተሟላ ሪፖርት ለማቅረብ ባይቻልም ዋና ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው የተያዩ ጉዳዮችን ማቅረባቸውን ጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች ስለመገኘቱ የሚያትተው ይህ መግለጫ፤ በሌላ በኩል የለውጥ ሒደቱ የገጠሙት ውስብስብ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች የሰብዓዊ መብት ቀውስ ስለመፍጠሩ ጠቅሷል። በብሔር ማንነትና አልፎ አልፎም በሃይማኖት መስመር የተካረረ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የአመጽ ግጭት እየቀሰቀሰ በከተማም በገጠርም፣ በጐዳናም በመንደርም፣ በሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ዜጐች በአሰቃቂና አስነዋሪ መንገድ ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከመኖሪያቸው፣ ከሥራቸው፣ ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል በማለት ተገልጿል።

ከዚህም ሌላ እጅግ ብዙ የሕዝብና የአገር ንብረት ስለመውደሙ በኮምሽኑ ሪፖርት ላይ መጠቀሱንና ቀውሱ መሣሪያ የታጠቁ ቡድኖች ሰዎችን በኃይል እስከማገትና መግደል የደረሰ እንደኾነ የሚያሳይ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች፣ የውጭ አገር ዜጎች፣ ወንድና ሴት፣ ወጣት ተማሪዎችና ሕፃናት ሳይቀሩ የዚህ ሰለባ እንደኾኑ የኮምሽኑ ሪፖርት አመላክቷል። "የዚህ ሁኔታ የስር ምክንያት የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን በመኾናቸው፣ በመንግሥትና ይህ ምክር ቤትም በተለይ ለፖለቲካዊ ችግሮች በአገርና ሕዝብ የሰላም ፍላጎት እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሠረተ አገራዊ መፍትሔ መሻቱን ልዩ ትኩረት ሠጥቶ ጥረቱን ሊቀጥል ያስፈልጋል" ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላው የምርመራ ሥራ የአጥፊዎችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስታውቋል።

የአመጽ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ችግሩ እንዳይባባስ በመከላከልና አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት መልሶ በማስፈን በተለይ የፌዴራል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሕይወት መስዋእትነት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን በሪፖርታቸው ተመልክቷል። በሌላ በኩል ግን አንዳንድ አካባቢዎች በፌዴራልም ኾነ በክልል የጸጥታ ኃይሎች የጸጥታ ማስከበር ሒደት ውስጥ ዜጐች ከሕግ ውጭ ለሞት፣ ለእስርና እንግልት የተዳረጉበት ሁኔታም በመኖሩ፤ የሕግና ሥርዓት ማስከበር ከፍተኛ አስፈላጊነት የመኖሩን ያህል፤ የሕጋዊነትና የሰብዓዊ መብት መርኅ መተግበር አስፈላጊነት ተብራርቷል።

ዶ/ር ዳንኤል በፓርላማ ቀርበው ካቀረቡት ሪፖርታቸው ውስጥ በአጽንኦት ሊታዩ ከሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች መካከል ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች በመንግሥት ሳይሆን የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባላቸው ቡድኖች መኾኑን ነው። በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መነሻቸው መንግሥት ሳይሆን፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች መኾናቸውንና በአገሪቱ ለሚስተዋሉ አመጽና ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቶች ስለመኾናቸውም ሳያመላክቱ አላለፉም።

ከዚህ ቀደም ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይካሔድ የነበረው በፖሊስና በጸጥታ ኃይሎች እንደነበር የሚያስታውሰው የኮምሽነሩ ማብራሪያ፤ ይሁንና አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠው የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ምክንያት ኾኖ መገኘቱን ሳያመላክት አላለፈም።

ይህ ሪፖርት ተከሰቱ ካላቸው ሁኔታዎች አንፃር የመፍትሔ ሐሳብ ብሎ ያስቀጠባቸውን ነጥቦችም የጠቆመበት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ከፖለቲካ ተሳትፎ መብት ጋር ተያያዥ የኾኑት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ መወሰድ ይኖርባቸዋል ያላቸው አንዱ ነጥብ ነው። ይህንንም ሐሳብን "በነፃነት የመግለጽ መብት በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ከዋና ከተማችን አንስቶ በክልሎችም ውስጥ አልፎ አልፎ አለአግባብ የማደናቀፍ ሁኔታ ስለተከሰተ፤ የፌዴራልም ኾነ የክልል መንግሥት ኃላፊዎች ይህን አዝማሚያ አጥብቀው ሊከላከሉና ችግር ሲከሰትም ፈጣን መፍትሔ እንዲሠጡ ያስፈልጋል" በማለት ገልጾታል።

በአንፃሩ ኃላፊነት የጎደለው የመደበኛም ሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የጥፋት መሣሪያም ሊሆን ስለሚችልና አሳሳቢ ምልክቶችም በመታየታቸው የሚዲያ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘጋቢዎችና ፀሐፊዎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ እንደሚያስፈልግ በመግለጫው አስፍሯል።

በሌላ በኩል አገራችን አሁን ከምትገኝበት ልዩ የሽግግር ሁኔታ አንፃር ሰላምንና ደኅንነትን ማስፈን የሁሉንም ወገኖች ድርሻ ስለሚጠይቅ፤ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጐች ኃላፊነት ስለኾነ፤ በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ትልቅ ሚናና ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክቷል። ስለዚህም የአመጽ ተግባሮችን በግልጽ በማውገዝና ደጋፊቻቸውን ወደ ኹከትና ብጥብጥ ከሚገፋፋ ተግባርና ንግግር ተቆጥበው በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ እንደሚያስፈልግም ከዚሁ ሪፖርት መቅረብ ጋር ተያይዞ የወጣው የኮምሽኑ መግለጫ አስታውቋል።

ኮምሽነሩ ሪፖርታቸውን ካሰሙ በኋላ ከፓርላማው ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ሠጥተዋል። ባለ 11 ገጹ ሪፖርት ፓርላማውን ከወትሮ ለየት ያለ የሐሳብ ፍጭት የታየበት አድርጐታል። በተለይ አንድ የፓርላማ አባል በአዲሱ ኮምሽነር የቀረበው ሪፖርት በ11 ገጽ መገደብ አልነበረበትም። የቀደመው ኮምሽን ያቀረበው ሪፖርት 50 ገጽ የነበረና የተሻለ ነበር የሚል አስተያየት የተደመጠበት ነበር። በሌላ የፓርላማ አባል ደግሞ የአሁኑንና የቀድሞውን ኮምሽነር በንጽጽር ማቅረብ አይቻልም ብለው ሞግተዋል። ሪፖርት በገጽ ብዛት ማበላለጥ እንደማይቻል በመግለጽ፤ የፓርላማ አባልዋን ሐሳብ ተቃውመዋል። ሌሎች ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ኮሚሽነሩ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሠጥተዋል። በሌላ በኩል ግን ኮምሽኑ ያቀረበው የስድስት ወር የአፈፃፀም ሪፖርት፤ አሁን አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር ማካተት የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዮችም እንደነበሩ በማስታወስ፤ ሪፖርቱ እነዚህ ጎደሉ ያላቸውን ጉዳዮች አካትቶ ይቅረብም ተብሏል። (ኢዛ)

ጊዜያዊ ምዝገባና እውቅና

ከሰሞኑ ዜናዎች ለአራት የፖለቲካ ድርጅቶች የእውቅና ሠርተፍኬትና ጊዜያዊ ምዝገባ ፍቃድ መሠጠቱ ተጠቃሽ ነው። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ እውቅና ከሠጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል በጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ ይመራል የተባለው "ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ" አንዱ ነው።

ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ከባልደራስ ሌላ የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ ምዝገባ ፍቃድ የተሠጣቸው ሦስቱ ፓርቲዎች “አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ”፣ “አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ”ና “እናት ፓርቲ” የሚል መጠሪያ ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመለክተው እንዲህ ዐይነቱ ፍቃድ የሚቆየው ለሦስት ወራት ብቻ ነው። ይህ ጊዜያዊ ፍቃድ መሠጠቱ ከተለገጸ በኋላ በአቶ እስክንድር ነጋ የተባለው የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች መግለጫ ሠጥተው ነበር። በመግለጫቸው ፓርቲው ለመሥራት ያቀዳቸውን ሥራዎች የጠቆሙ ሲሆን፣ ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመጣመር የመሥራት እቅድ ያለው መኾኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ፓርቲው ከማን ጋር ለመሥራት እንዳሰቡ በመግለጫቸው ላይ አልተጠቀሰም። (ኢዛ)

የደቡብ ጥያቄና ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ክልል ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዚህ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ጉዳይ በአንድ ጀንበር መልስ መሥጠት አዳጋች ስለመኾኑ ያስገነዘቡበት ነበር። በተለይ በደቡብ ክልል መዋቅር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ከሕብረተሰቡ ጋር ሰፊና የሰከነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም በሠጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል።

በዚህ ውይይት ላይ በአብዛኛው የቀረበው የክልል፣ የወረዳና የዞን ጥያቄዎች ሲሆኑ፤ ሌሎች መሠረተ ልማትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይ ወረዳ ዞን እንሁን፣ የሚለው ጥያቄ ላይ የደቡብ አካባቢ ሕዝቦች ከ20 ዓመታት በላይ አንድ ክልል በመኾን በአንድነት መኖራቸውንና ክፉና ደጉን በጋራ ያሳለፉ የኢትዮጵያ ምሳሌ ተደርገው የሚታዩ መኾኑን በማስታወስ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ተወስኗል፤ ከእንግዲህ በኋላ ክልል የሚባል ጥያቄ የለም ዝም ብላችሁ ኑሩ እንደማይባልም፤ በየሰፈሩ ክልል ካልሆንኩ ለሚለውም ሁሉንም ክልል ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት አቅም ያለመኖርን ሲሆን፣ ይህንንም በተለያየ ምሳሌ አስረድተዋል። ችግሩንም መፍትሔውንም ሚዛናዊ በኾነ መንገድ ማየት ይገባል። በዚህም ዘለግ ላለ ጊዜ የሚያገለግል አደረዳጀት መፍጠር አስፈላጊ ነው። መንግሥት በክልሉ የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን እየፈታ መኾኑንና በሒደትም የሚታዩ ጉዳዮች መኖራቸውን፤ ለዚህም በየጊዜው ውይይት ማድረግ እንጂ ጥድፊያ እንደማያስፈልግ ገልጸውላቸዋል።

የክልሉን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ችግሩን እንዴት እንፍታው በሚለው ሐሳብ ችኮላ ሳይሆን የሰከነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ለተወያዮቹ የገለጹት፤ ክልል በምን መልኩ ቢደራጅ ይሻላል የሚለውን ለመወሰንም ሕዝቡን የሚጠቅም ውይይት በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል። ለዚህም በየዞኑ፣ በየወረዳውና በየቀበሌው ማኅበረሰቡን ሊያወያዩ የሚችሉ ቁጥራቸው 80 የኾኑ ከክልሉ የተውጣጡ ግለሰቦች የተሰባሰቡበት ቡድን መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ከአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አንፃር የቀረቡ ጥያቄዎች የነበሩ ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ከሠጡት ሰፊ ማብራሪያ ሊጠቀስ የሚችለው፤ በማናቸውም ሁኔታ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል ተግባር ድርድር ያለመኖሩን ነው። ደጋግመው እንዳሉትም ኢትዮጵያ አትፈርስም። (ኢዛ)

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎች

በተጠናቀቀው ሳምንት በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ ከተሠጠባቸው ጉዳዮች አንዱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ይጠቀሳል። ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ሕጋዊ ሰውነት እንዲሠጠው የሚለው ነው። በዚህ ረቂቅ ላይ ተወያይቶም በሙሉ ድምፅ በመወሰን ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለፓርላማ እንዲተላለፍ ወስኗል።

ሌሎቹ ውሳኔ የተሠጠባቸው ጉዳዮች ደግሞ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምርና ልማት ማዕከል ማቋቁሚያ ረቂቅ ደንብ የሲቪል አቪየሽን አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ፣ አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂና የመከላከያ ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ለመወያየት ውሳኔ ማሳለፍ ችሏል።

በተለይ አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ የአገሪቱ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ጊዜው የሚጠይቀውንና ደረጃውን የጠበቀ የሕብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረካ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርሆዎች ላይ የተመሠረተና ውጤታማ አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችል የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት እንዲቻል አጋዥ ይኾናል የተባለ ስትራቴጂ ነው። ከዚህም ሌላ ስትራቴጂው የተፈጸሙ ወንጀሎችን መፍትሔ ከመሥጠት በላይ ለወንጀል መነሻ ምክንያቶችን በመቀነስ ወይም በማጥፋት ጭምር ለመሥራት የሚያስችል አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ መኾኑም ተገልጿል።

የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ በቀረበው በዚህ ረቂቅ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በስፋት ከተወያየ በኋላ፤ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ስትራቴጂው በሥራ ላይ እንዲውል ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ መወሰኑንም መረጃው አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ብዙ ሲያነጋግር የነበረው የመከላከያ ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ጉዳይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተመለከተውና ውሳኔ ያሳለፈበት ነበር። ባሳለፍነው ሳምንትም የመከላከያ ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ቀርቦ ተመክሮበታል። በረቂቅ ደንቡ ዋና ይዘትም ከብረታብረትና ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር በማዞር በአንድ ኮርፖሬሽን ሥር እንዲደራጅ ማድረግ ነው። በዚህም መሠረት የደጀን አቪየሽን ኢንጂንየሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የጋፋት አርማመንት ኢንጂንየሪንግ ኢንዱስትሪ የሆሚቾ አሚውኒሽን ኢንጂንየሪንግ ኢንዱስትሪና የፊውል ነዳጅና ፕሮፔላንት ንዑስ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በአንድ ኮርፖሬሽኑ ሥር በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ይቻል ዘንድ የቀረበ ደንብ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በወጣው መረጃም የመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው መሠረት፤ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል ስለመወሰኑ አመልክቷል።

ያሳለፍነው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይም ስለመወያየቱና ይህም ረቂቅ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል እንዲጸድቅ ለፓርላማ እንዲተላለፍ ተደርጓል። (ኢዛ)

የግማሽ ዓመት ክንውን

በኢትዮጵያውያን የበጀት ዓመት ስሌት መሠረት የ2012 በጀት ዓመት አንድ ብሎ ከጀመረ ግማሽ ዓመት ተቆጥሯል። ባለፉት ስድስት ወራት የተቋማት ምዘናን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን ይፋ ማድረግ የተለመደ ነውና፤ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት ክዋኔያቸውን እያሳወቁ ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ባንኮችና ሌሎች ተቋማት ይገኙበታል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ካደረገው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፤ በ2012 ግማሽ የበጀት ዓመት ከ127.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰቡን ሲያስታውቅ፤ ይህ ገቢ ከእቅዱ በላይ ነው ተብሏል። ይህ በስድስት ወር የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ28.9 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። የጉምሩክ ባለሥልጣን ደግሞ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወሮች ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዲሁም ሕገወጥ ገንዘብ መያዙን አስታውቋል። በዚህ የባለሥልጣኑ የስድስት ወር ሪፖርት በስድስት ወር ውስጥ 48.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 54.8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡና ከእቅድ በላይ ገቢ ማግኘቱን ጠቁሟል። ይህ ገቢ በ2011 ግማሽ ዓመት ተገኝቶ ከነበረው የ17.3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብሏል።

ሌላው የግማሽ ዓመት መረጃውን ያቀረበው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት የኢንፎርሜሽን መረብ ኤጀንሲ ነው። በዚህ መረጃው መሠረት በስድስት ወራት በተለያዩ ቁልፍ የአገሪቱ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ 285 የበይነ መረብ (ሳይበር) መከሰታቸውን ነው። ይህ የጥቃት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ እንደጨመረም ታውቋል። ኾኖም እነዚህን ጥቃቶች የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ተብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ