የአባ ጳውሎስ ልዩ የጥበቃ ሹም ቃላቸውን ሰጡ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. July 31, 2009)፦ ለጥቅምት ወር 2002 ዓ.ም. ቀጠሮ የተያዘለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ውዝግብ በአሁኑ ወቅትም መልክና ቅርፁን ለውጦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። በዚሁ ውዝግብ ከአቶ አባይ ፀሐዬ ቀጥሎ አቶ በረከት ስምኦንም እጃቸውን ማስገባታቸው ታውቋል።

 

ከጠቅላይ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት አካባቢ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የማስታወቂያና የግንኙነት ሚኒስትሩ አቶ በረከት፣ በእነ አባ ኢጲፋኒዮስና አቡነ ቄርሎሰ ላይ በደረሰው የውክብያ፣ የማስፈራራት እና የበር ሰበራ ድርጊት በእጅጉ ተቆጥተዋል።

 

ምንጮቹ ባሉት መሠረት አቶ በረከት ስምኦን የተቆጡት “እንዴት የአባቶች ክብር እኛ ሳናውቀውና ሳንመክርበት በደህንነት ሰዎች ጉልበት ይደፈራል? ይህ መንግስታችንን የሚያስወቅስ የደካሞችና ኃላፊነት የማይሰማቸው ተግባር ነው” የሚለውን መከራከሪያ ነጥብ አንስተው ነው፡፡ በዚህም የተነሣ በአቶ በረከትና በአቶ አባይ ፀሐዬ መ/ቤት በሚታዘዙት የደህንነት ሰዎች መካከል ፍጥጫ መፈጠሩን ምንጮቻችን አስረድተዋል።

 

ይህንኑ መሠረት አድርጐም የፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽን የጳጳሳቱ ክብር ተደፈረ፣ በሕይወታቸውም ላይ ታላቅ አደጋ አንዣቦ ነበር በተባለበት ቀን፤ ወደ ጳጳሳቱ ማደሪያ በተሽከርካሪ ገብተው በር ሲደበድቡና ሲሰብሩ፣ ክብረ-ነክ ስድብ ሲሳደቡ የነበሩትን ሰዎች “ማንፈቅዶ ነው ያስገባቸው…” የሚለውን ነገር ለማጣራት ባደረገው እንቅስቃሴ፤ የብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ልዩ ጥበቃና የፕሮቶኮል ሹም ኃላፊ ናቸው የሚባሉት “አባ ዕንቁ” የተባሉ ሰው ተጠርጣሪ ሆነው በመገኘታቸው፤ ግለሰቡን ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ጠርቶ ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። “አባ ዕንቁ” ቃላቸውን ከሰጡም በኋላ ዋስ ጠርተው ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን የጠቅላይ ሀገረ-ስብከት ምንጮች አስታውቀዋል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ሲኖዶስ መካከል በስልጣን መባለግ በሙስናና አባታዊ ሃላፊነትን ባለመወጣት ምክንያት በተነሱ አለመግባባቶች ለሁለት ተከፍሎ ከፍተኛ ክርክር ሲደረግበት ከቆየ በኋላ የአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጉዳዩ እስከመግባት የደረሱ ቢሆንም እልባት ሳያገኝ ለጥቅምት 2002 ዓ.ም መቀጠሩ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ሰአት የአባ ጳውሎስ ተቃዋሚ የሆኑት በእነ አቡነ ሳሙኤል ደጋፊዎች ላይ ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰባቸው መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

በተያያዘም ግንቦት 15 ቀን 2001 ዓ.ም. “አቡነ ጳውሎስን ከአስተዳደር ኃላፊነት የሚያገል አሠራር በሲኖዶስ ፀደቀ” የሚል ጽሁፍ ይዛ በመውጣቷ አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ሐሙስ ሐምሌ 23 ቀን አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ እና ሪፖርተሩ አብርሃም በጊዜው ሲሆኑ በጣቢያ ለ6 ሰዓታታ ያህል ቆይተው 8፡30 ላይ በዋስ ተለቀዋል።

 

ይኸው የፓትሪያርኩን ስም የሚያጐድፍና ብፁእናቸውን የሚነካ ዘገባ አቅርባችኋል በሚል ለክስ የተዳረጉት ጋዜጠኞች ለዘገባቸው በቂ ማስረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል።

 

ጋዜጠኞች የደረሰባቸው ችግር እንዳለ ተጠይቀው ለሰአታት ከመጉላላት ውጭ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳልደረሰባቸው ገለጸዋል። የአዲስ ነገር አዘጋጅ ባልታወቁ ሰዎች ተደብድቦ እንደነበር አይዘነጋም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ