የተሰራጩት መግለጫዎችና ዘገባዎች የፓርቲውን ደጋፊዎች አምታትተዋል

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2001 ዓ.ም. July 17, 2009)፦ በተለየም በዚህ በያዝነው ሣምንት ”አንድነት ለዲሞክረሲና ለፍትህ” የተሰኘውን ፓርቲ አስመልክቶ በተለያዩ የኢትዮጵያውያን መገናኛ ብዙኀን የመሰነጣጠቅ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ተዘግቧል። በሣምንቱ ማብቂያ ላይ የድርጅቱን አለመሰንጠቅና ታግደዋል የሚባሉትን 21 የፓርቲውን አመራሮች አለመታገድ በሚመለከት መግለጫ ወጥቷል። ዘገባዎቹና መግለጫዎቹ የፓርቲውን ደጋፊዎች አመታትዋል።

 

በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን እየታገልን ነው ከሚሉትና በሠላማዊ ትግል ከሚያምኑት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በብዙኀን ኢትዮጵያውን ዘንድ ከፍተኛ ግምት እንደተሰጠው የሚታወቀው የአንድነት ፓርቲ በአመራሮቹ መሃከል ከፍተኛ ሽኩቻና ስምምነት ማጣት እየተስተዋለበት መገኘቱ ይታወቃል።

 

በሀገር ውስጥ የሚታተሙት ”ሰንደቅ” እና ”ሪፖርተር” ጋዜጦች የፓርቲውን የህዝብ ግንኙት ኃላፊና ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ኃይሉ አርኣያን በመጥቀስ እንደዘገቡት ከሆነ 21 የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላትን ፓርቲው አግዷል።

 

21 የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ”የአንድነት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ” በሚል ርዕስ ሐምሌ 2 ቀን አንድ ጽሑፍ ማሰራጨታቸው ታውቋል። ከ21ዱ አባላት ውስጥ የፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ስም የሚገኝበት ሲሆን፣ የጽሑፉ ይዘት ርዕሱ እንደሚጠቁመው በተለይም በከፍተኛ አመራሩ ውስጥ አለ የሚባለውን ችግር ጠቁሟል። በተለይም የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰሩ በኋላ በአመራሩ ላይ ተስተውለዋል የተባሉትን ችግሮች ለማሳየት ሞክሯል።

 

በፓርቲው ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነትን የአመራር ዘርፍ ላይ የሚገኙትን 21ዱን የፓርቲውን አባላት ያገደው ቡድን ልዩነታቸው ፓርቲው ከ”መድረክ” ጋር አብሮ የመሥራቱን ጉዳይ በመቃወማቸው መሆኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን መዘገቡ ይታወቃል። የትኞቹ ወገኖች እንደሆኑ በትክክል ባይታወቅም፤ ሁለት የተለያዩ መግለጫዎች ፓርቲው እንዳሰራጫቸው ለማወቅ ችለናል።

 

ሁለቱም መግለጫዎች ከኢንጂንየር ግዛቸው (ከአጋጁ ቡድን) እንደተሰራጩ ተገምቷል። ሁለተኛው መግለጫ ”ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ ማብራሪያ” በሚል የተሰራጨ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

የመጀመሪያውና አንደኛው መግለጫ “የአንድነት ፓርቲ ዲሞክራሲያዊና ደንባዊ አሠራር ተጠናክሮ ይቀጥላል” በሚል የተሰራጨ ሲሆን፤ ”… የአፍራሹ ጽሑፍ ባለቤቶች ነን በሚል ስማቸው ከተጠቀሱት ውስጥ በአብዛኛው በተለመደው የሥነ-ምግባር ጉድለታቸውና ደንብ ጣሺነታቸው እንዲሁም አፍራሽ ጽሑፎችን በየጋዜጣው በማውጣታቸው ከአመራር የታገዱ፤ በፓርቲው አቅም ማነስ ምክንያት ከወርሃዊ ውሎ አበል ተከፋይ ሠራተኛነታቸው የተነሱ፤ በተደጋጋሚ የሰብሳቢነት ሚናቸውን ረስተው የብ/ም/ቤት ስብሰባ ረግጦ የመውጣት አመል ያላቸው ናቸው። የእነዚህ ጥቂት ግለሰቦች አፍራሽ ጽሑፍ በአሉባልታና በጥላቻ የተሞላ ከመሆኑም በላይ ፓርቲው የቆመለትን የዲሞክራሲ መርኅና የአብላጫ ድምፅ ውሳኔን የሚጥስ፤ በጥቅሉ ግን የፓርቲውን ብ/ሥ/አስፈፃሚ ኮሚቴና ብሔራዊ ም/ቤቱን በተራና አልባሌ ቋንቋ የሚዘልፍ፤ ባጠቃላይም ራሳቸው ደራሲዎቹን ከፓርቲው የሚነጥል ማመልከቻ ነው። …” ይላል።

 

በመቀጠልም፤ “… ስለዚህ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በፓርቲው ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ደንቡ የሚፈቅድለትን ሕጋዊ እርምጃ ሁሉ በየደረጃው በመውሰድ ላይ ሲሆን፣ የመጨረሻው እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ ም/ቤታችንም በቅርቡ ተሰብስቦ የሚሰጠውን ደንባዊ ውሳኔ ደግሞ በቀጣይ የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን። …” ሲል ይደመድማል።

 

ሁለተኛውና ”ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ ማብራሪያ” እንደሆነ ተገልጾ የተሰራጨው መግለጫ ደግሞ፤ ”በ16/07/2001 ዓ.ም. በጀርመን ሬዲዮ የተላለፈውና በሌሎች የግል ጋዜጠኞች አንድነት ፓርቲ 21 የአመራር አባላት ከፓርቲው አግዷል የሚለው ዘገባ ፍፁም መሠረት የሌለው ሐሰት ዜና ነው” ይልና፤ ”... በመሠረቱ የአንድነት ፓርቲ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ነው። የአባላትን ነፃ ሃሳብ፤ ጥያቄና ቅሬታ በመዋቅሩ ውስጥ ደንቡን ተከትሎ ያለ ምንም ገደብ እንዲስተናገድ ያደርጋል። የብዙኀንን አብላጫ ድምፅና ዲሞክራሲያዊ ውሳኔያችን የሚያከብሩትን በደንቡ መሠረት እንዲንቀሳቀሱና እንዲያስተናግዱ ማድረግ የአንድነት አመራር አባላት ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ዲሞክራሲያዊና ደንባዊ አሠራር የአንድነት ፓርቲ የህልውና መሠረት ነው። ስለሆነም በማንኛውም ጊዜ የአንድነት አመራር በአብላጫ ድምፅ የተወሰኑ ጉዳዮች እንዲተገብሩ ዲሞክራሲያዊና ደንባዊ አሠራር እንዲረጋገጥ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ በማንም ግለሰብ ወይም አባላት እንዲቀለበስ ጨርሶ አይፈቅድም። ...” የሚል ድምዳሜ ያሰፍራል።

 

በሁለቱም መግለጫዎች ላይ ለማመልከት የተፈለገው የአመራር አባላትን የማገድ ሥልጣንና ኃላፊነት የብሔራዊ ምክር ቤቱ መሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛው መግለጫ (”ማብራሪያ” በሚል የተሰራጨው) የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11.1 እና 11.4 ይጠቅሳል።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ፓርቲው መጪው ሣምንት መጀመሪያ ላይ የኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው ቡድን የብሔራዊ ምክር ቤቱን አስቸኳይ ጉባዔ እንደጠራ ጠቁመዋል። ምናልባትም የፊታችን ሰኞ ሊካሄድ ይችላል የሚባለው የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጉባዔ ከተካሄደና 21ዱን አባላት ካገደ የፓርቲው መሰንጠቅ እውን እንደሚሆን ታምኗል።

 

ይህንን በፓርቲው ውስጥ ተከስቷል እየተባለ ያለውን የመሰንጠቅ ወይንም የተወሰኑትን የአመራር አባላት የማገድ ሁኔታን አስመልክቶ ነዋሪነታቸው በአውሮፓ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ቀድሞ የቅንጅት፤ አሁን ደግሞ የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባልን የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር አስተያየት እንዲሰጡት አነጋግሯል። አስተያየታቸውን የሰጡት እኝሁ ኢትዮጵያዊ፤ ”... በፓርቲው ውስጥ የተከሰተውን መጠነኛ ቅራኔ መፍታት ያልቻሉት የትናንቱ ታዋቂው የቅንጅት አመራሮች በመሆናቸው በእጅጉ አዝናለሁ። ከሌላ ድርጅት ጋር አብሮ የመሥራትና ያለመሥራትን በሚመለከት አንድ ድርጅት የራሱን ሰዎች እስከማገድ የሚያደርሰው፤ የልዩነት ሃሳብን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ’እኔ እበልጥ’፣ ’እኔ እበልጥ’ በሚል ግለሰባዊ በሆነ ልዩነት ደርጅትን ማኮስመን ከምደግፈው የአንድነት ፓርቲ የማልጠብቀው ነው።” ብለዋል።

 

እኝሁ የፖለቲካ ግለሰብ አክለውም፤ ”የፓርቲዋን እውነት ለመጠበቅ ስትል መስዋዕትነት የከፈለችውን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ፈለግ ተከትለው መሄድ ያልቻሉ የፓርቲው አመራሮች በመሆናቸው አዝኛለሁ። በፓርቲውም አፍሬአለሁ።” በማለት በምሬት አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ሰጥተዋል።

 

ከኢትዮጵያ ዛሬ፦ ለአንባብያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በተለያዩ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙኀን የተዘገቡትን፣ በፓርቲው አመራር አባላት እንዲሁም በፓርቲው ስም የወጡትን መግለጫዎችና ጽሑፎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል በዚህ አጋጣሚ ጉዳዩን ተከታትለን የተጣራ መረጃ ለመስጠት የበኩሉን ጥረት ለማድረግ ይሞክራል።

 

1፣ ”የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ” ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. በ21ዱ የአንድነት ከፍተኛ አመራር አባላት ተበተነ የተባለው ጽሑፍ፣ 

 

2፣ ”አንድነት በ’ወሳኝ ምዕራፍ’ ውስጥ ገብቷል”፣ ”21 የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላቱን አገደ”፣ ”ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ሽመልስ ተ/ፃዲቅ፣ አቶ ደበበ እሸቱ ከታገዱት ውስጥ ይገኙባል” - ሰንደቅ ጋዜጣ ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ዕትም፣

 

3፣ ”የአንድነት አመራር ለሁለት እየተሰነጠቀ ነው፤ እስካሁን ሦስት ኃላፊዎች ታግደዋል” በውብሸት ታዬ፣ ሐምሌ 7 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

4፣ “የአንድነት ፓርቲ ዲሞክራሲያዊና ደንባዊ አሠራር ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሐምሌ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. ከአንድነት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

 

5፣ ”ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ ማብራሪያ” ሐምሌ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. ከአንድነት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ