የግንቦት ሰባት አባላት ናቸው የተባሉ 35 ሰዎች ታሰሩ
በጉዳዩ ላይ ግንቦት ሰባት መግለጫ ሰጥቷል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. April 25, 2009)፦ የግንቦት ሰባት አባላት ናቸው የተባሉ 35 ሰዎች በትናንትናው ዕለት መታሰራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። ይህን መግለጫ በማስመልከት ግንቦት ሰባትም መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫው እንደሚለው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ሥነሥርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት 35 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና የወንጀል ምርመራ መጀመሩን ገልጾ፤ በቀጣይ ስለ ጉዳዩ በዝርዝር የሚገለፅ መሆኑንና አስታውቋል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ "በሀገራችን ሠላማዊ ትግል አብቅቷል በማለት የደም ማፋሰስን መንገድ እንደ ብቸኛ የትግል ስልት ያወጀው ራሱን ግንቦት 7 ብሎ የሚጠራውና በውጭ ሀገር በእነ ብርሃኑ ነጋ የተቋቋመው የፀረ-ሠላም ቡድን ሕገመንግሥታችንንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን በኃይል ለመገርሰስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ በማድረግ የወታደራዊ ንዑስ ቡድንና የሲቪል ንዑስ ቡድን በሚል በሀገር ውስጥ ያደራጀው የሽብር መረብና እንቅስቃሴ በፀጥታ ኃይሎች ከሸፏል" የሚል ነው።
“የወታደራዊ ንዑስ ቡድኑ ጥቂት በሥራ ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና በብዛት ደግሞ ከመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የዲሲፕሊን ጥፋቶች የተቀነሱ አባላትን ያቀፈ ሲሆን፣ የሲቪል ንዑስ ቡድኑ ደግሞ ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ አባላትን ያካተተ ነው” ሲል ገልጿል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የዚህን የኅቡዕ የሽብር መረብ እንቅስቃሴ ረዘም ላለ ጊዜ ክትትል ሲያደርግበት ከቆየ በኋላ ትናንት ሚያዝያ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ሥነሥርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት 35 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
በተጨማሪም የፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት በተደረገው ብርበራ ተጠርጣሪዎቹ ለሽብር ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጁአቸውን የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ ቦምቦች፣ የሳተላይት፣ የኮምፒዩተርና የመገናኛ መሣሪያዎች፣ ወታደራዊ ዩኒፎርሞች፣ የዕቅድ ሰነዶችና ሌሎች በርካታ ማስረጃዎች መያዛቸውን ገልጿል።
መግለጫው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በታየበት ወቅትም፤ የጦር መሣሪያዎች፣ ቦምቦች፣ የሳተላይት፣ የኮምፒዩተርና የመገናኛ መሣሪያዎች፣ ወታደራዊ ዩኒፎርሞች፣ የዕቅድ ሰነዶችና ሌሎች ነገሮች ታይተዋል።
በሌላ በኩል ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት መንግሥት ያወጣውን መግለጫ በመቃወም የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል። “የመለስ አገዛዝ በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. “ራሱን የግንቦት 7 ብሎ የሚጠራው ቡድን የሽብር ሴራ ከሸፈ” በማለት ያወጣውን መግለጫ አንብበነዋል።
“የመለስ አገዛዝ በተለያዩ ወቅቶች በህዝብ ውስጥ ተቃውሞ ሲበዛበት፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች አፋጠው ሲይዙት፣ በገዛ ሠራዊቱና በሲቪል አስተዳደሩ ውስጥ ችግር በገጠመው ቁጥር፣ ህዝብን ለማደናገር ወይም የሚፈልጋቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ለማጥቃት ሲፈልግ እንዲህ አይነቱን መግለጫ ማውጣትና ህዝብን ማደናገር፣ መግለጫውን ተከትሎ የሚፈልገውን መግደል፣ ማሰር፣ ከሥራ ማባረር፣ ከቀየው ማፈናቀልና ማሳደድ ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ዕድሜው ደጋግሞ ሲፈጽመው የኖረ ነውረኛ ድርጊቱ እንደሆነ ይታወቃል።
“ይህ በዛሬው ዕለት ግንቦት 7 ንቅናቄን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ ከዚህ በፊቱ ወያኔ ሲያወጣው ከነበሩት መግለጫዎች ልዩነት የሌለው መሆኑን ንቅናቄያችን ይገልፃል። የሚይዘው የሚጨብጠው ያጣው የመለስ አገዛዝ የግንቦት 7ን ንቅናቄ በማንሳት አንዴ ‘በሠላም እንቀሳቀሳለን የሚሉ ድርጀት አባላት በስውር የግንቦት 7 አባላት ናቸው’ የሚል የስም ዝርዝር ሲያወጣ፣ አንዴም ‘እነዚህ ከበርቴዎች ግንቦት 7ን ይደግፋሉ’ በማለት የማሸበሪያ ወረቀት ውስጥ ውስጡን ሲበትንና ባለሀብቶቹን ሲዘርፍ፣ አሁን ደግሞ ‘የተወሰኑ የሠራዊት አባላት የግንቦት 7 ሰዎች ሆነው ተገኙ’ ብሎ በራዲዮና በቴሌቭዥን ሲያስተጋባ፤ ግንቦት 7 ንቅናቄ እየተነሳ ምላሽ በመስጠት የሚያጠፋው ጊዜ እንደሌለው ለማሳወቅ እንወዳለን።
“ንቅናቄያችን እንደተገነዘበው ግንቦት 7 ለመለስ ዜናዊና በአምባገነናዊ ክበቡ ለተሰባሰቡት ጥቂት ዘረኞች እንቅልፍ የነሳቸው ድርጅት መሆኑን ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ተገቢ ነው።
“ንቅናቄያችን የወያኔን ማስፈራሪያ ክስና ሌላም ነገር ፈርቶ ይህን ዘረኛ አምባገነን ሥርዓት ከሀገራችን ሀዝብ ጫንቃ ላይ በማንሳት ህዝብ የሀገሩና የሕይወቱ ባለቤት የሚሆንበትን መራራ ትግል በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የጀመረውን ፍልሚያ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ወዳጅም ሆነ በመለስ ዜናዊ ስር የተሰባሰቡት አምባገነን ዘረኞችና ደጋፊዎቻቸው ሊያውቁት ይገባል።” ሲል ግንቦት ሰባት በመግለጫው ምላሽ ሰጥቷል።



