የዳኛ አባት ስም መሳሳት 2000 ብር አስቀጣ
ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ቅጣቱን ከፍላ ተለቀቀች
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. November 4, 2008)፦ የእንቢልታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚያስችሉትን ዳኛ የአባት ስም በመሳሳትዋ በፍትህ ሚኒስቴር በተመሰረተባት ክስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት የ2000 ብር ቅጣት ወስኖባታል።
በዛሬው ዕለት ጋዜጠኛ ጽዮን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ለስድስት ሩብ ጉዳይ አካባቢ በፖሊስ ታጅባ ታስራ ካደረችበት 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ”ፈጣን ችሎት” ተብሎ በሚጠራው 14ኛው ወንጀል ችሎት ቀርባለች። የዛሬው ቀጠሮዋ ለቅጣት ውሳኔዋን እንደነበር አይዘነጋም።
ትናንት ዳኛ አብርሃም ተጠምቀ ”ጥፋተኛ ነሽ” ብለው ከወሰኑባት በኋላ ሲ.ፒ.ጄ. (CPJ - Committee to Protect Journalists) የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት የአፍሪካ ፕሮግራም ኮርዲኔተር ቶም ሮድሰ ”ጋዜጠኛን በዘገባ ስህተት መወንጀል አሰቃቂ ድርጊት ነው” ብለዋል። አክለውም ”ፍርዱ አግባብነት የለውም። ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ መታሰር የለባትም” ብለዋል። (የሲ.ፒ.ጄ.ን ሦስት ዘገባዎች አስነብበኝ፣ 1) Press freedom in the news 11/05/08 2) Editor convicted over misidentification 3) Ethiopian journalists detained over misidentification)
ዳኛው ጋዜጠኛዋ የ2000 ብር ቅጣት ከወሰኑባት በኋላ ቅጣቱን ከፍላ ነፃ መሆኗ አስኪረጋገጥ ድረስ ታስራ ቆይታለች። በመጨረሻም ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ ከእስር መለቀቋን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ዘግቧል።
እንቢልታ ጋዜጣ በቅጽ 1 ቁጥር 041 የመስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም. ዕትሙ ”የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚያስችሉት ዳኛ ከችሎት ተነሱ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ላይ የዳኛውን የአባት ስም በመሳሳቱ ዓቃቤ ሕግ ”የሐሰት ወሬ በመፃፍና በማሰራጨት በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲስፋፋ በማድረግ” በሚል ጥቅምት 13 ቀን ክስ መመስረቱ አይዘነጋም። የተመደቡት ዳኛ መሐመድ ዑመር ሆነው ሳለ፣ ጋዜጣው ”ዳኛ መሐመድ አሚን ሳኒ” በማለቱ ሲሆን፣ ዳኛ መሐመድ አሚን ሳኒ ደግሞ በቅንጅት መሪዎች ክስ ላይ ከሦስቱ ዓቃቢያነ ሕጎች አንዱ የነበሩ ናቸው።
በዚሁ ክስ ምክንያት ዋና አዘጋጅዋ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ፣ ምክትል አዘጋጁ ጋዜጠኛ ሀብቴ ታደሰ እና አዘጋጁ ጋዜጠኛ አጥናፉ አለማየሁ ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን ታስረው የነበረ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ሲሆን በማግስቱ ስትፈታ፣ ጋዜጠኛ ሀብቴ እና ጋዜጠኛ አጥናፉ ሁለት ቀናት ታስረው ክስ ሳይመሰረትባቸው ጥቅምት 14 ቀን መፈታታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።



