የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት

ወጣቶች ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ

ኢዛ (ሐሙስ ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 15, 2021)፦ የሕወሓት ሽብርተኛ ቡድን የጀመረው ጥቃት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም የገፋው በሕልውናችን ላይ የተጋረጠ አደጋ በመኾኑ፤ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት በመመከት አገር የማዳኑ ተልዕኮ እንዲሳካ ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጐን እንዲቆም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠየቀ።

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስተዳደሩ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የቡድኑን ጥቃት ለመመከት “ወጣቶችን አቅማችን የሚፈቅድ ሠራዊታችንን በመቀላቀል፤ ሌሎቻችን ደግሞ የሞራልና የስንቅ ድጋፋችንን አጠናክረን በመቀጠል ደጀንነታችንን በተግባር የምናሳይበት መኾን ይኖርበታል” በማለት ለሕዝቡ ጥሪ አቅርቧል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠት በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር ይመክናል!

በሰሜን ኢትዮጲያ ከተካሔደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ መንግሥት ሕዝቡ በጦር እንቅስቃሴ ሳይረበሽ በጥሞና ጊዜ ፋታ አግኝቶ እርሻውን የሚያከናውንበት የእርዳታና ድጋፍ አቅርቦቱም ያለሰበብ ሳይደናቀፍ የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ወስዷል።

ኾኖም ግን ይህ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ መንግሥት የታወጀውን ሕዝብን ያስቀደመ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ተጠቅሞ ከስሕተቱ ተምሮ የትግራይን ሕዝብ ከከፋ ስቃይ እና መከራ መታደግ ሲገባው፤ የመንግሥትን አርቆ አስተዋይነት እንደሽንፈት ቆጥሮ ከተደበቀበት ጎሬ ወጥቶ እንደ ድል አድራጊ በየአካበቢው መፎከር ብቻ ሳይኾን ከዚያም አልፎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የተዘረጉትን መልካም የሰላም እድሎችን ሁሉ ዝግ በማድረግ እንደገና ጥቃት ከፍቷል።

ጥቃቱ የተከፈተብን መላ ኢትዮጵያውያን ዓለምን ባስደነቀ መልኩ እጅግ ሰላማዊ የኾነ ምርጫ አከናውነን የጋራ አሸናፊነታችንን ባረጋገጥንበት ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላንን ቁርጠኝነት በተግባር ባሳየንበት ወቅት መኾኑም ብቻ ሳይኾን፤ ሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብን በመሙላት ላይ ባለንበትና መላው ኢትዮጵያውያን የአገራችንን የትንሳኤ ዘመን ብስራት የኾነው የህዳሴ ግድባችን ላይ እየተቃጣ ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ለሉአላዊነታችን መከበር በአንድነት ትከሻ ለትከሻ በቆምንበት ወቅት መኾኑ ጉዳዩን በተለየ ስሜት እንድንመለከተውና ኃላፊነታችን ላቅ ያለ መኾኑን ያስገነዝበናል።

ይህ የሽብር ቡድን ለዚህ እኩይ ዓላማው፤ እንክብካቤ የሚያሻቸው፤ የጦር መሣሪያ ሳይኾን ደብተር ማንገብ የሚገባቸውን ሕፃናት፤ የሃይማኖት አባቶችን፤ አዛውንቶችን ደካሞችን ጨምሮ በግዳጅ በጦርነት በመማገድ ለአገራችን ብቻ ሳይኾን ለዓለም አቀፍ ሕግጋት ተፈጻሚነት ደንታ የሌለው ጨካኝ ቡድን መኾኑን በይፋ እያስመሰከረ ይገኛል።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸው ጭምር ይህ የሽብር ቡድን መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ወደ ጎን በማለት በንጹኀን ላይ እምነትን ጭምር መሠረት አድርጎ ግድያና ጭፍጨፋ ሲያካሒድ፤ ባለው አቅም ሁሉ ትንኮሳ ከማድረግ አልፎ ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጅና ሲጀምር የተቋቋሙበትን ዋና ዓላማ እና የጋዜጠኝነትን ሥነ-ምግባር በጣሰ መልኩ ጉዳዩን ዓይቶ እንዳላየ ሲያልፉት ተመልክተናል። ይባስ ብለው አሁን ላይ መንግሥት የሕልውና ዘመቻውን በጀመረበት ሰዓት የተኩስ አቁም ይደረግ በሚል የተለመደ የሽብር ቡድኑን የማዳኛ ታክቲካቸውን ለመተግበር ሲሯሯጡ ታዝበናል፤ ይህ ኢ-ፍትሐዊ ተግባር ለመላው የኢትዮጰያ ሕዝብ ድብቅ ዓላማቸውን ይፋ ያደረገ ኾኗል።

ወትሮም ቢኾን እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ሰላም ኾና ማደር የለባትም

“እኔ ከሞትኩ፤ ሰርዶ አይብቀል” እንዲሉ፤ በተደጋጋሚ እኔ ካልመራው ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት! በማለት ሲናገር የከረመውና ላለፉት ዓመታት አቅሙ በቻለው ሁሉ ከውስጥም ከውጪም ካሉ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሁሉ ጋር ሲሰራና ሲያሰማራ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን ሲያደርግ የቆየው ይህ ቡድን፤ ከጥፋት ተልእኮው መቼም የማይመለስ መኾኑ ለማንም ተመልካች ግልጽ ነው።

አሁንም ቢኾን የተጀመረው ማጥቃት እና ትንኮሳ፤ የአንድ ወገን የአንድ አካባቢ ጥቃት ብቻ አይደለም። ይህ ጥቃት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ፤ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም የገፋው በሕልውናችን ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው።

ይህ አሸባሪ ቡድን የአገራችን ሕዝቦች መተባበርና አንድነት እንቅልፍ የሚነሳው፤ ኢትዮጵያ ተበታትና እስካላየ አልያም እራሱ እስካልመራ ድረስ መቼም ቢኾን አርፎ የማይቀመጥ፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጠ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ጠላት ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሁልጊዜውም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በኾነው ሠራዊታችን ኩራት ይሰማናል።

ለሠራዊታችንም ማንኛውንም ድጋፍ ማድረግን አጠናክረን እንቀጥላለን።

በዚህ ሰዓት አሸባሪ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት በመመከት የተጀመረው አገር የማዳን ተልእኮ ግቡን እንዲመታ መላው ሕዝባችን ለአገሩና ለሠራዊቱ ሁሌም እንደሚያደርገው ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ በገንዘብ፤ በጉልበትም ሆነ በእውቀት አቅም በፈቀደው ሁሉ በማድረግ አገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።

ወጣቶችና አቅማችን የሚፈቅድ ሠራዊታችንን በመቀላቀል፤ ሌሎቻችን ደግሞ የሞራልና የስንቅ ድጋፋችንን አጠናክረን በመቀጠል ደጀንነታችንን በተግባር የምናሳይበት መኾን ይኖርበታል።

መላው ኢትዮጵያውን፤ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሸባሪው ቡድን በሚነዙ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሳንወናበድ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር፤ እርስ በእርስ በመመካከርና በመደጋገፍ፤ የተቃጣብንን አገራዊ ጥቃት በሕብረትና በአንድነት፤ እንደ አንድ ልብ ኾነን ልንመክት ይገባል።

በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያ የጸጥታ ኃይሉን በጋራ በትብብር በእውቀት ላይ የተመሠረተ ስምሪትና ተግባር የምትተቹና እየከፋፈላቹህ በማኅበራዊ ሚዲያ የምትጽፉ ከዚህ ድርጊታቹህ በመቆጠብ ይልቁንም የጸጥታ ኃይሉን ስምሪት ለጸጥታ አካሉ ትተን፤ በአገራችን ላይ ከውስጥም ከውጭም በየአቅጣጫው የተከፈተውን የዲጂታል ሚዲያ ጦርነት በትብብርና በአንድነት ልንመክት ይገባል።

የከተማችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሠራዊታችን ከምናደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍም ባሻገር የአካባቢያችንን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ፤ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመሥራት፤ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር፤ የጀመርነውን የከተማችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ እንቅስቃሴ እንቀጥላለን፤ አገራዊ ኃላፊነታችንን በንቃት እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!!

ጀግኖች አባቶቻችን ተባብረውና ተጋግዘው በጀግንነት ያቆዩልንን ነፃ አገር እኛ ልጆቻቸው የአባቶቻችንን ታሪክ በመድገም የኢትዮጵያን ክብር ከፍ እናደርጋለን!

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ሕብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!

ሐምሌ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ