ለትግራይ ለ2014 የተያዘው በጀት በእንጥልጥል ላይ ነው
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሸዴ
መንግሥት በጀቱ እንዲለቀቅ ውሳኔ ላይ አልደረሰም
ለክልሉ 12 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት ነበር
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 7, 2021)፦ የፌዴራል መንግሥት በ2014 በጀት ዓመት ለትግራይ ክልል ተብሎ የተያዘውን በጀት ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ አለመድረሱ ተገለጸ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሸዴ ትናንት በበጀት ድልድልና ተያያዥ ጉዳዮች ለፓርላማ (ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ሰጥተውት በነበረ ማብራሪያ ላይ፤ የትግራይ ክልል በጀት ጉዳይ አሁን ላይ ምን መኾን እንዳለበት መገመት እንደማይቻል ማመልከታቸው ተገልጿል።
ይህ በጀት ይለቀቅ አይለቀቅ የሚለው ወደፊት ውሳኔ የሚሰጥበትና የሕግ ትንታኔ የሚጠይቅ ይኾናል የተባለ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን በጀቱ በእንጥልጥል ላይ ስለመኾኑ ለማወቅ ተችሏል። በ2014 ክልሉ የተያዘለት በጀት 12 ቢሊዮን ብር እንደኾነም ተመልክቷል። (ኢዛ)



