Food oil

የምግብ ዘይት

በኢትዮጵያ ያሉ የዘይት ማምረቻዎች አቅም ከፍላጐት በላይ ቢኾንም እያመረቱ አይደለም
ብዙ ችግሮች መኖሩን ሚኒስትሩ ገለጹ

ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 28, 2021)፦ በአገር ውስጥ ያሉ የምግብ ዘይት ማምረቻዎች 1.25 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም ላይ ያለመኾናቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በምግብ ዘይት አቅርቦትና ተያያዥ ጉዳዮች በተደረገ ምክክር ላይ እንደገለጹት፤ እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ባሉባቸው በርካታ ተግዳሮቶች ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ ያለመኾኑ ነው።

በአገሪቱ 232 የምግብ ዘይት ማምረቻዎች ያሉና የማምረት አቅማቸው 1.25 (አንድ ነጥብ ሁለት አምስት) ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን ቢኾንም፤ አሁን ባሉበት ደረጃ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ያለመቻላቸው በአገር ውስጥ ያለውን ፍላጐት ለማሟላት አላስቻለም።

ከንግድ ሚኒስትሩ የዛሬ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፤ በ2014 በጀት ዓመት የአገሪቱ የምግብ ዘይት ፍጆታ 906 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚኾን ነው።

ይህ የሚያሳየው የአገሪቱ የዘይት ማምረቻዎች አገሪቱ በዓመት ከምትፈልገዊ ፍጆታ በላይ የማምረት አቅም ያላቸው መኾኑን ነው። ነገር ግን አሁንም በአገሪቱ የምግብ ዘይት አቅርቦት ከፍተኛ ተግዳሮት ከመኾንም አልፎ፤ አምስት ሌትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት ዋጋ ከ530 ብር በላይ ደርሷል። ይህ የኾነው ደግሞ በአገሪቱ ግዙፍ የሚባሉ ትላልቅ የዘይት ማምረቻዎች በተመረቁ ማግስት ነው።

የንግድ ሚኒስትሩ እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ባሉባቸው በርካታ ችግሮች በሙሉ አቅም እያመረቱ ያለመኾናቸው፤ በአንጻሩ ግን የማምረት አቅማቸው አገሪቱ በዓመት ከምትፈለገው ፍጆታ በላይ ነው መባሉ፤ እንዲሁም አሁን ያለው የዋጋ ውድነት ሲታይ የአገሪቱ የምግብ ዘይት አጠቃላይ ገበያና ሁኔታ እንቆቅልሽ አድርጐታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ