የጄኔራል ባጫ መግለጫ እያነጋገረ ነው
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለ ችግር በድርድር እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላት ፍላጐት እንደተጠበቀ ነው
በጦርነት እንፈታለን ከተባለም ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች
ግድቡ ከተነካ ግብጽና ሱዳንን ጠራርጐ ባሕር ይቀላቅላቸዋል
ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 26, 2021)፦ በሞስኮ የዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት በጦርነት ለመፍታት ፍላጐት የሌላት መኾኑን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷን ለሚደፍር ጠላት ግን ዝግጁ መኾኗን ገለጹ።
RT ከተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ሌ/ጄኔራሉ ያደረጉት ቃለምልልስ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለው ያለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ፍላጐት ያላት ስለመኾኑ ሲሆን፣ ችግሩን በጦርነት ለመፍታት መሞከር ግን መፍትሔ እንደማይኾን የገለጹበት ነው።
ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን ያለመግባባት በውይይት የመፍታት ፍላጐት እንደሌላት ያመለከቱት ጄኔራል ባጫ፤ ግብጾች ለውይይት መጥተው የመወያያ አጀንዳውን ውድቅ በማድረግ እስካሁን መቀጠላቸውም አስታውሰዋል። ነገር ግን ይህንን ችግር በጦርነት ለመፍታት እንደማይቻል በመግለጽም፤ ብቸኛው አማራጭ አይኾንም ብለዋል። ግብጾችም ያለውን ችግር በወታደራዊ መንገድ መፍታት እንደማይችሉም ጄኔራል ባጫ በዚሁ ቃለምልልሳቸው ገልጸዋል።
ግብጾች ግድቡን ለማጥቃት እንደማይሞክሩ ተናግረው፤ ቢሞክሩ እንኳን አለመግባባቱን ሊፈቱ እንዲሁም ግድቡን ሊያጠፉ እንደማይችሉም አመልክተዋል።
ግድቡ ጠንካራ በመኾኑ በቦምብ እና በተዋጊ ጀቶች ሊወድም አለመቻሉን በማከል፤ የግድቡን ጥንካሬ ደግሞ ግብጽ ራሷ ታውቃለች በማለት ችግሩ በጦርነት የሚፈታ ይኾናል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን ያለው ችግር በውይይት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው በመግለጽም፤ በተለይም ኢትዮጵያ የሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ሲጠናቀቅ የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠር፤ እንዲሁም የውይይቱ አጀንዳ ግድቡ ሳይኾን የውኃ ክፍፍሉ ኾኖ ሁሉም ወገን ለድርድር ይመጣል የሚል እምነታቸውንም ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።
ችግሩን በጦርነት ለመፍታት ቢሞከር ኢትዮጵያ ያላትን ዝግጅት በተመለከተም ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር አገርን ከጠላት ለመከላከል ዝግጁ መኾኗንና ሉዓላዊነቷን ሊደፍር የሚችልን ጠላት ሁሉ ለመመከት ዝግጁ መኾኗን አረጋግጠዋል።
ጄኔራሉ በዚህ ቃለምልልሳቸው የህዳሴ ግድብን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል አቅም ኢትዮጵያ ያላት መኾኑን ከማረጋገጥ በላይ፤ ግብጽም ብትኾን ግድቡን ለመምታት ትሞክራለች ብለው የማያምኑ መኾኑን አክለዋል። ነገር ግን እንዲህ ካለው ሐሳብ ይልቅ ግብጽና ሱዳን ማድረግ ያለባቸው ብለው ያስተላለፉት መልእክት፤ ሁለቱ አገሮች ግድቡ እንዳይመታ እና እንዳይፈርስ መከላከል ነው ያለባቸው የሚል ነው። ግድቡ ተመታ እና ፈረሰ ተብሎ ቢታሰብ ግብጽና ሱዳንን ይዞ የሚጠፋ ስለመኾኑም ሊያውቁ እንደሚገባ አክለዋል።
ይህንኑ ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም ግድቡ በያዘው ውኃ ሁለቱንም አገራት ጠራርጐ ሜዴትራንያን ባሕር ውስጥ ይቀላቅላቸዋል።
ይህ የጄኔራል ባጫ መግለጫ ከተሰማ በኋላ የግብጽ ሚዲያዎች ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ ነገሩን እያራገቡት ሲሆን፤ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረገ ኾኗል።
በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ፤ ግብጽ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ችግር በድርድር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትሞክራለች ብለዋል። ነገር ግን አገራቸው ግብጽ የውኃ ጥቅሟን የሚነካ ኃይልን ለመታገስ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን ችግር በወታደራዊ መፍትሔ ለመፍታት ይሞከራል የሚለው አመለካከት ሊኾን የማይችል ስለመኾኑ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽ ቢኾንም፤ ከግብጽ ወገን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ፀብ ጫሪ ድርጊቶቿ በተለያዩ መንገዶች መታየታቸው አልቀረም።
በዚህ ሳምንት የግብጹ ኤታማዥር ሹም በሱዳን ቆይታ ማድረጋቸውና ሌሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ነው የሚለውን ግብጽ ብታስተባብልም፤ በተግባር ግን በግልጽ የሚታዩ ድርጊቶቿ ኢትዮጵያ በተጠንቀቅ መቆም እንዳለባት የሚያመለክት ስለመኾኑ ብዙዎች እየገለጹ ነው። ከዛሬው የሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ቃለምልልስ መረዳት እንደሚቻለው ችግር ቢከሰት እንኳን ኢትዮጵያ ዝግጁ መኾኗን ነው። (ኢዛ)



