Fisseha Eshetu (PhD)

ፍስሃ እሸቱ (ዶ/ር)

- በግብርናና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት የ10 ቢሊዮን ብር አክሲዮን ሊሸጡ ነው
- ሚዲያም አንዱ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ዘርፍ ነው

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 16, 2021)፦ የቀድሞው የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትና ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ለመሰማራት ኢትዮጵያ መግባታቸው እና ለእነዚህ ኢንቨስትመንቶች አሥር ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው አክሲዮኖችን ለሽያጭ ያቀርባሉ ተብሏል።

ዶክተር ፍስሃ “ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” (ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር (PurposeBlack ETH Trading S.C)) የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአክሲዮን ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር የሚያስችላቸውን ፍቃድ ማግኘታቸውም ታውቋል።

135 የሚኾኑ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ በአሜሪካ የተቋቋመው ይህ ኩባንያ፤ ከኢትዮጵያ ውጭ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በተመሳሳይ ቢዝነስ የሚንቀሳቀስ ይኾናል ተብሏል።

ኩባንያውን በተመለከተ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ ይሰማራል ተብሎ የሚጠበቀው የእርሻና አግሮ ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ትላልቅ የሱፐር ማርኬቶች ግንባታን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ሚዲያም የኩባንያም ሌላ የኢንቨስትመንት መስክ መኾኑ ታውቋል።

ኩባንያው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪዎችን ይጠይቃል የተባሉትን ሥራዎች ለመሥራት እያንዳንዳቸው መቶ ብር ዋጋ ያላቸውን 100 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ይሸጣል። ይህም ለመሸጥ ያሰበው አክሲዮን ድምር የ10 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነው።

በዶክተር ፍሰሃ እሸቱ የተቋቋመው ይህ ኩባንያ በአሜሪካ በሚገኝ “ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” (Black Economy Excellence) በሚል መጠሪያ ካለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር ከአንድ ዓመት በላይ ሲሠራ የቆየ ስለመኾኑ ተገልጿል። ኩባንያው የአክሲዮን ሽያጩን በቀጣይ ሁለት ሳምንት ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ኩባንያው የሚፈልገውን ካፒታል ለማሰባሰብ ከአገር ውስጥ ሌላ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን ያለመ ሲሆን፣ ለዚህም ትልቅ ንቅናቄ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ንቅናቄ በተመለከተም የፊታችን ቅዳሜ “አብረን እንሥራ” በሚል መርኅ ትልቅ ዝግጅት ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ብላክ ኢኮኖሚክ ኤክሰለንስ የተሰኘው ይህ በመላው ዓለም ላይ ያሉ ጥቁር ሕዝቦች በምጣኔ ሀብት ራሳቸውን እንዲያሳድጉና የጥቁር ሕዝቦችን ዓለማቀፋዊ ተሰሚነትና ክብር ለማሳደግ እየጣረ ያለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መኾኑ ታውቋል። ይህ ተቋም በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለአንድ ቢሊዮን ጥቁር ሕዝቦች አገልግሎት የሚሰጡ የኢንቨስትመንትና የንግድ ተቋማትን በመገንባት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ በሒደቱም አንድ ሚሊዮን የሚኾኑ ጥቁር ሚሊየነሮች ለመፍጠር ማቀዱ ታውቋል።

ዶክተር ፍሰሃ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል ዩኒቨርሲቲ በመክፈት ፈር ቀዳጅ ናቸው። የመጀመሪያውን ዕለታዊ የግል ጋዜጣ (ዕለታዊ አዲስ) በማሳተም ይታወቃሉ።

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን ለሼክ መሐመድ አላሙዲና ለዶክተር አረጋ ይርጋው በመሸጥ ከአገር ወጥተው ለዓመታት በአሜሪካ ሲኖሩ ቆይተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ