Amhara Prosperity Party

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚቆሙበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደሚገኙ አስገነዘበ

ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 20, 2021)፦ በየትኛውም የአመለካከት ልዩነት ውስጥ ኾነን እንኳን ለውጭ ጠላት በአንድነት የመቆም የረዥም ዘመን ታሪክ ያለን መላ ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ ትናንት ታሪክ ለመሥራት በጋራ መቆም የግድ የሚለን ጊዜ ላይ ነን ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም በሚል ርዕስ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ፤ በተለይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና በተጽዕኖ እጅ ለመጠምዘዝ የሚያደርጉት ሙከራ ጐልቶ የወጣ በመኾኑ፤ ይህንን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ለመመከት ኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም እንደሚኖርባቸውም የሚያሳስብ ነው።

የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የበረታባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ብሎ የጠቀሳቸው ሦስት ጉዳዮች መኾናቸውንና እነዚህም የህዳሴ ግድብ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የቀጠለው የሕግ ማስከበር ዘመቻና መጪው የምርጫ (ምርጫ 2013) ሒደቶች መኾናቸውንም አመልክቷል።

በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች ላይም ሰፊ ማብራሪያ የሚሰጠው መግለጫ በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት የአማራ የጸጥታ ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ የሚለውንም የኮነነም ነው። እነሱ እንደሚሉት (የውጭ ኃይሎችን ነው) የአማራ የጸጥታ ኃይል አካባቢውን ለቅቆ ቢወጣ አሸባሪው ትሕነግ የተለያዩ እድሎች የሚያገኝ መኾኑንም ይገልጻል።

ከእነዚህ ውስጥ የአሸባሪው የትሕነግ (ሕወሓት) ቡድን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርለት መኾኑንና ነባርና አዳዲስ ሸማቂ ኃይሎችን በአካባቢው ለማንቀሳቀስ ነፃ መሬት ያገኛል የሚሉት ይገኝበታል። መግለጫው የራያን፣ የወልቃይትንና በአጠቃላይ የአካባቢውን ፖለቲካ ትኩሳት የዳሰሰ ሲሆን፤ በተለያየ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ትንኮሳዎች እየተደረጉ መኾኑን በማተት፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ ይቁሙ የሚለውን ቁልፍ መልእክቱን አስተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ምሁራን መማክርት የአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ተመሳሳይ ይዞታ ያለው መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል።

የአማራ መማክርት የአሜሪካ መንግሥት በአንቶኒ ጄ ብሊንከን በኩል የተሰጠው መግለጫ ኢ-ፍትሐዊ መኾኑንም አመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ