የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት አልቆመም
በደብረ ማርቆስ ሰሞኑን የተካሔደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ (ፎቶ፣ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተወሰደ)
በጅማ እና በደቡብ ክልል በአማሮ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች ንጹኀንን ገደሉ
ኢዛ (እሁድ ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 25, 2021)፦ በጅማ እና በደቡብ ክልል ደግሞ በአማሮ ልዩ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ሰዎች ስለመግደላቸው እየተገለጸ ሲሆን፤ ግድያው ብሔር ተኮር ስለመኾኑም በጥቃቱ ዙሪያ እየተሠራጩ ያሉት መረጃዎች እያመለከቱ ነው።
በጅማ ሊሙኮሳ ወረዳ፣ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ ቀበሌ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ዳኖ ቀበሌ በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከ መቶ ይደርሳል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ቢኾንም፤ እስካሁን ከገለልተኛ ወገን የሟቾቹን ቁጥር በትክክል ማረጋገጥ አልተቻለም።
ኾኖም ጥቃቱ ከሚያዝያ 14 ቀን ጀምሮ በተጠቀሱት አካባቢዎች እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ዘር ተኮር ጥቃት ስለመፈጸማቸው ተነግሯል።
በእነዚህ አካባቢዎች ስለተፈጸመው ጥቃት ዛሬ አጭር መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን፤ እስካሁን ስድስት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው አስተዳደር አስታውቋል። በእነዚህ አካባቢዎች ስለተፈጸመው ጥቃት ኮምሽኑ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጅማ ሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ ቀበሌ በሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በታጠቁ ኃይሎች ስለደረሰ ጥቃት ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ክልል፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ፣ ዳኖ ቀበሌ በሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ታጣቂዎች 6 ሰዎች እንደገደሉ የአካባቢው አስተዳደር አሳውቋል።
በኮሳ ወረዳ የደረሰውን አደጋ ተከትሎም በዕለቱ የክልልና የፌዴራል ጸጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል። ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል አካላት ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በቅርበት እየተነጋገረ ሲሆን፤ የክትትል ተግባሩን የሚቀጥል መኾኑን አሳውቋል።
ኮሚሽኑ በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እና የሰዎች ሞት ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቦ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተደጋጋሚነትና መስፋፋት የጸጥታ መዋቅሩ የመከላከል እና የዝግጁነት አቅም ከፍተኛ መሻሻል ሊደረግበት እንደሚገባ የሚጠቁም መኾኑን በአጽንኦት ጥሪ ያቀርባል ብሏል።
ይህ የኮሚሽኑ መግለጫ እንደሚያሳየው ከኾነ ብሔር ተኮር ጥቃት አሁንም ያለማቆሙን የሚያመለክት ኾኗል። በሌላ በኩል ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይቁም በሚል በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሚካሔደው የተቃውሞ ድምፅ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት የተቃውሞ ድምፆች ከተሰማባቸው ከተሞች ውስጥ ደብረ ማርቆስ፣ መርሃቤቴ፣ ግንደወይን ይጠቀሳሉ። (ኢዛ)



