ኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ጽኑ ሕሙማን ቁጥር የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች
ቫይረሱ በአሁኑ ጊዜ ባለባቸው ሰዎች ቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 6, 2021)፦ በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አሳሳቢ በሚባልበት በዚህ ሰዓት፤ በጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ ልትይዝ መቻሏ ተገለጸ። በአሁኑ ሰዓት ኮሮና ቫይረስ ባለባቸው ሰዎች ቁጥርም፤ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን እንደያዘች ነው።
በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይሎች አስተባባሪ ዶክተር ሚዛን ኪሮስ እንዳስታወቁት፤ የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ እና ኢትዮጵያ በኮቪድ 19 በሚያዙና ጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ እንድትኾን አድርጓታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንም አስተባባሪው አመልክተዋል።
በሽታው ያለባቸው እና በጽኑ ሕክምና ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ፤ የበሽታው ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መኾኑን ያስረዳል። ይህም የበሽታው ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቋሚ ስለመኾኑ ይኸው የዶክተር ሚዛን ገለጻ ያመለክታል።
በተለይ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡን አስተባባሪው ተናግረዋል። አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በሚፈለገው ልክ ምርመራዎች እየተካሔዱ ባለመኾናቸው እንጂ፤ በሌሎች ክልሎችም የበሽታው ሥርጭት እየጨመረ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ምልክቶች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።
በአገሪቱ ያለውን የቫይረሱ አጠቃላይ ትክክለኛ ሥርጭት ለማወቅ በቅርቡ ሰፊ አገራዊ ጥናት ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረና የጽኑ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣት በሕክምና መስጫ ማዕከላት የኦክስጅን እጥረት ማጋጠሙ እየተነገረ ነው። የሁኔታው አሳሳቢነት በሽታውን ለመከላከል በዓቃቤ ሕግ በኩል የአፍና የአፍንጫ ማስክ ማድረግን እና ሌሎች ጥንቃቄዎችን የማይተገብሩ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ ተላልፏል። እስከ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለ መረጃ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 219,381 የደረሰ ሲሆን፣ በጽኑ ሕመም ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 850 ደርሷል። በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 52,400 ደርሷል። (ኢዛ)



