ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍዋን አረጋገጠች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (2013 ዓ.ም.)
በአይቮሪ ኮስት 3 ለ 1 ተሸንፋም ቢኾን አልፋለች
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 30, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋገጠ። ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ የምታስተናግደው ካሜሮን ስትኾን፤ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት 2022 እ.ኤ.አ. ይካሔዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዛሬ ከአይቮሪ ኮስት ጋር ባደረገው ጨዋታ አቻ መውጣት የሚያሳልፈው ቢኾንም፤ በአይቮሪ ኮስት 3 ለ 1 ተሸንፏል።
ኾኖም ኢትዮጵያ ካለችበት ምድብ ዛሬ ጨዋታ ያደረጉት ማዳጋስካር እና ኒጀር አቻ መውጣት ወይም የኒጀር ማሸነፍ፤ ኢትዮጵያ ብትሸነፍም ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳልፋት ነበርና፤ ማዳካስካር እና ኒጀር እኩል በመውጣታቸው፤ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ነጥብ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ አስችሏታል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችው ከስምንት ዓመት በኋላ ሲሆን፣ እሱም በ2005 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2013) ነበር።
ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሲመሩ የነበሩት ጋናዊው ዳኛ ቻርልስ ቡሉ 80ኛው ደቂቃ ላይ ራሳቸውን ስተው በመውደቃቸው በቃሬ ተይዘው ከሜዳው በመውጣት በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። የኢትዮጵያ እና የአይቮሪ ኮስት ጨዋታም እንዲቋረጥ ተደርጓል። (ኢዛ)



