በቴዲ አፍሮ ችሎት ዳኛ ስም ስህተት ሦስት ጋዜጠኞች ታስረው አደሩ
(ተጨማሪ ዘገባ)
![]() |
| ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ |
|
| ጋዜጠኛ ሀብቴ ታደሰ |
ከሳሻቸው ፍትህ ሚኒስቴር ነው
ፍርድ ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ ታስረው ቢውሉም ችሎት አልቀረቡም
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. October 22, 2008)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በስልክ የጠራቸውን ሦስት ጋዜጠኞችን ቃላቸውን ተቀብሎ ልደታ በሚገኘው የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ፈጣን ችሎት ሊያቀርባቸው የሞከረ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ሊያቀርብ ባለመቻሉ ሦስቱም ጋዜጠኞች በተለምዶ ሦስተኛ ተብሎ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንዲያድሩ መደረጉን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አስረዳ።
የአርቲስት ቴዲ አፍሮን ክስ የሚያስችሉትንና የቀድሞውን ዳኛ ልዑል ገ/ማርያምን ተክተው ችሎቱን እያስቻሉ ያሉትን ዳኛ መሐመድ ዑመር የአባት ስም አሚን ሳኒ በማለት የእንቢልታ ጋዜጣ በመዘገቡ የተነሳ ፍትህ ሚኒስቴር ክስ መመስረቱን ለኢትዮጵያ ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰው ዘገባ ይጠቁማል።
ዳኛ መሐመድ ዑመር ያለፉትን ሁለት የቴዲ አፍሮ ችሎቶች ያስቻሉት ሲሆኑ፣ "መሐመድ አሚን ሳኒ" የሚባሉት ደግሞ የቅንጅት መሪዎች በታሰሩበት ጊዜ ከሳሽ ከሆኑት ሦስት ዓቃቤ ሕጎች ውስጥ አንዱ የነበሩት ናቸው።
የጋዜጣውን አሣታሚና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ፣ ምክትል አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሀብቴ ታደሰ እና አዘጋጅ ጋዜጠኛ አጥናፉ ዓለማየሁ ትናንት በስልክ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በደረሳቸው ጥሪ መሠረት ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ ወደተጠሩበት ያመሩ ሲሆን፣ ፖሊስ ቃላቸውን መቀበሉን ለመረዳት ችለናል።
ምንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ ፖሊስ ቃል ከተቀበለ በኋላ በዋስ የሚለቅ ቢሆንም፤ ፖሊስ ሦስቱንም ጋዜጠኞች ከምሣ ሰዓት በኋላ ላይ ልደታ ወደሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለት ፖሊሶች አጅቦ ወስዷቸዋል። በተጨማሪም የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ መስጠቱን ለማወቅ ችለናል።
ዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ከፍቶ ጉዳዩን እንዲያየው ለተፈለገው ”ፈጣን ችሎት” ተብሎ ለሚጠራው ማቅረብ እንዳልቻለ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ችለናል። ”ፈጣን ችሎት” ተብሎ በሚጠራው ችሎት የሚታዩ ክሶች ምንም ዓይነት ማስረጃ ለማያስፈልጋቸውና እጅ ከፍንጅ ሲቀሙ፣ ሲዘርፉ፣ ... የተያዙ ግለሰቦች ጉዳይ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
ጋዜጠኞቹ ሙሉውን ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ በሁለት ፖሊሶች ታጅበው የዋሉ ቢሆንም በ14ኛ ወንጀል ችሎት ”ፈጣን ችሎት” ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ችሎት ያልቀረቡ በመሆናቸው የክስ ቻርጅ አልተሰጣቸውም። አመሻሹ ላይም ፖሊስ የዋስትና መብታቸውን ሳያከብርላቸው በመቅረቱና ነገ ፍርድ ቤት እስከሚያቀርባቸው ድረስ አስሮ ሊያሳድራቸው እንደሆነ አረጋግጠናል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ጋዜጠኞቹ በእስር ላይ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገራቸውና ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ የሆነ አንድ የሕግ ባለሙያ፣ እንዲህ ያለውን ስህተት ጋዜጣው ”ዕርማት” ብሎ እንዲያወጣ የጉዳዩ ባለቤት በማሳሰብ፤ ጋዜጣው ዕርማቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ካላወጣው ወደክስ መሄድ እንደሚቻል አስረድተዋል። ዕርማቱ በአንድ ወር ውስጥ ከወጣ ግን ወደ ክስ መሄዱ እንደማያዋጣ አክለው ገልጸዋል።
የጋዜጠኞቹን ጉዳይ እየተከታተሉ የሚገኙ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት ከሆነ፤ ነገ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ችሎት እንደሚቀርቡና የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች ምግብና ልብስ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ወስደውላቸዋል። የጋዜጣው አሣታሚና ዋና አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ሁለቱ አዘጋጆችዋ እንዲለቀቁላትና እሷ እንድትታሰር ፖሊስን ብትጠይቅም አዎንታዊ ምላሽ ሳታገኝ መቅረቷን እነዚሁ ወገኖች ገልጸውልናል።
እንደነኝሁ ወገኖች ገለጻ ከሆነ፣ ”ፈጣን ችሎት” ተብሎ የሚጣራውን 14ኛ ወንጀል ችሎት የሚዳኙት ዳኛ አብርሃም ተጠምቀ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸውልናል። ዳኛ አብርሃም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ የቅንጅት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ታስረው በተከሰሱበት ጊዜ ዓቃቤ ሕግ እንደነበሩ አይዘነጋም።
እንቢልታ ጋዜጣ በሩት አሣታሚ ስር በየሣምንቱ ዓርብ እየታተመ የሚወጣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኪነጥበባዊ፣ ... የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የግል ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው የተመሰረተው ባለፈው ዓመት ታህሳስ 2000 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዕትሙን ያወጣው ታህሳስ 18 ቀን 2000 ዓ.ም. ነው። ጋዜጣው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነባቢነትንና በአንባብያን ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል።




