Sebhat Nega

አቦይ ስብሃት ነጋ

ጠበቆች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 22, 2021)፦ በዛሬው ዕለት ከቀድሞ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አዲስ ዓለም ባሌማ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በዛሬው ቀጠሮ ፍ/ቤት ቀርበዋል። ፍ/ቤት የቀረቡት የዓቃቤ ሕግ የቅድመ ምርመራ ምስክር ለመስማት ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ አቤቱታዎችን ያቀረቡበት ኾኗል።

በዕለቱ የአቶ ስብሃት እና የሌሎች የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ያቀረቡት አቤቱታ መካከል ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ማረፊያ ቤት እንዳንገባ ተከለከልን የሚለው ይገኝበታል። ከፍርድ ቤት የጥብቅና ፈቃዳችሁን አቅርቡ ብለውን ተመልሰናልም ብለዋል። ባልተመካከርንበት ሁኔታ ምስክር መሰማቱ ተገቢ ስላልኾነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ብለዋል።

ሌላው አቤቱታ፤ አምባሳደር አባይ ወልዱ ዓይናቸው እየተጋረደ ስለኾነ በግል እንዲታከሙ ይታዘዝ የሚል ሲሆን፤ አቶ ስብሃትም በግል እንዲታከሙ የታዘዘው ትእዛዝ ተፈጻሚ አልኾነም የሚል አቤቱታ አሰምቷል። ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ ምግብ ቅዳሜ እና እሁድ እንደሚገባላቸው በመጥቀስ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ እንዲፈቀድ ትእዛዝ ይሰጥልንም ሲሉ ጠይቀዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር ብዙ መኾኑን በመጥቀስም፤ ዕድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ስላሉ ለኮሮና እንዳይጋለጡ ታሳቢ ቢደረግ ሲሉም ጠበቆቹ አቤቱታ አቅረበዋል። ዓቃቤ ሕግም የተነሱ አቤቱታዎች ተገቢነት የሌላቸውና ጠበቆችም ባለፈው ሳምንት ተጠርጣሪዎችን ማግኘት ይችሉ ነበር በማለት ጉዳዩ በጠበቆቹ ቸልተኝነት የመጣ መኾኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።

ይህ የቅድመ ምርመራ ምስክር በመኾኑም በአፋጣኝ ማስረጃ ለማቆየት ምስክር መስማት እንዳለበት በመጥቀስ፤ በጠበቆች የተነሳው አቤቱታ ጉዳዩን ለማዘግየት በማሰብ ነው በሚል የጠበቆቹን አቤቱታ ተቃውሟል።

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ፤ ጠበቆች ሥነምግባር በጎደለው እና የችሎቱን ክብር ባልጠበቀ መልኩ ተከራክራችኋል በሚል ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ የተነሱትን አቤቱታዎች መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት የይደር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ