ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)

በአገር ክህደት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለውና ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ክስ ከተመሠረተባቸው ሰባት ጄኔራሎች ዋና አስተባባሪው ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)፣ (መኻል ላይ ቀይ ያደረገው)

ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትእዛዝ ተሰጠ

ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 17, 2021)፦ በሰሜን ዕዝ ጦር ራዲዮ መገናኛን ለሕወሓት ቡድን በመስጠት፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ እና በተያያዥ ወንጀለኞች ተጠርጥረው ጉዳያቸው እየታየ ያለው እነ ሜጀር ጀነራል ገብረመድኅን ፍቃዱ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ኾኖ ወደ ማረሚያ ቤት ይውረዱ ተባለ።

የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ የተመለከተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብር እና ሕገመንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፤ የዓቃቤ ሕግን መቃወሚያ በመመርመር ዋስትና የማያሰጥ በመኾኑ፤ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ተከሳሾቹ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

በእነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን መዝገብ ዓቃቤ ሕግ ከከሰሳቸው 21 ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ውስጥ፤ ሰባቱ ለፍ/ቤቱ በጠበቃቸው በኩል የዋስትና ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያመለክተው መረጃ፤ ዓቃቤ ሕግ ግን የተፈጸመው ወንጀል የሰው ሕይወት ያለፈበት በመኾኑ ዋስትናው ሊፈቅድ አይገባም ብሎ ተከራክሯል።

በዛሬው ችሎት የሁለቱን ወገኖች ክርክር የተመለከተው ፍ/ቤቱ፤ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ እና ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ያዘዘ ሲሆን፤ ተለዋጭ ቀጠሮም ሰጥቷል። ተለዋጭ ቀጠሮው መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፤ በዚህ ቀጠሮ በችሎቱ ያልተገኙ ተከሳሾች በተገኙበት ክሱን የሚመለከት መኾኑንም ለማወቅ ተችላል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ