ኦነግ አዲስ ሊቀመንበር መምረጡን ገለጸ
አዲሱ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ (በመድረኩ ላይ ከተቀመጡት በግራ ያሉት)፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ (በምስሉ ላይ በቀኝ)
አቶ ዳውድ ኢብሳ የተቃውሞ ድምፅ አሰምተዋል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 15, 2021)፦ በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሎ ውዝግብ ውስጥ የቆየው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አዲስ ሊቀመንበር መምረጡን አስታወቀ። ኦነግን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ አራርሶ ቢቂላ ናቸው።
ባለፉት ሁለት ቀናት ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሔድ የቆየው ኦነግ፤ አቶ ብርሃኑ ለማን እና አቶ ቀጄላ መርዳሳን ደግሞ የግንባሩ ምክትል ሊቀመናብርት ኾነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል ተብሏል።
በሁለቱ ቀናት የግንባሩ ጉባዔ 43 ቋሚ እና አምስት ተለዋጭ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም ምርጫ አካሒዷል።
ዛሬ ሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በታወቀው የግንባሩ የምርጫ ሒደት ላይ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን አጠቃላይ የተካሔደው ጉባዔ አሳታፊ ያልኾነና ተቀባይነት የሌለው ነው ብሎታል።
ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በቀጣዩ ምርጫ እንደማይሳተፍ ያስታወቀ ሲሆን፤ አሁን የኦነግ ሊቀመንበር ኾነው የተመረጡት አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመሩት ኦነግ ደግሞ፤ በምርጫው መሳተፍ አለመሳተፉን የሚያረጋግጥ መረጃ አልተገኘም። ከሰሞኑ ጉባዔ በፊት አቶ ቄጄላ ኦነግ በምርጫው መሳተፍ አለመሳተፉ አጠራጣሪ መኾኑንና ይኽም አቶ ዳውድ ኢብሳ የፈጠሩት ችግር ነው ሲሉ ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁለቱ የኦነግ ቡድኖች አመራሮች መኻል የተፈጠረውን ያለመግባባትን ልዩነት ለመፍታት የሚቻለው የግንባሩን ድርጅታዊ ጉባዔ አንድ ላይ በማካሔድ መኾኑን የሚያመላክት ውሳኔ ሰጥቶ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። (ኢዛ)



