የብሮድካስት ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሥራ ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነገረ
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ
ምክንያታቸው ይፋ አልተደረገም
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 8, 2021)፦ ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ሥራ ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው እየተነገረ ነው።
እንደ ምንጮች ገለጻ ከኾነ፤ ዋና ዳይሬክተሩ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው፤ የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቁ ነው።
ከኃላፊነት ለመልቀቃቸው ምክንያት የኾናቸው ጉዳይ ባይታወቅም፤ በኃላፊነት ቦታው ላይ ላለመቆየት የመልቀቂያ ደብዳቤ ስለመጻፋቸው እኚሁ ምንጮች ያመላክታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ጌታቸው፤ ባለሥልጣኑን መሥሪያ ቤት በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ዳይሬክተሩ ይፋዊ ማረጋገጫ ያልሰጡበት ቢኾንም፤ አንዳንድ ሚዲያዎች ግን የሥራ የመልቀቂያ ጥያቄውን ስለማስገባታቸው፤ ኾኖም ግን የመንግሥት ውሳኔን የሚጠብቅ ነው የሚል ምላሽ ከዶክተር ጌታቸው ስለማግኘታቸው ጠቅሰዋል። (ኢዛ)



