መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት እርምጃ እወስዳለሁ አለ
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ
አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት የንግድ አሻጥር ነው ብሎ መንግሥት ያምናል
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 1, 2021)፦ መንግሥት አሁን ያለውን የዋጋ ንረትና ገበያውን ለማረጋጋት የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱንና ምርቶች በመንግሥት ድርጅቶች በኩል ሊከፋፈል እንደኾነም አስታውቋል። አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት የንግድ አሻጥር ነው ብሎ መንግሥት እንደሚያምን ተነገረ።
ከኑሮ ውድነትና ገበያን ከማረጋጋት አኳያ መንግሥት ስለሚወስደው እርምጃ በይፋ መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ናቸው።
ከወቅታዊው የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት ይወስዳል ብለው ከገለጹዋቸው መፍትሔዎች መካከል ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለመንግሥት ድርጅቶች በማቅረብ እንዲከፋፈል ማድረግ ነው።
መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት ያስችለኛል ያለውን የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን እንደሚተገብር ያመለከቱት ዶ/ር ኢዮብ፤ ገበያን ያረጋጋሉ የተባሉ ምርቶችን በ“አለ በጅምላ” በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች በማስገባት ለማከፈፈል አቅዷል።
ይህንኑ እቅዱን ለማስፈጸምም መንግሥት ከዚህ በፊቱ በተለየ ጣልቃ በመግባት በምርቶቹ ሥርጭትና ክፍፍል ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ስለመኾኑ ይኸው የዛሬው (ሰኞ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም.) የሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ ያመለክታል።
በቅርቡ ከተደረገው የነዳጅ ጭማሪ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉት ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት የንግድ አሻጥር ነው ብሎ መንግሥት ያምናል ብለዋል።
የንግድ ሥርዓቱ ችግርም ለዋጋ ንረቱ አንድ መንሥኤ ስለመኾኑ ከማብራሪያው ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፤ አሁን ላይ ያለው የዋጋ ንረት ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ተከማችቶ የመጣ የዋጋ ንረት ውጤት ነው ተብሏል። (ኢዛ)



