የኢፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

የኢፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

አብዛኞቹ በቀድሞ የሕወሓት መኮንኖች የተቋቋሙ ነበሩ

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 12, 2020)፦ የጁንታው የሕወሓት ቡድን ተልዕኮ በማስፈጸም ተደርሶባቸዋል የተባሉና ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ሲሠሩ የተደረሰባቸውን 14 የግል የጥበቃ ኤጀንሲዎችን ማገዱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

ከተልዕኮዋቸው ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው እነዚህ ኤጀንሲዎች ከጁንታው ሕወሓት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም የተለያዩ ግለሰቦችን ወደ ኤጀንሲዎቹ አስርገው በማስገባትና የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፤ በሕብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሴሩ መኾኑ ስለተደረሰባቸው እንዲታገዱ እንደተወሰነም መግለጫው ያመለክታል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች እንዲታገዱ ተወሰነ፡፡

እንደሚታወቀው የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች የግልና የመንግሥት ተቋማትን ለመጠበቅ ከመከላከያና ከፖሊስ በጡረታና በክብር የተቀነሱ የሠራዊት አባላት የጸጥታ ሥራ ላይ ካላቸው ልምድ በተጨማሪ ተገቢውን ሥልጠና አግኝተው ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሚሰጣቸውን የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድና ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት የሚፈለገውን መስፈርቶች አሟልተው የመንግሥትና የግል ተቋማትን እንዲጠብቁና አገራቸውን፤ እንዲሁም ራሳቸውን እንዲጠቅሙ በሚያስችል ሁኔታ መቋቋማቸው ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ የግል የጥበቃ ኤጀንሲዎች የተቋቋሙበትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው፤ ከቀጠሯቸው የጥበቃ አባላት መካከል ለሌላ እኩይ ተግባር የመረጡዋቸውን በመመልመል፣ ለተቋም ጥበቃ የተሰጣቸውን የጦር መሣሪያ በማስታጠቅና በማሰማራት በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ አካላት ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተንቀሳቀሱ መኾኑ ተደርሶባቸዋል፡፡

ለአብነትም ከአሳለፍነው 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን እነዚህ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች በቀጠሯቸው የጥበቃ አባላትና ተባባሪዎቻቸው ባንኮችንና የተለያዩ ድርጅቶችን ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ቆይተዋል። በዚህም ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብና ንብረት ዘርፈዋል፤ እንዲዘረፍም አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተቋማቱን እንዲጠብቁበት የታጠቁትን በርካታ የጦር መሣሪያ ይዘው እንደጠፉም ተረጋግጧል። እነዚህ ከተልዕኮአቸው ውጭ እንደሚንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ይህም አልበቃ ብሏቸው፤ አሁን ባለው ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ በጁንታው የሕወሓት ወንበዴ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም፤ የተለያዩ ግለሰቦችን ወደ ኤጀንሲዎቹ አስርገው በማስገባትና የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ በሕብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥቃት ለመፈጸም እያሴሩ መኾኑ ተደርሶበታል።

ስለኾነም ከዚህ ቀጥሎ ስማቸው የተገለጸው የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች፦

1. ንስር የሰው ኃይል እና የጥበቃ አገ/ኃ/የተ/የግ/ማ
2. አጋር የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
3. ስብኃቱና ልጆቹ የንብረት አስ/ጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
4. ሰላም ሴኩሪቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ
5. ኃይሌ ተክላይ እና ጓደኞቻቸው የጥበቃ አገልግሎት ህ/ስ/ማ
6. ክፍሌ ጎሳዬ ሃጎስ እና ወ/ገብርኤል የጥበቃ አገልግሎት ሽርክና /ማ
7. ዮናስ፣ ሮዛ እና መብርሂት የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሽ/ማ
8. ሃየሎም እና ብርሃኔ የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሸ/ማ
9. ደመላሽ፣ ሃፍቱ እና ጓደኞቻቸው የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሸ/ማ
10. ህሉፍና ሃለፎም የጥበቃ አገ/ህ/ሽ/ማ
11. ዋልታ የጥበቃ የሰው ኃይልና ኮሚሽን ኃ/የተ/የግ/ማ
12. ሴፍ የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
13. አትላስ ጠቅላላ አገ/ኃ/የተ/የግ/ማ
14. ጎሕ የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ

ለአገርና ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ሲባል ሥራቸውን እንዲያቆሙ የተወሰነና እስከአሁን ባለው አገር የማተራመስና ሕገ-ወጥ ሥራቸው በሕግ የሚጠየቁ መኾኑን እየገለጽን፤ ስማቸው ከላይ የተገለጸው የጥበቃ ተቋማት በአስቸኳይ ሥራቸውን አቁመው ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፖርት እንዲያደርጉ እናሳውቃለን፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የግልም ኾነ የመንግሥት አካል ከነዚህ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ምንም ዐይነት ቅጥር እንዳይፈጸም የተከለከለ መኾኑን እንገልጻለን፡፡

በመጨረሻም ከላይ ስማቸው በተገለጸው የግል ጥበቃ ኤጀንሲ ሥር ተቀጥረው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ያሉ ሠራተኞችን በተመለከተ ተገቢውን ልየታ በማድረግ፤ ማስተካከያ እስኪወሰድ ድረስ በተመደቡበት ቦታ የጥበቃ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲሠሩና የሚጠብቋቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት ኋላፊዎችም በተሰጠው መግለጫ መሠረት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርጉ ኾኖ፤ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና የግል ጥበቃ ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት በማድረግ ቀጣይ በሚሰጡ የሥራ መመሪያዎች ብቻ ሊሠሩ እንደሚገባ በጥብቅ እናሳስባለን።

የኢፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ