ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)

በአገር ክህደት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለውና ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ክስ ከተመሠረተባቸው ሰባት ጄኔራሎች ዋና አስተባባሪው ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)፣ (መኻል ላይ ቀይ ያደረገው)

በአገር ክህደት ጭምር ይጠየቃሉ

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 12, 2020)፦ የሰሜን ዕዝን የራዲዮ መገናኛ በመጥለፍ የተጠረጠሩት የመከላከያ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱን ጨምሮ ሰባት ጄኔራሎች አገርን በመክዳት ወንጀልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በማሰብ ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በዛሬው ዕለት በአገር ክህደትን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሜ/ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ ሌላ፤ የመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ የደቡብ ዕዝ የሰው ኃይል ልማት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ገብረዮሐንስ ዳርሲኒዮስ፣ የሰሜን ዕዝ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ኢንሱ ኢጳጆ ረሾን ይገኙበታል።

በአጠቃላይ በአገር ክህደት ወንጀልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ማሰብ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥራ ውለው፤ በዛሬው ዕለት (ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው።

የፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ መንግሥትና ሕዝብ የጣሉባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፤ ትግራይ ክልል ከሚገኘው ፀረ-ሰላም ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል፤ በመከላከያ ጦር ውስጥ ሴሎችን በማደራጀት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜን ዕዝ ራዲዮ ግንኙነት ማቋረጣቸውን ገልጿል።

በዚህ አድራጎታቸውም ሠራዊቱ እርስ በእርስ እንዳይገናኝ፤ እንዲሁም በጦሩ ላይም የሞት፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል። የጦር መሣሪያ እንዲዘረፍም ማድረጋቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን የፈጸሙ ስለመኾኑ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱም የወንጀሉን ክብደትና በአገር ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ወንጀል በመኾኑ ለፖሊስ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ