L. Gen. Bacha Debele

ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት (ፎቶ፣ ከኢቲቪ ስክሪን ሹት)

ድርጊቱን የፈጸሙትና የጁንታው ተባባሪዎች የሠራዊቱ አባላት፣ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻዎች እና የኦነግ ሸኔ ናቸው

ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 10, 2020)፦ በመቀሌ የመሸገው የሕወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት፤ የተሰዉ የአገር መከላከያ ሠራዊትን አስከሬን አውሬ እስከማስበላት የደረሰ ዘግናኝ ተግባር የተፈጸመበት ጭምር እንደነበር ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ አስታወቁ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ የሚካሔድባቸውን የጦር ቀጠናዎችን ከጎበኙ በኋላ ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፤ የሕወሓት ማፊያ ቡድን አገሩን ሲጠብቅ የነበረውን ሠራዊት ጨፍጭፎ ግፍ ሠርቷል ብለዋል።

ይህንን ዘግናኝ ተግባር ለመፈጸም በዋናነት በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩ ትግርኛ ተናጋሪ በኾኑ አባላት አማካኝነት እንዲፈጸም የተደረገ ጭምር መኾኑን የገለጹት ሌ/ጄኔራል ባጫ፤ ከባንዳው የሕወሓት ቡድን ሦስት ተልእኮ መፈጸማቸውን ጠቅሰዋል።

ድርጊቱን የፈጸሙትና የጁንታው ተባባሪ የኾኑት የሠራዊቱ አባላት፣ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻዎች እና የኦነግ ሸኔ መኾናቸውን አስረድተዋል።

ተልእኳቸውም ሠራዊቱን ከውስጥ ማፍረስ፣ ሠራዊቱን መውጋት እና ማዘናጊያ የሽምግልና ሥራ የሚሉ እንደነበር ያስረዱት ጄኔራሉ፤ እነዚህን ተልእኮዎችን ሁሉንም ስለመፈጸማቸው ጠቅሰዋል።

በዚሁ መግለጫቸው ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ የሰሜን ዕዝን ለማፍረስ በማቀድ መቀሌ የመሸገው ጁንታ ቡድን በዕዙ ውስጥ የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎችን በመጠቀም የፈጸመው መኾኑ ገልጸዋል።

የጁንታው ቡድን የወታደሩ ራሽንና ደምወዝ መላኩን ቀድመው የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ፤ የሰሜን ዕዝ ከየትኛውም ሠራዊትና ከማዕከል ጋር እንዳይገናኝ የራዲዮ መገናኛውን በማቋረጥ ወደ ጥቃቱ እንደተገባ የሌ/ጄኔራል ባጫ ማብራሪያ አመልክቷል።

ይህንን የራዲዮ መገናኛ እንዲቋረጥ በማድረግ ሁነኛ ሚና የተጫወተው ደግሞ ዋና የራዲዮ መገናኛ ኃላፊው መኾኑንም ገልጸዋል።

የራዲዮ ግንኙነቱ ከተቋረጠ በኋላ የ21ኛው ክፍለ ጦር አዛዥን ጨምሮ የተወሰኑ የጦር አመራሮችን በማፈን፤ በተለይም አጋዥ ኃይል የሚባለውን እና ለ21 ዓመታት የአገሩን ዳር ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን ሠራዊት፤ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጨፍጭፈውታል በማለት የተፈጠረውን አሳዛኝ ድርጊት ገልጸዋል።

ለ21 ዓመታት አብረዋቸው በነበሩ ሰዎች ጭምር መወጋታቸውና ጥቃቱም ሠራዊቱ ምንም ዝግጅት ባላደረገበት ወቅት የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ቢከሰትም፤ ሠራዊቱ መሣሪያ በመንጠቅ ጭምር ተጋድሎ አድርጓል።

ሁኔታውን ዘግናኝ የሚያደርገው አሳዛኝ ተግባር ደግሞ፤ አድብቶ በተፈጸመው ጥቃት መሥዋእት የኾኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አስከሬን ላይ የተፈጸመው ነው። ይህንንም ጄኔራሉ “እነዚያን የተሰዉትን የመከላከያ አባላት ከሬሳቸው ላይ ልብሳቸውን አውልቀው ራቁታቸውን ለፀሐይ አሰጡት” በማለት አስረድተዋል። ይህ ሬሳ እስከዛሬ ድረስ አልተቀበረም። ፈንድቶ የአሞራና የጅብ ሲሳይ ስለመኾኑም የሁኔታውን አሳዛኝነት በቁጭት ገልጸዋል። ይህ ጀግንነት ያለመኾኑን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።

በዚህ አረመኔ ቡድን የተፈጸመውን ጥቃት እና ድርጊት የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ፤ ሬሳው ላይ እንደጀግና መዘፈኑ ነው። እንዲህ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሠራዊቱን ቁጭት ውስጥ የከተተው እንደኾነ በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት የአገር መከላከያ ሠራዊቱ በጁንታው ቡድን ጦር ላይ እርምጃ እየተወሰደና እየተደመሰሰ መኾኑንም ጄኔራሉ አስታውቀዋል። ዛሬ ወይንም ነገ የተለያዩ የድል ዜናዎች ትሰማላችሁም ብለዋል።

ይህ የዛሬው የሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ እያደረገ ያለውን ጥቃትና ግስጋሴ ያመለከተም ነበር። በሌላ በኩል ጁንታው አለኝ ብሎ የሚያወራው መሣሪያ ተራ ፕሮፖጋንዳ መኾኑን የሚያመለክት ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል። የሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌን የዛሬውን መግለጫ ለመመልከትና ለማድመጥ፤ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ