ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ)

ግብረ ኃይሉ እንዳስፈላጊነቱ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባም ኾነ እንዳይወጣ ትእዛዝ መስጠት ይችላል

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 5, 2020)፦ አዋጁ ተፈጻሚ በሚኾንበት ክልል ውስጥ ፖሊስ ወይንም ሌላ ማንኛውም የጸጥታ ኃይል ትጥቁን እንዲፈታ ትእዛዝ መስጠት የሚችል መኾኑ ተገለጸ። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ ግብረ ኃይሉ አካባቢውን ለመቆጣጠርና ሰላምን ለማስፈን አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣንም እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ አስፈላጊ ኾኖ ሲያገኘው ማንኛውንም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባም ኾነ እንዳይወጣ ትእዛዝ መስጠት እንደሚችልም በዛሬው ማብራሪያቸው አመልክተዋል።

ከዚህም ሌላ ሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣልና የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስን መከልከል እንዲችል ለግብረ ኃይሉ ሥልጣን እንደተሰጠውም ታውቋል።

አዋጁ የሚጸናበትን ጊዜ፣ የአፈጻጸም ወሰንና አዋጁን በሚያስተገብረውና በሚያስፈጽመው ግብረ ኃይል ሥልጣንና ተግባር ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ አዋጁን የማስፈጸምና የማስተግበር ሥልጣን የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል መኾኑን እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም መኾኑን አስታውሰው፤ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም ለጦር ኃይሎች በጠቅላይ አዛዥ እንደሚኾንም ጠቅሰዋል።

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአፈጻጸም ወሰን በዋናነት በትግራይ ክልል ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ ግብረ ኃይሉ ሊያሰፋውና ሊያጠበው እንደሚችልም የተሰጠው ማብራሪያ ያመለክታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ