የወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሹም ሽረት
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
ሰባት የቢሮ ኃላፊዎች በአዲስ ተተክተዋል
ከአሥሩ ክፍለ ከተሞች ሥራ አሥፈጻሚዎች ሦስቱ ብቻ ቀርተዋል
ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 20, 2020)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ሌሎች ከፍተኛ የከተማው ቢሮ ኃላፊዎችን በአዲስ የተካ ሹመት ተሰጠ። ከአሥሩ የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ሦስቱ ብቻ ባሉበት እንዲቀጥሉ ተደረገ። ሹመቱን የሰጡትና ያጸደቁት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ከተደርጉ ሹም ሽሮች አብዛኛውን የኃላፊነት ቦታዎች የነካ ነው በተባለው ሹም ሽር፤ ምክር ቤቱን በአፈ ጉባዔነት ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ዘርፈሸዋል ንጉሤ ለሁለት ዓመት ከአራት ወር በአፈ ጉባዔነት ያገለገሉትን ወይዘሮ አበበች ነጋሽን ተክተው ተሹመዋል። ከዚህም ሌላ በምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅራቢነት ስምንት ከፍተኛ ሹመቶች የቀረቡለት የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤ የቀረቡለትን ሹመቶች በሙሉ አጽድቋል።
በዚም መሠረት አቶ ጥራቱ በየነ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ ኾነው ተሹመዋል።
ዶ/ር መስከረም ፈለቀ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኃላፊ፣ ኢንጂንየር አያልነሽ ኃይለማርያም የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣ ዶ/ር መስከረም ምትኩ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ዶ/ር ሚልኬሳ ጃጋማ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተፈራ ሞላ የሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ ኃላፊ እና አቶ ሙሉጌታ ተረፈ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ኾነው ተሹመዋል።
በከተማው አስተዳደር የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲኾኑ ከተሾሙት ሌላ፤ ከፍተኛ ለውጥ የተደረገበት ሹም ሽር የተደረገው በክፍለ ከተሞች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ላይ ነው።
ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በጸደቀው የክፍለ ከተሞች የዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት መሠረት፤ ከአሥሩ ክፍለ ከተሞች የሰባቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል። በቀደመው ሹመታቸው የቀጠሉት የሦስት ክፍለ ከተሞች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሲሆኑ፤ አሥራ አንደኛ ክፍለ ከተማ ኾኖ ዛሬ ለጸደቀው ለአዲሱ “ለሚ ኩራ” ክፍለ ከተማም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሹሟል።
ክፍለ ከተሞችን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለመምራት ዛሬ በተሰጠው ሹመት መሠረት፤ ወይዘሮ ሽታዬ መሐመድ የልደታ፣ ወይዘሮ ነፃነት ዳባ የነፋስ ስልክ፣ አቶ ሙሉቀን ታረቀኝ የኮልፌ፣ አቶ አባዌ ዮሐንስ የጉለሌ፣ ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድ የአቃቂ ቃሊቲ፣ ዶ/ር እመቤት ጌታነህ የአራዳ፣ አቶ አስፋው ተክሌ የየካ፣ እንዲሁም አቶ ኤልያስ መሐመድ የለሚ ኩራ (አዲሱ ክፍለ ከተማ) ክፍለ ከተሞች ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመኾን እንዲያገለግሉ ተሹመዋል።
በዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸው እንዲቀጥሉ የተወሰነላቸው አቶ ጀማል ረዲ የቂርቆስ፣ አቶ መኮንን አምባዬ የቦሌ እና አቶ ይታየው ደጀኔ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው። (ኢዛ)



