Ethio Telecom

ኢትዮ ቴሌኮም

40 በመቶ ለውጭ ኩባንያዎች ይሸጣል
መንግሥት 55 በመቶውን ድርሻ ይይዛል
ለኢትዮጵያውያኖች አምስት በመቶ ድርሻ ይሸጣል

ኢዛ (ሰኞ ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 7, 2020)፦ በኢትዮጵያ በመንግሥት ይዞታ ሥር ከሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የኾነው ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ በአንዳንድ ወገኖች ጥያቄ እያስነሳ ቢኾንም፤ የኩባንያው 40 በመቶ ድርሻ ለውጭ ኩባንያዎች እንዲተላለፍ ውሳኔ ላይ ስለመደረሱ ታውቋል።

ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ማሻሻያ ሥራዎች ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል ለማዛወር እየተሠራ ባለው ሥራ 40 በመቶው ለውጭ ኩባንያ እንደሚሸጥ ወይም የባለቤትነት ድርሻው የሚዛወር ሲሆን፣ አምስት በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያውያን እንዲያዝ የሚደረግ መኾኑ ተነግሯል።

መንግሥት በኢትዮ ቴሌኮም የሚኖረው የባለቤትነት ድርሻ 55 በመቶ ኾኖ የሚቀጥል ስለመኾኑም በዚሁ መድረክ ላይ ተገልጿል።

ለኢትዮጵያውያን ዜጐች የተመደበው የአምስት በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በአክሲዮን ሽያጭ የሚሸጥ እንደሚኾንም ታውቋል። በዚህ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተገኙ ሲሆን፤ ዘርፉን ሊብራላይዝድ ማድረግ ሒደቱ የፖሊሲ ግፊት የሌለበት እና በአገር በቀል ኢኮኖሚ የማሻሻያ አቅጣጫዎች ላይ የተመሠረተ መኾኑን አመልክተዋል።

የአገሪቱን የቴሌኮም ዘርፍ ለማዘመንና የኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለማዛወር ለሁለት አዳዲስ ኦፕሬተሮችም ፍቃድ እንደሚሰጥ በዛሬው መድረክ ላይ ተነግሯል። ፈቃድ መስጠትም ሆነ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል የማዛወሩ ሥራ ከሌብነት በጸዳ እና አገር በሚጠቅም መልኩ እንደሚከናወንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል የማዛወሩ ሥራ ከተለያዩ ወገኖች ጥያቄ እያስነሳ የቆየ ሲሆን፤ ይህንን ግዙፍ የአገር ሀብት በዚህ መልክ ማስተላለፉ ተገቢ አለመኾኑንም ያመለክታሉ።

ከጥቂት ወራት በፊት ኢዜማ የቴሌ ለመሸጥ ጥድፊያ የማያስፈልግና መሸጡ ጉዳት እንዳለው በይፋዊ መግለጫ አቋሙን ማስታወቁ አይዘነጋም።

ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አሠራሩ ከፍተኛ እመርታ እያሳየና አገልግሎትን እያሻሻለ ዓመታዊ ትርፉንም እያሳደገ ከመምጣቱ አንጻር፤ ኩባንያው መሸጥ የለበትም የሚለውን አመለካከት እያጐላው ስለመምጣቱ መገንዘብ እየተቻለ ነው። የዛሬው መረጃ ግን መንግሥት በከፊል የባለቤትነት ድርሻውን ለማዛወር የቆረጠ መኾኑን አመልክቷል።

ኢትዮ ቴሌኮም 2012 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን በቅርቡ ይፋ እያደረገው 47.7 (አርባ ሰባት ነጥብ ሰባት) ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንና፤ ይህም ገቢ ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 31.4 (ሠላሳ አንድ ነጥብ አራት) በመቶ ብልጫ ያለው ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ