የኢዜማ ጋዜጣዊ መግለጫ በፖሊስ ታገደ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላ ጋር ተያይዞ ፓርቲው ዛሬ መግለጫ ሊሰጥ ነበር
ኢዛ (ዓርብ ነኀሴ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 28, 2020)፦ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ኢፍትሐዊ ዕደላን በተመለከተ ሲያዘጋጀው የነበረው ጥናት ላይ የቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ ታከለ ኡማ ጽሕፈት ቤት፤ የመሬት ልማት ቢሮና የቤቶች ኤጀንሲን ምላሽ ለማካተት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ቢያጣም፤ በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ላይ ሊሰጥ የነበረው መግለጫ በፖሊስ ታገደ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ ዓርብ ነኀሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ማገዱን ፓርቲው አስታወቀ።
ጋዜጠኞችና የኢዜማ አመራሮች በራስ ሆቴል ቀድመው የተገኙ ቢኾንም፤ የቂርቆስ ፖሊሶች መግለጫው ሊሰጥ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በስፍራው በመገኘት፤ ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት እንደማይቻል በማሳወቅ የኢዜማ አመራሮችና ጋዜጠኞች አዳራሹን እንዲለቁ አስገድደዋቸዋል።
የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ከእገዳው በኋላ እንዳስታወቀው፤ ፓርቲው ከዚህ ቀደም ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ እንደሚያደርገው ለራስ ሆቴል እና ለሰላም ሚኒስቴር በደብዳቤ ቁጥር ኢዜማ/695/12 አስቀድሞ ማስታወቁን ገልጿል።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት እንዳስታወቀው፤ አዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ኢፍትሐዊ ዕደላን በተመለከተ ያጠናውን ጥናት በተመለከተ፤ የፊታችን ሰኞ ነኀሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት በማኅበራዊ ሚዲያ ያስተላለፈው ሙሉ መልእክት ከዚህ በታች ቀርቧል። (ኢዛ)
እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም! - ኢዜማ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (#ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራን እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላን በተመለከተ የሚደርሱትን ጥቆማዎች በመቀበል ጉዳዮን የሚመረምር ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። የጥናቱን ውጤት ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ ዛሬ ዓርብ ነኀሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ ነበር።
ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲዘጋጅ ከዚህ ቀደም ጋዜጣዊ መግለጫ ስንሰጥ እንደምናደርገው ሁሉ ጋዜጣዊ መግለጫው ለሚደረግበት ራስ ሆቴል እንዲሁም በደብዳቤ ቁጥር ኢዜማ/695/12 ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር አስቀድመን አሳውቀናል።
ፓርቲያችን ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ ለመከታተል እና ለሕዝብ ለማድረስ የተጠሩ ጋዜጠኞች ከተባሉት ሰዓት ቀድመው በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ሲሆን፤ ብዙዎቹም የቀረጻ መሣሪዎቻቸውን አሰናድተው የመግለጫውን መሰጠት በመጠባበቅ ላይ እያሉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባል መኾናቸውን የገለጹ የፖሊስ አባላት መግለጫው መሰጠት እንደማይቻል በማሳወቅ፤ ጋዜጠኞቹ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል። ፖሊሶቹ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለማስቆም የሰጡት ምክንያት፤ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲካሄድ ትእዛዝ አልተሰጠንም የሚል ነበር።
በስፍራው የተገኙት የኢዜማ አመራሮች ሙሉ ትብብር ያደረጉ ሲሆን፤ ስለመግለጫው ለሰላም ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ለፖሊስ አባላቱ አስረድተዋል። ወደ ሰላም ሚኒስቴር በመደወልም የተፈጠረውን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሳወቁ ሲሆን፤ የፖሊስ አባላቱን ከሰላም ሚኒስቴር ጋርም በስልክ የማገናኘት ሥራ ተሠርቷል። ነገር ግን የፖሊስ አባላቱ መልሰው "የሰላም ሚኒስቴር ሊፈቅድ የሚችለው ስብሰባዎችን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አይደለም። የመግለጫ ጉዳይ የሚመለከተው ፖሊስን ነው" በሚል መግለጫውን በመከልከል ጸንተዋል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈጸመ ያለውን የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላን አስመልክቶ የሠራውን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ለማሳወቅ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተስተጓጉሏል።
ትላንት የአዲስ አበባ መሬት በሕገወጥ መንገድ እየታጠረ ሲወረር እና ሲዘረፍ ማቆም ያልቻሉ የሕግ አስከባሪዎች፤ በሕጋዊ መንገድ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ አጥር ኾነዋል። የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደዛሬው ዐይነት እክል ትላንትናም አላስቆመንም፤ ዛሬም አያስቆመንም! የተፈጸመ ስሕተት ካለ አዳምጦ ለማረም ከመዘጋጀት ይልቅ የዜጎችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በማፈን እና እውነቱን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ለመራቅ መሞከር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት እንደኾነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ዛሬ በተከሰተው መግለጫውን የማስተጓጎል ተግባር እውነታውን ማድበስበስ እና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም።
ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በጥናታችን የደረስንበትን ውጤት አያይዘን የነሱን ምልከታ በጥናት ውጤታችን ውስጥ ለማካተት ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀን የነበረ ቢኾንም፤ ሁሉም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመኾናቸው በተጨማሪ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የላክንላቸውን ደብዳቤም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በጥናቱ የደረሰበትን ሕገ ወጥነት እና ኢፍትሐዊነት ሰኞ ነኀሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት 8 ሰዓት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። ሐሳባችንን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ወደኋላ እንደማንል እና ያገኘነውን ውጤት ሕዝብ ጋር እንደምናደርስ እንዲያውቁት በድጋሚ ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ልከናል።
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት



