የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሕወሓትን ከአባልነት አገደ
አቶ ደረጀ በቀለ የኢትዮጵያ የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሰብሳቢ
“ሕወሓት እና ኢዲዩ የጥምረቱን ጉዞ ለማደናቀፍ እና አገር ለማተራመስ እየሠሩ ነው” ጥምረቱ
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 25, 2020)፦ በሕወሓት አሰባሳቢነት የተደራጀ መኾኑ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት፤ ሕወሓት እና ኢዲዩን ከአባልነት ማገዱን አስታወቀ።
የፌዴራሊስት ኃይሎች የጥምረት አባል የኾኑት ሕወሓት እና ኢዲዩ ከጥምረቱ መታገዳቸውን ያስታወቀው፤ ለሁለት ቀናት ሲያካሒድ የነበረውን ጉባዔ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው።
ወደ 25 የሚደርሱ አባላት አሉት ተብሎ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ምጥረት፤ ሁለቱን አባል ፓርቲዎች ያገደው የጥምረቱን ጉዞ ለማደናቀፍ እና አገር ለማተራመስ እየሠሩ ነው በሚል ነው።
እንዲህ ዐይነቱን ተግባር መፈጸም፤ ከጥምረቱ ዓላማ፣ አሠራር እና ደንብ መሠረት ተቀባይነት የሌለው በመኾኑ፤ ሕወሓት እና ኢዲዩ ከጥምረቱ አባልነታቸው እንዲታገዱ ሊወሰን መቻሉን በመግለጫው አመልክቷል።
ከዚሁ መግለጫ ጋር በተያያዘም በተለይ ሕወሓት ሕብረቱን የራሱ ጥገኛ አድርጎ ሊጠቀምበት እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም በመጥቀስ፤ ጥምረቱ ይህንን ዐይነቱን አካሔድ አይቀበልም ብሏል።
በተለይ የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው ሕወሓት እና ኢዲዩ የጥምረቱ ማዕከል መቀሌ እንዲኾን በመፈለጋቸው፤ አዲስ አበባ በተካሔደው 3ኛ እና 4ኛ የጥምረቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ባለመፍቀዳቸው ሳይገኙ ቀርተዋል።
ጥምረቱ ከዚህ ቀደም ከሕወሓት በተለየ፤ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ መራዘሙ አግባብ መኾኑን በመግለጽና አቋሙን በማሳወቅ፤ መቀሌ የታሰበውን የጥምረቱን መቀመጫ አዲስ አበባ በማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛል።
የጥምረቱ የአደረጃጀት ኮሚቴ ጥምረቱ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በበኩላቸው “ፓርቲው የጥምረቱ አባላት ለመከፋፈል የተለያዩ ጫናዎች እየፈጠረ ነው” ይላሉ። “ይህ ብቻ ሳይሆን፤ ሕወሓት ጥምረቱን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ አገርን ለማወክ እየተንቀሳቀሰ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፓርቲው በጥምረቱ ስብሰባ ላይ እንደማይገኝና የጥምረቱ ስብሰባም መቀሌ ካልተካሔደ ተቀባይነት እንደሌለው እየገለጸ መኾኑን የገለጹት አቶ ቶሎሳ፤ “ሕወሓት እኔ ያልኩት ካልኾነና እኛ ካልመራን ትክክል አይደለም የሚል” ግትር አቋም ያራምዳል ሲሉም ሕወሓትን ይከሳሉ።
ሕወሓት በቀጣይ ከጥምረቱ ጋር “ይቀጥል ወይስ ይሰረዝ” በሚለው ጉዳይ ላይ የጥምረቱ አባላት ሰፋ ያለ ውይይት እንዳደረጉ የሚያመለክተው መረጃ፤ በውይይቱ የተወሰኑ አባላት ሕወሓትን ጨምሮ ሌሎች መተዳደሪያ ደንቡን የማያከብሩ ከጥምረቱ ይሰረዙ ሲሉ፣ በቁጥር በርከት ያሉት ደግሞ “አንድ እድል ይሰጣቸው” ማለታቸውን መረጃው አመልክቷል። በመጨረሻም ጥምረቱ ሕወሓት በቀጣዩ ጉባዔ እንዲሳተፍ ጥሪ ተደርጎ አቋሙን ግልጽ ያድርግ በማለት ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ተጠቅሷል። “መጨረሻ ላይ ግን ሁሉም የጥምረቱ አባላት በሁለቱ ፓርቲዎች መሰረዝ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል” በማለት ከጉባዔው በኋላ የደረሱበትን ስምምነት ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በተካሔደው የጥምረቱ የአዲስ አበባ ጉባዔ ላይ ጥምረቱ በአባልነት ከያዛቸው 25 ፓርቲዎች ውስጥ፤ ጉባዔው 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች መገኘታቸውና አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥምረቱን መቀላቀላቸው ተገልጿል። (ኢዛ)



