ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ታሪፍ 100 በመቶ ዋጋ እንዲጨምር ተወሰነ
የኮድ ሁለት ተሽከርካሪዎች ገደብ ተነስቷል

ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 27, 2020)፦ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ ተግባራዊ እንዲኾኑ ተወስነው ከነበሩት መመሪያዎች ውስጥ ኮድ ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብን የተመለከተውና በሦስት ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተገለጸ።

ዛሬ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ ማሻሻያ የተደረገባቸው አራት ጉዳዮች፤ ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ከፊል እንቅስቃሴ ክልከላ፤ የማስክ (የአፍና የአፍንጫ ጭንብል) አጠቃቀም፤ በአገር አቋራጭ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ናቸው።

ማሻሻያዎቹ የተደረጉበትን ምክንያት በመግለጫው ላይ ያመለከተው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች 100 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ ጭምር ውሳኔ የተሰጠበት ማሻሻያ ተደርጓል። በማሻሻያው ላይ ዓቃቤ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰጠ ፕሬስ መግለጫ

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በመንግሥትና በባለድርሻ አካላት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ትእዛዞች፣ ክልከላዎችና መልእክቶች እየተላለፉ ነው። እነዚህን መልእክቶችና ትእዛዞች ሰምቶ ለራስ በመፈጸምና ሌሎችን እንዲፈጽሙት በማድረግ በኩል በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም፤ ነገር ግን በርካታ በሚባለው ሕብረተሰቡ ዘንድ የመዘናጋት፣ የቸልተኝነትና በሽታውን አስመልክቶ የሚሰጡ ትእዛዛቶች ወደ ጎን በመተው የሚሰጡ መግለጫዎችን የመላመድና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎች እየተስተዋለ ይገኛል።

በቅርቡ በመንግሥት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ወሰጥ ያደረግነው ምልከታ ከቅደመ ጥንቃቄ ጋር በተያያዘ የመዘናጋት፣ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ አሳሳቢ እንደኾነ ለማረጋገጥ ችለናል። ማኅበረሰባችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም በግብይት ቦታዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መሰጫ አካባቢ እያሳየ ያለው መዘናጋትና ሕጎቹን ያለማክበር ጉዳይ አሳሳቢ ነው።

ይህ የኮሮና ቫይረስ በአገራችን በተገኘበት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች ጋር ሰነጻጸር እየቀነሰ መዘናጋት እየጨመረ ሲሆን፤ በተቃራኒው አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እጅጉን አሳሳቢና ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ እየኾነ ይገኛል።

መንግሥት በሽታውን ለመከላከልና ሥርጭቱን ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ፤ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ መኾኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያ ቁጥር 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር 2/2012 ማሻሻያዎችን የያዘ መመሪያ ቁጥር 4/2012ን አጽድቆ ሥራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ ሰጥቷል።

በዚሁ መሰረትም በመመሪያ ቁጥር 4 በኮድ 2 የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረው ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ፣ የማስክ አጠቃቀም፣ በአገር አቋራጭ የሕዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

የኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ መጣል የሚገባው የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ፤ በከፊል በመገደብ ግለሰቦች ቤታቸው እንዲውሉ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተደርጎ በሙሉና በጎዶሎ መለያ ቁጥር ከፊል እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ኾኖም የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበው መልኩ ቤታቸው ከመዋል ይልቅ የሕዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ፤ እንዲሁም ተራቸው ባልኾነ ቀን ቤታቸው ከመዋል ይልቅ በሰፊው የመንቀሳቀስ ሁኔታ የተስተዋለ መኾኑ ክልከላውን መልክ መቀየር አሰፈላጊ ኾኗል።

በመኾኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረው ክልከላ ተነስቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንዲተገበር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወስኗል።

የእንቅስቃሴ ገደብ መቀነሻ አሠራሮች አንዱ የኾነው በአገር አቋራጭ ተሽከሪካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ነው።

የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመላክታል።

በዚሁ መሠረት አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች መደበኛ የወንበር አቅማቸው ከ45 (አርባ አምስት) ሰው በላይ የኾነ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋው 75% እንዲኾን የተወሰነ ሲሆን፤ መደበኛ የወንበር ቁጥራቸው እስከ (45) አርባ አምስት ሰው የኾኑ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ 100% መኾኑ ተወስኗል።

በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተሻሻለው መመሪያ መሠረት የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከቤት ውጭ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግን ግዴታ እንዲኾን ወስኗል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በፋብሪካዎች የተሠራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን ይችላል። ይህን ግዴታ በማስፈጸም ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወሰኗል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ መግቢያ ሰዓት 1፡30 እንዲኾን የተቀመጠ ሲሆን፤ መውጫ ሰዓቱም 9፡30 እንዲኾን ተደርጎ ተሸጋሽጓል። ይህም የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ነው።

በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ሕብረተሰብ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት በመኾኑ፤ የሚታዩ መዘናጋቶችን እና ችላ ባይነትን በመቅረፍ ሁላችንም ሕግና ሥርዓቱን ማክበር ግዴታ እንደኾነ በመገንዘብ፤ መላው የአገራችን ሕዝብ እራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን የኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው ጉዳት ለአፍታም ሳይዘናጋ ለመጠበቅ ርብርብ እንዲያደረግ ጥሪያችንን እናቀረባለን።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለተጨማሪ መረጃ ስልክ፡- 0111-5-51-50-99

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ