በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የበለጠ ሥጋት እየፈጠረ ነው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ረቡዕ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
የውጭ ጉዞ ታሪክና በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች የበለጠ በቫይረሱ እየተጠቁ ነው
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 20, 2020)፦ የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ከተሰማ ሁለት ወራት በላይ ቢቆጠሩም፤ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ችግሩ አደገኛ እየኾነ መምጣቱን እያመላከተ ነው። ዛሬ በ24 ሰዓታት ውስጥ የተደረገውን የምርመራ ውጤት ተከትሎ ከተሰጠው ሪፖርት በኋላ የጤና ሚኒስትሯ የሰጡት መግለጫም አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የወረርሽኙ ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን የሚያስረዳ ነው። የውጭ ጉዞ ታሪክና በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች የበለጠ በቫይረሱ እየተጠቁ ነው።
እንደ ጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የዛሬ (ረቡዕ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.) መግለጫ ወረርሽኙ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ ሥርጭት አስጊ ስለመኾኑ የሚያመለክተው ይኸው መግለጫ፤ እስከ ዛሬዋ ዕለት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተገለጹት ሰዎች ውስጥ 228ቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኾነው መገኘታቸው አንድ ማሳያ ነው።
ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እያደረገ የመጣው ግን የአዲስ አበባው ቁጥር ማደጉ ብቻ ሳይሆን፤ በአሁኑ ወቅት እንደ ዶ/ር ሊያ ገለጻ ወረርሽኙ በሰባት ክልሎች እና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች ላይ የቫይረሱ መከሰት ነው።
ሚኒስትሯ የወረርሽኙን መስፋፋት አመላካች ነው ብለው የጠቀሱት ሌላው ማሳያ፤ በአገሪቱ ካሉ 80 ዞኖች ውስጥ 40 በሚኾኑት የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን ነው። የበሽታው ሥርጭት ምን ያህል እንደተስፋፋ ከማመላከታቸውም በላይ፤ አሁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሌላው ወረርሽኙ አደገኛ እየኾነ መምጣቱን የሚያጠናከረው እውነታ ደግሞ፤ ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ተያዙ ከሚባሉት ሰዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከውጭ የሚመጡ ሰዎች እንደነበሩ ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ይህ ሁኔታ እየተቀየረ መምጣቱና በተቃራኒው በአገር ቤት ውስጥ ነዋሪ የኾኑና የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች ቫይረሱ እየተገኘባቸው መምጣቱ ነው።
ከዚህም ሌላ ከዛሬው ከዶክተር ሊያ መግለጫ መረዳት የሚችለው ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የበሽታው መስፋፋት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መኾኑን ነው። ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ስለመኾኑም ያስገነዘቡት ዶ/ር ሊያ፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባበት ወቅት መኾኑን አስገንዝበዋል።
በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው፤ “አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ምንም ዐይነት የጉዞ ታሪክም ኾነ ከበሽታው ተጠቂዎሽ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ግለሰቦች 93 በመቶ የሚኾኑት የተገኙት በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ መኾናቸውን ያሳያል” ብለዋል። ይህም በአዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ሥርጭቱ ይልቅ በእነዚህ ሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ ጐልቶ መታየቱን አሳይቷል።
እነዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከኾነ፤ የበሽታው ሥርጭት መጨመር እየታየ ያለውና በቫይረሱ እየተጠቁ ያሉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ያለው፤ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች ላይ እንደኾነ ሊጠቁም ችሏል።
በአገር ደረጃ ከተያዙት 365 ሰዎች ውስጥ 228 የሚኾኑት በአዲስ አበባ መገኘታቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ፤ ይህም ከጠቅላላው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ውስጥ 62.5 በመቶው በአዲስ አበባ የተገኙ መኾናቸውን ነው። ይህም በመኾኑ አዲስ አበባ ላይ ጠንክሮ ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የተቋማቱ ኃላፊዎች ጨምረው እንደገለጹት፤ በተለይ በዚህ በበዓል ወቅት ማኀበረሰቡ በጥንቃቄ ግብይት እንዲፈጽሙ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ (ረቡዕ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም) ይፋ በተደረገው ሪፖርት፤ በ24 ሰዓታት ውስጥ 3,460 ለሚኾኑ ሰዎች የላብራቶር ምርመራ ተደርጎላቸቅው ቫይረሱ በሃያ አራት ሰዎች ላይ ተገኝቷል። ከ24ቱ ተጠቋዎች ውስጥ ዘጠኙ ከአዲስ አበባ፣ ሰባቱ ከትግራይ፣ ስምንቱ ከአማራ ክልል መኾናቸው ታውቋል።
እንደ ሪፖርቱ ከ24ቱ ውስጥ 12ቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፤ ስምንቱ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ናቸው ተብሏል። ቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ ምንም ዐይነት የጉዞ ታሪክና ንክኪ የሌላቸው ናቸው። እስከዛሬ ድረስ በአገሪቱ ለ65,760 ሰዎች የላቦራሮቲ ምርመራ መደረጉ ታውቋል። (ኢዛ)



